አታላይ አምላክ ብቁ ያልሆነ አዳኝ
እስልምና ስለ አላህና ስለ ኢየሱስ በእርግጠኝነት የሚያስተምረው ሲመረመር፡፡
David Wood
ትርጉምና ቅንብር በአዘጋጁ
ባለፉት ሁለት ሺ ዓመታት ውስጥ ክርስትያኖች የጌታ ኢየሱስን ሞትና ትንሳኤ በማወጅ ላይ ይገኛሉ፡፡ የእስልምና እምነት ግን እነዚህን (የጌታን ሞትና ትንሳኤ) ሁለቱንም የክርስትና መሰረታዊ እምነቶች ይክዳል ይቃወማልም፡፡ ከዚህም ባሻገር ይህንን እውነታ በተመለከተ ክርስትያኖች ከሚቀበሉት ውጭ የሆነን ታሪክ እንዲሁም የተለየ አባባልን ለማስቀመጥም ይሞክራል፡፡ ነገር ግን ለነዚህ ክህደቶች ሙስሊሞች የሚሰጧቸው ማብራሪያዎች በራሳቸው በኩል እጅግ ከፍተኛ ዋጋን የሚያስከፍላቸው ይሆናል፡፡ ምክንያቱም እነዚህን እውነቶች በተመለከተ የየያዙት የታሪክ ሥሌት የሚከተሉትን ሁለት ነገሮች ያስከትላል እነዚህም፡-
አንደኛ፡- እግዚአብሔርን እጅግ አሰቃቂ የሆነ አታላይ ሲያደርገው፤
ሁለተኛ፡- ጌታ ኢየሱስን ደግሞ በነቢያት ታሪክ ውስጥ እጅግ አሳዛኝ የሆነ ውድቀትን የወደቀ ነቢይ ያደርገዋል፡፡
ስለዚህም ሙስሊሞች አላህ እውነት ነው፤ እንዲሁም ኢየሱስ ደግሞ ከአላህ ነቢያት እንዱና ኃይለኛው ነው በማለት ቢናገሩም እንኳን እነዚህ አባባሎቻቸው በሙሉ ትርጉመ ቢስ ነው የሚሆኑት ምክንያቱም የእስልምናን መሰረታዊ ትምህርት (ዶግማ) በከፍተኛ የሐሰት ትምህርት አደጋ ውስጥ የሚጥሉት ናቸውና፡፡ እነዚህን ለመመልከት ነጥቦቹን እንደሚከተለው እናጢናቸው፤
አላህ ክርስትናን በድንገት (ሳይታሰብበት) ነው የጀመረው
የእስልምናን ትምህርት ብንመረምር የምናገኘው ነገር ቢኖር አላህ ክርስትናን መጀመር ብቻ ሳይሆን በዓለም ውስጥ ካሉት ታላላቅ ኃይማኖቶች መካከል አንዱ እንዳደረገው ነው፡፡ ይህ እውነት እጅግ አስገራሚ ነው ምክንያቱም እስላሞች ክርስትናን እንደ ሐሰት ሃይማኖት ያቱታልና፡፡ በእርግጥ ሙስሊሞች የሚከራከሩት ክርስትና የሐሰት ሃይማኖት የሆነው ክርስትያኖች ስለበከሉት ነው በማለት ነው፡፡ ይሁን እንጂ በቁርአን ላይ እንደተገለፀው የክርስትና ትምህርት በመጀመሪያ ደረጃ ለማርያም ልጅ የተሰጠ የአላህ መልክት ነበር፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የኢየሱስ ተከታዮች ከእስልምና ጋር የሚመሳሰል ነገር እንደነበራቸው ሊያሳይ የሚችል - ቅንጣትም የሆነ የታሪክ ማስረጃ የለም፡፡ በመሆኑም ይህ የእነሱ አባባል ከእውነት የራቀና ታሪካዊ መሠረት የሌለው ነገር ነው፡፡ በእስልምና መሰረት ክርስትና የተበላሸ (የተበረዘ) ነው፣ ይህም የሆነው በራሱ በአላህ ነው፡፡ እስላሞች ይህንን ለምን እንደሚናገሩ ለመረዳት የሚከተሉትን ማስረጃዎች እንመልከት፡፡
ማስረጃ አንድ፡- ቁርአን ኢየሱስ የአላህ መልከተኛ እና የእስላም ነቢይ ነው በማለት ይናገራል፡፡
ቁርአን ምዕራፍ 19 የሚናገረው ኢየሱስ ገና እንደተወለደ የእስልምናን አስተምህሮ መስበክ እንደጀመረ ነው፡፡ ‹.... ከበታችዋም እንዲህ ሲል ጠራት፡- አትዘኝ ጌታሽ ከበታችሽ ትንሽን ወንዝ በእርግጥ አድርጓል ...› ቀጥሎም፤ ‹(ሕፃኑም) አለ፡- እኔ የአላህ ባሪያ ነኝ መጽሐፍን ሰጥቶኛል ነቢይም አድርጎኛል፡፡ በየትም ስፍራ ብኾን ብሩክ አድርጎኛል፤ በሕይወትም እስከ አለሁ ሶላትን በመስገድ ዘካንንም በመስጠት አዞኛል፡፡ ለእናቴም ታዛዥ (አድርጎኛል)፤ ትዕቢተኛ እምቢተኛም አላደረገኝም፡፡ ሰላምም በእኔ ላይ ነው በተወለድሁ ቀን በምሞትበትም ቀን ሕያው ኾኜ በምቀሰቀስበትም ቀን፤› 19.30-33፡፡
ስለዚህም በዚህ ማስረጃ መሠረት ኢየሱስ የእግዚአብሔርን መልክት በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ሲሰብክ ነበር ይህም ወደ ሰማይ እስከተወሰደበት ጊዜ ድረስ ነበር፡፡ በቁርአን መሠረት ኢየሱስ ያመጣው ወንጌል ከእሱ በፊት ከነበሩት ነቢያት ምንም የተለየ አልነበረም፡፡ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ባሪያና ነቢይ ሆኖ በቁርአን መሰረት እስልምናን ሰብኳል ማለት ነው፡፡ ‹ለናንተ ከሃይማኖት ያንን በርሱ ኑሕን ያዘዘበትን ደነገገላችሁ ያንንም ወደናንተ ያወረድነውን በርሱ ኢብራሂምን ሙሳንና ዒሳንም ያዘዝንበትን ሃይማኖትን በትክክል አቋቁሙ በርሱም አትለያዩ ማለትን (ደነገግን)፤ በአጋሪዎቹ ላይ ያ ወደ እርሱ የምትጠራቸው ነገር ከበዳቸው አላህ የሚሻውን ሰው ወደ እርሱ (እምነት) ይመርጣል የሚመለስንም ሰው ወደ እርሱ ይመራል› 42.13፡፡ እንዲሁም ደግሞ ‹የመርየም ልጅም ምሳሌ በተደረገ ጊዜ .... እርሱ በርሱ ላይ የለገስንለት ለእስራኤልም ልጆች ታምር ያደረግነው የኾነ ባሪያ እንጂ ሌላ አይደለም ... ዒሳ በታምራቶች በመጣ ጊዜም አላቸው፡- በእርግጥ በጥበብ መጣኋችሁ የዚያንም በርሱ የምትለያዩበትን ከፊሉን ለእናንተ ላብራራላችሁ (መጣሁ) አላህንም ፍሩ ታዘዙኝም፡፡ አላህ ጌታዬ ጌታችሁም ነውና ተገዙት ይህ ቀጥተኛ መንገድ ነው› 43.57-59 እና 63-64፡፡
ስለዚህም ኢየሱስ ያሳለፋቸው 33 ዓመታት ከመወለዱ እስከ አረገበት ቀን ድረስ ለእስራኤል ልጆች እስልምናን በመስበክ ነበር ማለት ነው፡፡ የተሰቀለ ከመሰለበት (ተሰቀለ ከሚባልበት) ጊዜ በእሱ ስብከት የተለወጡት እንደሚያመለክቱት ከሆነ፤ የእሱ የበፊት ስብከት በመጠኑም ቢሆን የተሳካለት ነበር የሚመስለው፡፡
ማስረጃ ሁለት፡ ቁርአን የሚናገረው ኢየሱስ እጅግ ብዙ ሰዎችን በትምህርቱ ለውጦ እንደበረ ነው፡፡
ኢየሱስ የመጀመሪያውን ዓይነት እስልምናን በመስበክ ሕይወቱን በሙሉ እንዳሳለፈ ሁሉ ለደቀመዛምርቱ ይሰብከው የነበረው መልክት ማተኮር የነበረበት በዋና ዋናዎቹ (በመሠረታዊዎቹ) የእስልምና ትምህርቶች ላይ መሆን ነበረበት፡፡ ደቀመዛምርቱም መሆን የነበረባቸው የአሁኑን እስላሞች ዓይነት ነበር፡፡ ይህም እስልምና ስለ ኢየሱስ ተከታዮቸ በትክክል የሚናገረው ነገር ነው ማለት ነው፡፡ ‹ዒሳ ከነርሱ ክህደት በተሰማው ጊዜ፡- ወደ አላህ (ተጨምረው) ረዳቶቼ እነማናቸው? አለ፤ ሐዋርያት፡- እኛ የአላህ ረዳቶች ነን በአላህ አምነናል እኛም ትክክለኛ ታዛዦች መኾናችንን መስክር አሉ፡፡› 3.52፡፡ እንዲሁም ደግሞ ‹ወደ ሐዋርያትም በኔና በመልክተኛዬ እመኑ በማለት ባዘዝኩ ጊዜ (አስታውስ) አመንን እኛም እስላሞች መኾናችንን መስክር አሉ፡፡› 5.111 ቀጥሎም ደግሞ ‹ኑሕን ኢብራሂምንም በእርግጥ ላክን በዘሮቻቸውም ውስጥ ነቢይነትንና መጽሐፎችን አደረግን ከነሱም ቅን አልለ ከነሱም ብዙዎቹ አመጠኞች ናቸው፡፡ ከዚያም በዱካዎቻቸው ላይ መልክተኞቻችንን አስከታተልን የመርየምን ልጅ ዒሳንም አስከተልን ኢንጂልንም ሰጠነው በነዚያም በተከተሉት (ሰዎች) ልቦች ውስጥ መለዘብንና እዝነትን አዲስ የፈጠሩዋትንም ምንኩስና አደረግን በነርሱ ላይ (ምንኩስናን) አልጻፍናትም ግን የአላህን ውዴታ ለመፈለግ ሲሉ (ፈጠሩዋት) ተገቢ አጠባበቅንም አልጠበቋትም ከነርሱም ለነዚያ ላመኑት ምንዳቸውን ሰጠናቸው ከነሱም ብዙዎቹ አመጠኞች ናቸው› 57.26-27፡፡
ከዚህ በላይ ባየነው ማስረጃ መሠረት ቁርአን ትክክል ከሆነ ኢየሱስ አንዳንዶቹን እስራኤላውያንን ወደ እስልምና ቀይሮአቸው ነበር ማለት ነው፡፡ ለዚህ እውነታ ምንም ታሪካዊ ማስረጃ ባይኖርም ለመነጋገር ያህል ግን የኢየሱስን መልክት በማመን ወደ እስልምና እምነት የተለወጡ አይሁዶች በመጀመሪያው መቶ ዓመት ምህረት ነበሩ ብለን እናስብ፡፡ ይሁን እንጂ ቆይቶም እንደምንመለከተው ይህ አስተሳሰብ ለሙስሊም የሃይማኖት ተከራካሪ ምሁራን ትልቅ ችግርን ነው የሚያመጣባቸው፡፡
ማስረጃ ሦስት፡- በመጀመሪያው መቶ ዓመት ከአይሁድ ወደ እስልምና የተለወጡ አይሁዶች፣ ለብዙ ጊዜ በዚያው እምነት ውስጥ እልፀኑም ነበር ማለት ነው፡፡
የኢየሱስ የመጀመሪያ ተከታዮች እስላሞች ነበሩ የሚለው ሐሳብና አመለካከት እጅግ የምር የሆኑ በርካታ ጥያቄዎችን አስነስቷል፡፡ በመጀመሪያው ዘመን ስለነበሩ ሙስሊሞች ለምን ምንም ነገር አልሰማንም ነበር? ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የመጀመሪያው መቶ ዓመት ተከታዮች እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ ታሪካዊ ማስረጃዎች አሉን፡፡ ይሁን እንጂ የክርስትና እምነት ተከታዮች የክርስቶስ ተከታይ የነበሩ እስላሞችን ሙልጭ አድርገው እንዳጠፉ የሚገልጥ ምንም የሆነ ታሪካዊ ማስረጃ የለንም፡፡ ስለዚህም እንዲህ ዓይነቱ አባባልና አመለካከት ትርጉም የለሽና ዘበት የሚሆን ነው፡፡ ስለ መጀመሪያው ዓመት አጠቃላይ ታሪክ የክርስትናም የክርስትያን ያልሆኑም የማስረጃዎች ምንጮች አሉን ነገር ግን ከእነዚህ ታሪካዊ ምንጮች ውስጥ አንዳቸውም ቢሆኑ ስለ ክርስትያን-ሙስሊሞች መኖር ምንም የተናገሩት ነገር የለም፡፡ እዚህ ላይ በፍፁም እርግጠኝነት ለመናገር የምንችለው ነገር የኢየሱስ ሞት በዘመኑ በነበሩት ባለስልጣናት ዘንድ በትክክል የታወቀ ነገር የነበረ መሆኑን ነው፡፡ እንዲሁም ደግሞ የኢየሱስ የመጀመሪያዎቹ ተከታዮች ጴጥሮስ ያዕቆብ እና ዮሐንስን ጨምሮ ኢየሱስ ለኃጢአታቸው በመስቀል ላይ እንደሞተና በሦስተኛው ቀን ከሞት እንደተነሳ አምነው እንደነበረ ነው (ከዚህም በተጨማሪ ደቀመዛምርቱ ኢየሱስ የመለኮታዊው አብ ልጅ እንደሆነ ያምኑ እንደበረ ነው ነገር ግን ይህ አሁን ለያዝነው ነገር መናጋሪያ ነጥቤ አይደለም)፡፡ አራቱም የአዲስ ኪዳን ወንጌሎች የሚናገሩት የቀደሙት ክርስትያኖች የኢየሱስን ሞት እና ትንሳኤ እንደሚያረጋግጡ ነው እንዲሁም የሐዋርያት ስራ፡፡ የጳውሎስም ደብዳቤ እንዲሁ የኢየሱስን ሞትና ትንሳኤ ያረጋግጣል (ይናገራል)፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የጥንት የሃይማኖት መግለጫ በትክክል እንደሚያስረዳው በ1ቆሮንቶስ 15 ላይ የተመዘገበው እውነታ ከኢየሱስ ሞት ጥቂት ዓመታት በኋላ እንደተፃፈ ሲሆን በሐዋርያት ዘመን ስለነበረው እምነት በጣም ጥንታዊና ጠቃሚ የሆነን ማስረጃ የሚሰጥ እንደሆነ ነው፡፡ ያም ማስረጃ እንደሚከተለው ይላል፡ ‹እኔ ደግሞ የተቀበልሁትን ከሁሉ በፊት አሳልፌ ሰጠኋችሁ እንዲህ ብዬ፡- መጽሐፍ እንደሚል ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ሞተ ተቀበረም መጽሐፍም እንደሚል በሶስተኛው ቀን ተነሣ ለኬፋም ታየ በኋላም ለእስራ ሁለቱ ...› 1ቆሮንቶስ 15.3-5፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ከአዲስ ኪዳን ውጭ የሆኑ እና ስለክርስቶስ ተከታዮች የሚናገሩ የጥንት የክርስትና ጽሑፎች አሉን፡፡ ለምሳሌም ያህል፤ የሮሙ ክሌመንት የሮም ቤተክርስትያን ቢሾፕ በመሆን በጴጥሮስ ተሾሞ የነበረው የጻፈው፣ ሐዋርያቱ በኢየሱስ ሞትና ትንሳኤ ያምኑ እንደነበረ ነው [see 1 Clement 42:3.] ፖሊካርፕ በሐዋርያው ዮሐንስ ተሾሞ የነበረ ሲሆን የኢየሱስን ከሞት መነሳት እጅግ በጣም ብዙ ጊዜ በጽሑፎቹ ውስጥ መዝግቦት ይገኛል፡፡ [See Polycarp, To the Philippians 1:2, 2:1-2, 9:2, 12:2] ከዚህም በተጨማሪ እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ ክርስትያናዊ ያልሆኑ ማስረጃዎች አሉን፡፡ እነዚህም ስለ ኢየሱስና ስለደቀመዛምርቱ እጅግ በጣም ጠቃሚ የሆኑ ማስረጃዎችን የሚሰጡ ናቸው፡፡ በአይሁድ ታሪክ ጸሐፊ በጆሴፈስ እና በሮማን ታሪክ ጸሐፊ በታሲተስ መሠረት ኢየሱስ በጴንጤናዊው በጲላጦስ የግዛት ዘመን እንደተሰቀለ ተዘግቦ ይገኛል [See Josephus, Antiquities 18.64, and Tacitus, Annals 15.44.]፡፡ የሳሞስታው ሉሲያን ግሪካዊው የትችት (ቀልድን) ጸሐፊ ደግሞ እንደተናገረው ‹ታውቃላችሁ ክርስትያኖች እስከ አሁን ድረስ ሰውን ያመልካሉ - ያም የሚከተሉትን የከበሩ ስርዓቶች ያመጣላቸውን የተከበረ ሰውን ነው በዚያም ታሪክ መሰረት እሱ ተሰቅሏል› በማለት ተናግሯል [Lucian of Samosata, The Death of Peregrine, 11-13.]፡፡ የአይሁድም ታልሙድ ሳይቀር የክርስቶስን መሰቀል መዝግቦታል[Talmud, Sanhedrin 43a.]፡፡
ስለዚህም እጅግ በጣም አሳማኝ የሆነው የመረጃ ትርጓሜ እንደሚያሳያው ከሆነ ከሚከተሉት እውነታዎች አኳያ ቁርአን የሚከተሉትን ሲናገር ሙሉ ለሙሉ ስህተት ነው እነዚህም፡-
1. ኢየሱስ በፍፁም አልሞተም እና
2. የኢየሱስ ተከታዮች በሙሉ ሙስሊሞች ነበሩ የሚሉት ናቸው፡፡
ይሁን ደህና በማለት ደግ እንሁንና አባባሉን እንቀበለው፤ እንዲሁም ደግሞ ካሉት እውነታዎች (ጭብጥ ማስረጃዎች) ባሻገር በመጀመሪያው መቶ ዓመት ሙስሊሞች ነበሩ ብለንም እንበል፣ ነገር ግን የእነሱ የመኖራቸው ማስረጃ በሙሉ ቆይቶ በክርስትያኖች ጠፋ ተደመሰሰ ማለት ነውን? በምንም መልኩ እውነት የማይመስለውን ይህንን አባባል እኛ እንቀበለው ብንልም እንኳን - ነገሩ እራሱ ለሙስሊሞች ትልቅ ችግርን የሚያስከትልባቸው ነው፡፡ እነዚህ የመጀመሪያው መቶ ዓመት ሙስሊሞች ምን ሆኑ፤ ወይንም ምን አገኛቸው? ያኔ የነበረው እስልምና በኢየሱስ መስዋዕትነት ሞትና ትንሳኤን በማመን እንዴት ሊተካ ቻለ? የኢየሱስ የ33 ዓመታት የእስልምና እምነት ስብከት፤ በማይቆይ (ዘለቄታዊ ባልሆነ) ሁኔታ ውስጥ እንዴት ወደቀ?
ሙስሊሞች ለእነዚህ ጥያቄዎች አሁንም መልስ ሊሰጡ የሚችሉትና በጣም የሚቀራረበው ክርስትና የኢየሱስን መልክት አጠፋው እንዲሁም የክርስትያኖች ቤተክርስትያን የኢየሱስን የእስልምና አስተምህሮ ደመሰሰው ወይንም አባለሸው በማለት ነው፡፡ ይሁን እንጂ እውነተኛ የሆነ ማንኛውም እስላም ይህንን አባባል በፍፁም አይቀበለውም ምክንያቱም ይህ አባባልና ክስ ቁርአን የሚናገረውን አባባል የሚደብቀው (የሚቃረነው) ይሆናልና፡፡
ማስረጃ አራት፡- ኢየሱስ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ እንደሞተ እንዲያምኑ አላህ ሰዎችን እንዳታለላቸው ቁርአን ይናገራል፡፡
በቁርአን መሠረት ኢየሱስ አንዳንድ አይሁዶችን ወደ እስልምና እንደቀየረ ነው፡፡ ነገር ግን ከታሪክ እንደምናውቀው የመጀመሪያዎቹ የኢየሱስ ተከታዮች መሞቱንና መነሳቱን በሚገባ አምነውበት ነበር፡፡ ስለዚህም ኢየሱስ ካረገ በኋላ ምንም እስላም ላለመኖሩ ግልጥ የሆነው ምክንያት የኢየሱስ ተከታዮች የነበሩት በሙሉ በመስቀል ላይ መሞቱንና ከሞትም መነሳቱን ማመናቸውን ነው፡፡ ስለዚህም እነዚያ የኢየሱስ ተከታዮች ይህንን ሐሳብ ከየት ነበር ያገኙት? በቁርአን መሰረት ኢየሱስ በመስቀል ላይ ሞተ የሚለው ሐሳብ የመነጨው (ወይንም የጀመረው) ከአላህ ነበር፡፡ የሚከተለውን ጥቅስ አስተውሉ፤
‹እኛ የአላህን መልክተኛ የመርየምን ልጅ አልመሲሕ ዒሳን ገደልን በማለታቸው (ረገምናቸው) አልገደሉትም ግን ለነሱ (የተገደለው ሰው በዒሳ) ተመሰለ፤ እነዚያም በርሱ ነገር የተለያዩት ከርሱ (መገደል) በመጠራጠር ውስጥ ናቸው ጥርጣሬን ከመከተል በስተቀር በርሱ ነገር ምንም እውቀት የላቸውም በእርግጥም አልገደሉትም፡፡ ይልቁንስ አላህ ወደርሱ አነሳው አላህም አሸናፊ ጥበበኛም ነው፡፡› ቁርዓን 4.157-158፡፡
እዚህ ጋ እንግዲህ የአላህ ብቸኛ ዓላማ ኢየሱስን መግደል የፈለጉትን ሰዎች ማሳሳት ነው (ማታለል) ነው ብለን ብናስብም ደቀመዛምርቱ ግን ለአላህ ማታለል ተታልለው ነበር ማለትም (ሰለባ) ሆነው ነበር ማለት ነው፡፡ ስለዚህም ክርስትያኖች ኢየሱስ በመስቀል ላይ ተሰቀለ እና ከሞትም ተነሳ የሚለውን ሐሳብ በማመናቸው ተጠያቂው ማነው? የኢየሱስን ጠላቶች ኢየሱስን እንደገደሉት ለማሳሳት (ለማታለል) አላህ ይህን አድርጎታል የሚለው የእስላሞች ሀሳብ ትክክል ከሆነ (ወይንም እንቀበለው ካልን) ይህም ደግሞ እንደገና ለእስላሞች ወደ ከባድ ችግር ውስጥ የሚያስገባቸው ነው የሚሆነው፡፡ ደቀመዛምቱን ማታለል ያልታቀደ ነው ብለን የምንል ከሆነ የምንመጣበት መደምደሚያ ሐሳብ የሚሆነው በዓለም ላይ ያለውን ታላቅ ሃይማኖት ለመመስረት እግዚአብሔር ምንም ሳያስብበት ያደረገው ነገር ነበር ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ያልታሰበበት ከነበረ እግዚአብሔር የስህተትን ሃይማኖት በመመስረት ላይ ነበር ማለት ነው፡፡ ስለዚህም የእስልምና አምላክ እጅግ በሚያስገርም መንገድ ምንም ነገርን የማያውቅ ወይንም እጅግ በጣም አታላይ ነው ማለት ነው፤ ይህም ደግሞ እሱ ሊሆን የሚችለው ከሁለቱ አንዱን ብቻ ነው፤ ማለት ነው፡፡
ይህም እንደገና የሚያመጣን በመሐመድ አቋም መሠረት በነቢያት ታሪክ ውስጥ እጅግ በጣም የከሰረው እና ያልተሳካለት ኢየሱስ ነበር ማለት ነው፡፡ ለ33 ዓመታት ሲሰብክ ነበር፤ (እንደተወለደ የጀመረውም የእስልምናን ትምህርት ነበር) ነገር ግን እሱ ከሞተ በኋላ የእስራኤል ልጆች በሁለት ትልልቅ ቡድኖች ተከፋፈሉ፡፡ የእሱን መልክት ያመኑቱ ክርስትያኖች ሆኑ እነሱም ሊታሰብ የማይቻልን ኃጢአት የሰሩ በደለኞች ሆኑ ምክንያቱም (የሽርክናን) ወንጀል ፈፅመዋልና፡፡ እንዲሁም ደግሞ የእሱን መልክት የተቃወሙቱ የእግዚአብሔርን ታላቅ ነቢይ መልክት ባለመቀበላቸው እጅግ ታላቅን ኃጢአት ፈፅመዋል፡፡ ስለዚህም ኢየሱስን ያመኑትም ሆኑ የተቃወሙት ሰዎች ማለትም ሁለቱም ወገን ስህተትን ፈፅመዋል ማለት ነው፡፡ በመሆኑም ማናቸውም ቢሆኑ በመጨረሻው የተረገሙና ወደ እሳት ባሕር የሚጣሉ ነው የሚሆኑት፡፡ ስለዚህም ሙስሊሞች ኢየሱስን ታላቅ ነቢይ አድርገው ማየታቸው በጣም የሚያስደንቅ ነገር ነው፡፡ እንደዚህ ከሆነ ደግሞ የሚመስለው እሱ ቢያንስ አንድ ወደ እስልምና የተቀየረ አማኝ ሊኖረው ይገባ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ እሱ ምንም እስላም የሆነ ተከታይ አልነበረውም፡፡ ከዚህም በላይ ደግሞ የእውነተኛ የእስላም ነቢይ ተከታዮቹን ለእግዚአብሔር ማታለል ተጋልጠው ከእስልምና መንገድ እንዳይመለሱ ማስጠንቀቅ ነበረበት፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ ይህንን መልክት በፍፁም አልተናገረውም፡፡
በእርግጥ እጅግ በጣም በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ በዓለም ላይ ያሉ ሰዎች በአሁኑ ጊዜ እስልምናን አይቀበሉም ምክንያቱም ኢየሱስ በመስቀል ላይ ስለኃጢአታቸው እንደሞተ ያምናሉና፡፡ ይህም ደግሞ በዚያን ጊዜ በአላህ የተደረገው ማታለልና ብቁ ባልሆነ መሲህ የተላለፈው መልክት ነበር ማለት ነው፡፡
አላህ በድንገት የጀመረውን የሐሰት ሃይማኖት አስፋፍቷል
እንግዲህ የእስልምናን ትምህርት እና እስላሞች የሚሄዱበትን ሎጂካዊ የመደምደሚያ መንገድ ስንከተል የምናስተውለው ነገር ቢኖር እግዚአብሔር ባለማስተዋል ወይንም ዝም ብሎ ክርስትናን እምነት እንደመሠረተ ነው፡፡ ነገር ግን ቁርአን እዚያ ሐሳብ ላይ አያቆምም፡፡ ቀጥሎም አላህ የፈጠረውን ምስቅልቅል ከማስተካከል ይልቅ ክርስትናን ወደሚቀጥለው ደረጃ ከፍ አድርጎታል ይላል፡፡
ማስረጃ አምስት፡ ክርስትና እንዲስፋፋ አላህ እንዳደረገ ቁርአን ይናገራል፡፡
እግዚአብሔር አንዴ በኢየሱስ ሞትና ትንሳኤ በውሸት እንዲታመን ካደረገ በኋላ ክርስትያኖች በትጋት ይህንን የሐሰት እምነት እንዲያስፋፉ በጣም ረድቷቸዋል፡፡ ‹እላንተ ያመናችሁ ሆይ የመርያም ልጅ ዒሳ ለሐዋርያቶቹ ወደ አላህ ረዳቴ ማነው? እንዳለ ሐዋርያቶቹም እኛ የአላህ ረዳቶች ነን እንዳሉት የአላህ ረዳቶች ኹኑ ከእስራኤልም ልጆች አንደኛዋ ጭፍራ አመነች ሌላይቱም ጭፍራ ካደች እነዚያን ያመኑትንም በጠላቶቻቸው ላይ አበረታናቸው አሸናፊዎችም ኾኑ› 61.14፡፡ ይህ ጥቅስ እጅግ በጣም ጠቃሚ ጥቅስ ነው ምክንያቱም የኢየሱስን ተከታዮች አላህ እንደረዳቸውና ኢየሱስን ከተቃወሙት አይሁዶች የበለጠ እንዳበረታቸው ይናገራል፡፡ ስለዚህም ቁርአን የሚናገረው አላህ የኢየሱስን ተከታዮች አሸናፊዎች እንዳደረጋቸው ነበር፡፡ እነዚህ ከአይሁዶች የበለጠ የጠነከሩት የኢየሱስ ተከታዮች ታዲያ እነማን ነበሩ? በታሪክ ውስጥ ግልጥ እንደሆነው ሁሉ ይህንን አባባል በትክክል የሚገልጡት ሰዎች እውነተኛ የሆኑት ክርስትያኖች የሆኑትና በኢየሱስ አምላክነት፤ ሞትና ትንሳኤ ያመኑት ብቻ ናቸው፡፡ በሌላ አነጋገር ደግሞ ሙስሊሞች እዚህ ላይ የእግዚአብሔር መልክት እንደተበላሸ እና እውነተኛው ወንጌል እንደተበረዘ እንዲሁም ሙሉ በሙሉ እንደጠፋ አድርገው መናገር እንደማይችሉ ነው፡፡ ምክንያቱም በዚህ ክፍል የሚናገረው የተሸነፉትን ቡድኖች አይደለምና፡፡ በመጀመሪያው መቶ ዓመት የክርስትያን-ሙሊሞች ነበሩ ብለን ብንልም እንኳን ያ ቡድን በማንም ቡድን ላይ የበላይነትን እንዳገኘ የምናየው ምንም ማስረጃ የለንም፡፡ በእርግጥ እነሱ ትልቅ ተቃውሞን ያገኙ ነበር፡፡ በዚያን ዘመን አይሁዶች ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖን ያስከተሉ ክርስትያኖች ብቻ ነበሩ፤ ክርስትናም በአንድ ጊዜ በመላው የሮማን ግዛት ውስጥ ተስፋፍቶ ነበር፡፡ እነዚህም ክርስትያኖች ያምኑ የነበረው አሁንም እውነተኛ ክርስትያኖች የሚያምኑትን መሠረታዊውን የክርስትና እምነት አስተምህሮን ነበር፡፡ ነገር ግን አሁንም ቁርአን የሚናገረው እነዚያን ሰዎች አላህ በኃይል እንዲንቀሳቀሱ እረድቷቸው እንደነበረ ነው፡፡
ታዲያ ክርስትና እንዴት ሊስፋፋና በዓለም ላይ ጠንካራ እንዲሁም ዋና ሃይማኖት ሊሆን ቻለ? ምክንያቱም የተስፋፋው በአላህ ኃይል ነበርና ነው፡፡ ኢየሱስ በመስቀል ላይ ሞተ የሚለውን ክርስትያኖች የሚከተሉትን ትምህርት ማነው የጀመረው? በቁርአን መሠረት፤ እግዚአብሔር የፈጠረው ፈጠራ ነበር፡፡ ክርስትያን ያልሆኑ የታሪክ ጸሐፊዎችም እንኳን የኢየሱስ ሞት ትክክለኛ የሆነ ማስረጃ ያለው የታሪክ ክስተት እንደሆነ ይመሰክራሉ፤ ለምሳሌም ያህል ጆን ዶሚኒክ ክሮሳን የተባለውና እጅግ በጣም ክርስትናን የሚቃወመውና ‹ከኢየሱስ ሰሚናር› የሚባል እንቅስቃሴ ውስጥ ያለው ሰው እንደተናገረው ‹የኢየሱስ መሰቀል ጉዳይ በታሪክ ውስጥ ተፈፀመ ብለን እንደምናምነው ማንኛውም ክስተት እርግጠኛ ነው› በማለት ነው (Jesus: A Revolutionary Biography [San Francisco: HarperCollins, 1991] p. 145). እነዚህ የታሪክ ጸሐፊዎች ይህን ሐሳብ ከየት ነው ያገኙት? እነሱ ያገኙት ከእግዚአብሔር ነው፡፡ ማለትም ብዙ ሰዎችን በኢየሱስ ሞት እንዲያምኑ ካታለላቸው ማለት ነው፡፡ ስለዚህም ዛሬ ለዚህ ማስረጃ የሚሆን እጅግ ብዙ የታሪክ ማህደር አለን፡፡ በአሁኑ ጊዜ በዚች በምድራችን ላይ ወደ ሁለት ቢሊዮን የሚሆኑ እና ክርስትያኖች ነን የሚሉ ሰዎች ሲኖሩ የሚመስለው ይህ እምነት በምድር ላይ ለመኖሩና በእስልምና ላይም ጥላን በማጥላቱ ኃላፊነቱን የሚወስዱትና ለብዙዎች ማሳሳት ተጠያቂ የሚሆኑት ኢየሱስና እግዚአብሔር ናቸው ማለት ነው፣ አይመስልምን!
ስለዚህም፡-
እስልምና እውነት ከሆነ ...
ምንም መናገር እስከማያስፈልግ ድረስ እኔ እንደማስበው የእስልምና አመለካከከት እጅግ በጣም ችግር ያለበት ነው፡፡ ይህም የሚመራን እግዚአብሔር በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን እንዳታለለ እንድናምን ነው፡፡ እንዲያውም የኢየሱስን ተከታዮች ኢየሱስ እንደሞተ እንዲያምኑ ያታለላቸው እግዚአብሔር ነው፡፡ ይህ ደግሞ እግዚአብሔር ሕዝቡን ለማታለል ባያስብና ባያደርገው ኖሮ ሊወገድ የሚችልና የማይሆን ነገር ነበር የሚሆነው፡፡ ነገር ግን ይህ እውነታ ለብዙ ለሌሎች ጥያቄዎች የሚያነሳሳ ነገር ነው የሚሆነው፤ ከእነዚህም ውስጥ፡- ኢየሱስ ሳይሞት እንደሞተ ሰዎች እንዲያምኑ እግዚአብሔር ያደረገው ለምን ነበር?
እግዚአብሔር ኢየሱስን ሳይሞት በደህንነት ወደ ሰማይ ስለወሰደው ይህንን ያደረገው እሱን ከሮማውያን ወይንም ከአይሁዶች ለመጠበቅ እንደነበረ ነው በማለት ሙስሊሞች ሊከራከሩ አይችሉም፡፡ ስለዚህም የኢየሱስ ጠላቶች ኢየሱስን እንደተገደለ እያዩ ወይንም ሞተ በማለት እንዲረኩ ለምን እግዚአብሔር አደረጋቸው? ሌሎችን ሰዎችን ሳያታለል፣ ኢየሱስን እንዲያውም እያዩ ለምን አልወሰደውም ነበር? እነዚያን ሰዎች እግዚአብሔር የሚያታልልበት ምንም ምክንያት የለም፤ አለ ብሎ ለመቀበልም አያስችለንም፡፡ በተለይም እንዲህ ዓይነቱ ማታለል ወዲያውኑ ክርስትና የሚባለውን እምነት ለመመስረት እየመራ ማለት ነው፡፡
ይህ ለሙስሊሞችም ለማንም የሚያስተውል አዕምሮ ላለው ሁሉ ለመዋጥ የሚያስቸግር ኪኒን ነው የሚሆነው፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም እስልምና የሚያስገድደን የክርስትናን አመጣጥ በዚህ መልኩ እንድናየው ነው፡፡ አይገርምም! ይገርማል፡፡
ስለዚህም:-
ሀ. እስልምና እውነት ከሆነ እግዚአብሔር የላካቸውን ነቢያት እንዲታመኑባቸው ሰዎችን ያታልላል ማለት ነው፡፡
ለ. እስልምና እውነት ከሆነ መሲሁ ኢየሱስ በምንም መልኩ ብቁ ያልሆነ ስለነበር በእግዚአብሔር መላክ አልነበረበትም ምክንያቱም በታሪክ ከተነሱት ሰዎች ሁሉ ይልቅ የኢየሱስ ሕይወት ሰዎችን የመራው ወደ ስህተት እምነት ስለሆነ፡፡
ይህ ደግሞ የሚያሳየው ሙስሊሞች እግዚአብሔር ላይ ያላቸው መረዳት ከተለመደው የታሪካዊ መረዳት ጋር አብሮ የማይሄድ መሆኑን ነው፡፡ (ይህም የእስልምናን መረዳትንም ጨምሮ ነው)፡፡ ስለዚህም እስልምና ወጥ የሆነ የሃይማኖት እምነት እንዳልሆነ የሚያሳይ ነገር ነው፡፡ በመሆኑም የእስልምና እምነት - የሚያስብ አዕምሮ ባለው ሰው ሁሉ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት የሌለበት እምነት ነው፡፡ እስልምና ስለ ክርስትና አጀማመር ያለው አመለካከት በጣም ዝቅ ያለ እና ንቀት የተሞላበት ገለጣን የተሞላ ነው፡፡ እስልምና እውነት ከሆነ የክርስትና እምነት መኖርና መስፋፋት በምንም ዓይነት መልኩ ምንም ትርጉም የማይሰጥ ነው ማለት ነው፡፡
ክርስትና እውነት ከሆነ ....
በሌላ መልኩ ክርስትና ስለ እስልምና አነሳስ በቀላሉ ነው የሚዘግበው፡፡ በእርግጥ ክርስትና እውነት ከሆነ የእስልምና አነሳስ እና መስፋፋት ትክክለኛ ስሜትን የሚሰጥ ነው የሚሆነው፡፡ ክርስትና እንደ እስልምና ላሉት ሃይማኖቶች መነሳት ያወረሰው (ያደረገው አስተዋፅዖ) ነገር ወዲያውኑ ግልፅ ካልሆነ የሚከተሉትን የአስተሳሰብ አካሄዶች መመልከት በጣም ያስፈልጋል፡-
ክርስትና እውነት ከሆነ የሚከተሉትም ዓረፍተ ነገሮች ትክክል ናቸው ማለት ነው፡-
1. ሰዎች ወደ እግዚአብሔር መምጣት የሚችሉት በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ብቻ ነው፡፡
2. ሰይጣን በትክክል ሕልውና ያለውና ሰዎች ወደ እግዚአብሔር እንዳይመጡ የሚከላከል አካል ነው፡፡
እነዚህን ዓረፍተ ነገሮች በአዕምሮአችን ይዘን ስለ ሰይጣን ጥቂት ተጨማሪ ነገሮችን የምንመለከት እንደሆነ እስኪ እንይ፡፡ ሰይጣን ሰዎችን ከእግዚአብሔር ለማራቅ የሚፈልግ ከሆነ፣ እንዲሁም ሰዎች ወደ እግዚአብሔር የሚመጡበት መንገድ በክርስቶስ በኩል ብቻ ከሆነ፣ የሰይጣን ዋናው እና ትልቁ የቅድሚያ ሥራ የሚሆነው ምንድነው? የሚለውን መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ የሰይጣን ዋናው ዓላማ የሚሆነው ሰዎችን በተለያዩ ኢ-ሞራላዊ የሕይወት ነገር ላይ እንዲያተኩሩ ማድረግ አይሆንም (ምንም እንኳን እሱ ያንን ማድረጋቸውን ቢፈልገውም ማለት ነው፤ ምክንያቱም ይህ እግዚአብሔር የፈጠረውን ስርዓት የበለጠ ያበላሸዋልና)፡፡ ነገር ግን የሰይጣ ዋናና የቅድሚያ ዓላማ የሚሆነው ሰዎች ከክርስቶስ የሚርቁበትን፣ ክርስቶስን የሚቃወሙበትን መንገድ ማመቻቸትና እውን ማድረግ ነው፡፡ ይህ ክርስቶስን ያለመቀበል መንገድ ብቻ ነው ከእግዚአብሔር ጋር እንዳይቀራረቡና እንዳይታረቁ ሊያደርጋቸው የሚችለው፡፡
ነገር ግን እንዴት ነው ሰዎች ክርስቶስን ሊክዱለትና ላይቀበሉ እንዲችሉ የሚያደርገው? እዚህ ጋ በዓለማችን ላይ እጅግ ብዙ የሚሆኑ ሰዎች ስለ እግዚአብሔር ምንም ግድ የሌላቸው ምንም ደንታ የሌላቸው እንዳሉም ማወቅና መገንዘብ ያስፈልገናል፡፡ ስለዚህም በተቻለው መጠን የተቻለውን ያህል እጅግ ብዙ ሰዎችን ከእግዚአብሔር አርቆ መጠበቅ ስለሆነ ዋናው ዓላማው፣ ሰይጣን ትኩረት የሚያደርገው ሃይማኖተኛ በሆኑ ሰዎች ላይ ነው፡፡ ማለትም በሃይማኖተኛ ሰዎች ላይ በከፍተኛ ደረጃ ስራውን ይሰራል፡፡ ስለዚህም እነዚህን ሃይማኖተኛ የመሰሉ ሰዎችን ከእግዚአብሔር ለማራቅ ደግሞ ሁለት መንገዶች አሉ፡፡
አንደኛ፡- ሁሉም ዓይነት የሃይማኖት ንግግርና ውይይት ምንም ጥቅም የለውም በማለት ለማሳመን ሰይጣን ከፍተኛ ጥረትን ማድረግ አለበት፡፡ (ይህንንም ማድረግ የሚችለው እምነት የሌለው ሴኩላር ማህበረሰብን በማስፋፋት ነው፤ ይህም አሁን በዓለም ላይ እየሆነ እንደምናየው ያለው ነው)፡፡
ሁለተኛ፡- ለእውነት ምትክ የሆነንና እውነት የመሰለን ውሸትን መስጠትና ማቅረብ አለበት፡፡ (ይህም ለደኅንነት አስፈላጊ የሆነውን እምነት ሰዎች እንዲቃወሙና እንዳይቀበሉ በማድረግ ነው)፡፡
ስለዚህም ክርስትና እውነት ከሆነ፤ ሰይጣን እንዲያደርግ የምንጠብቀው ሰዎች የክርስቶስን ሞትና ትንሳኤ እንዳይቀበሉና እንዲክዱ ያነቃቃል ያበረታታልም ብለን ነው፡፡ ይህም እነዚህ ሃይማኖቶች በአንዳንድ ነገር ክርስትናን የሚመስልም (ነገር ግን ጠቃሚ ያልሆነ መመሳሰል) ነገርም እንኳን ቢኖራቸውም ጭምር ነው፡፡ አሁን ነው እንግዲህ ክርስትና እውነት ከሆነ የምንገምተው ነገር ግልፅ የሆነ መልክን እየያዘ የሚመጣው፡፡ ስለዚህም እስልምና ከምንገምተው ግምት ጋር እንዴት እንደሚገጥም ቀጥሎ እንመልከት፡፡
የእስልምና መልክት እንደሚከተለው የሚመስል ነው፡ ‹በእግዚአብሔር እመኑ መልካምንም ነገር አድርጉ፡፡ እነዚህንም በብቃት ካደረጋችሁ ወደ መንግሰተ ሰማይ ትሄዳላችሁ፡፡ ኢየሱስን አትቀበሉ እሱ የእግዚአብሔርን መልክት ለእስራኤል ልጆች ብቻ ያስተላለፈ ታላቅ ነቢይ ብቻ ነበርና፡፡ እንዲሁም ኢየሱስ ከድንግል ነበር የተወለደው እሱም ታላላቅ የነበሩ ብዙ ተዓምራትን ሲያደርግ ነበር ስለዚህም እሱ መሲህ ነበር፡፡ ነገር ግን ምንም ነገርን ብታደርጉ እሱ ለኃጢአታችሁ በመስቀል ላይ እንደሞተ አድርጋችሁ አትመኑ፡፡ እንዲሁም እሱ ከሞት እንደተነሳም አትመኑ፡፡ በእርግጥም እናንተ ልትፈፅሙ ከምትችሉት እጅግ በጣም አስከፊው ኃጢአት አንዱ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው ብላችሁ ማመናችሁ ነው፡፡ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ አይደለምና፡፡› እዚህ ጋ የምናስተውለው ነገር እስልምና ዋና ዋናዎቹን ለደኅንነት የሚያስፈልጉትን የክርስትናን ትምህርቶች የሚቃወም መሆኑን ነው፡፡ ይህንም ሲያደርግ አንዳንዶቹንና ምንም የማይጠቅሙትን በመቀበል ነው (ይህም ለማስመሰል ያህል ብቻ የተደረገ ነው)፡፡ ለምሳሌም ያህል ሙስሊሞች በእግዚአብሔር እንዲያምኑ ታዘዋል፡፡ ሰይጣንም እና መላእክቱ ይህንንም ያምናሉ አይደል?! ሙስሊሞች መልካምን ነገር እንዲያደርጉ ታዘዋል ነገር ግን በዓለም ላይ ያሉ ሃይማኖቶች ሁሉ ይህንን ያደርጋሉ፡፡ ሙስሊሞች ስለ ኢየሱስ አንዳንድ ነገሮችን እንዲያምኑ ይፈቀድላቸዋል (እንደ ነቢይነቱና ከድንግል መወለዱን) ነገር ግን እነዚህ እምነቶች ማንንም ሊያድኑ አይችሉም፡፡ ነገር ግን ለደኅንነት በጣም ጠቃሚ ወደ ሆኑት ነገሮች ላይ ስንመጣ ማለትም - እንደ የኢየሱስ አምላክነት፣ የኢየሱስ በመስቀል ላይ መሞት፣ ስለ ኢየሱስ ትንሳኤው (ከሞት ስለመነሳቱ)፤ እውነቶች ላይ ስንመጣ እስልምናን የምናገኘው እጅግ በጣም አሸባሪ በሆነ ሁኔታ እነዚህን ነገሮች ሲቃወማቸው ነው፡፡
(ማስታዎሻ፡- (እዚህ ጋ ከብዙዎች አስተምሮዎች መካከል በእግዚአብሔር ማመንን ባለመጥቀሴ አንድ ሰው ሊደነቅ ይችል ይሆናል፡፡ በእግዚአብሔር የማመንን እጅግ በጣም አስፈላጊነት መካዴ አይደለም፡፡ ነገር ግን እዚህ ግልፅ ለማድረግ የምፈልገው በአስፈላጊ ዶክትሪንና - አስፈላጊና ብቁ በሚሉት ዶክትሪኖች መካከል ልዩነት ለማድረግ ነው፡፡ በእግዚአብሔር ማመን ለደኅንነት አስፈላጊ ነው ነገር ግን ደኅንነትን ለማስገኘት ብቁ አይደለም፡፡ በአንፃሩ ግን የክርስትያን አስተምህሮ የሆነው በክርስቶስ ጌትነት ለኃጢአተኞች ሞቶ መነሳቱን ማመን አስፈላጊና ለደኅንነትም ብቁ ነው፡፡ ማለትም እነዚህ አስተምህሮዎች ለክርስትያን አስፈላጊና ብቁ እንዲሁም ደኅንነትንም ዋስትና የመስጠት ብቃት ያላቸው ናቸው፡፡ ነገር ግን እስልምና ይህንን አስተምህሮ ነው እጅግ በጣም አምርሮ የሚዋጋው እንዲሁም የሚቃወመው፡፡)
ስለዚህም እስልምናን በትክክል የሚገልፀው መግለጫ የሚሆነው ከዚህ በላይ ያየነውና ሰይጣን የሚያቋቁመው (ወይንም የመሠረተውን) ሃይማኖትን ይመስላል ብለን እንዳልነው ያለውን ነው፡፡ ምክንያቱም ሰዎች ወደ ክርስቶስ እንዳይመጡ መንገድን የሚዘጋና ለደኅንነት ወይንም መንግስተ ሰማይ ለመግባት የሚያስችለውን መንገድ የሚያስክድ ሃይማኖት ስለሆነ ነው፡፡
እዚህም ላይ ክርስትና ስለ እስልምና መነሳት ትንቢት መናገሩን ለማየት የሚያስችል ቀላል መንገድ አለ፡፡ ይህንንም ለመመልከት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉትን አንዳንድ ትንቢቶችን መመልከት እንችላለን፡፡ ለምሳሌም ያህል ጌታ ኢየሱስ ‹ብዙ ሃሰተኛ ነቢያት ይነሳሉ ብዙዎችንም ያስታሉ› ማቴ 24.11 በማለት ተናግሯል፡፡ ጳውሎስም በዚህ ላይ የሚከተለውን ጨምሯል ‹መንፈስ ግን በግልጥ በኋለኞች ዘመናት አንዳንዶች የሚያስቱ መናፍስትንና በውሸተኞች ግብዝነት የተሰጠውን የአጋንንትን ትምህርት እያደመጡ ሃይማኖትን ይክዳሉ ይላል› 1ጢሞቲዎስ 4.1፡፡ እዚህ ላይ ያለው (የሚያስቱ መናፍስት የሚለው ሐረግ ቁርአን አላህ ስለ ኢየሱስ ሞት ሰዎችን እንዲያምኑ ያታለለበትን ማታለል ዓይነት በቁርአን ውስጥ የተገለጠውን ዓይነት ማለት ነው)፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በተደጋጋሚ የሐሰት ነቢያትና አስተማሪዎች እንደሚመጡ ተናግሯል፤ አስጠንቅቋልም ይህም ወንጌልን ለመበረዝና ሰዎችን ከእምነት ለማራቅ ነው፡፡ ነገር ግን በመሐመድ ጊዜ ይህንን ማስጠንቀቂያ ያስተውሉት ጥቂት ሰዎች ብቻ ነበሩ፡፡
የመጨረሻ ሐሳብ
በታሪክ ሁሉ ውስጥ በጣም ብዙ ሰዎች ነቢያት ነን በማለት እየተነሱ ተናግረዋል፡፡ በእርግጥም እጅግ በጣም ብዙዎች የሚሆኑና እራሳቸውን የሾሙ ነቢያት አሉ፡፡ አሁንም ተነስተዋል እንዲሁም ነገና ተነገ ወዲያም ብዙዎች ይነሳሉ፡፡ ምናልባት በአንድ ወቅት ወደ ፊት ነቢይ ነኝ የሚል ቢነሳ፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ አዲስን መገለጥ አግኝቻለሁ ብሎ የሚል ሰው ቢነሳ፤ ማን ይቀበለዋል? የሚልን ጥያቄ እንጠይቅ፡፡
(እስልምናም እንኳን እራሱን ነቢይ ያደረገ አዲስ ነቢይ አለው፡፡ ይህም በጣም የታወቀው ሚርዛም ጉላም አህመድ ነው፡፡ እሱም ያወጀው ነገር በ19ኛው መቶ ዓመት መጨረሻ ላይ እራሱን ነቢይ ነኝ በማለት ነው፡፡ እንዲያውም እሱ ያወጀው የኢየሱስ ሁለተኛ ምጣት እኔ ነኝ በማለት ነበር፡፡ ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ተከትለውታል፡፡ ነገር ግን ብዙዎቹ ሙስሊሞች እነዚህን ‹አህመዲያዎች› ብለው የሚጠሯቸውን የሚመለከቷቸው እንደ ሐሰት አስተማሪዎች ነው፡፡ እነዚህ አህመዲያዎች እስላሞች ነን በማለት እራሳቸውን ቢጠሩም እንኳን ወደ መካ - ሃጂ - እንዳያደርጉ ተክልክለዋል፡፡ የአሕመዲያን እንቅስቃሴ ልዩ የሚያደርገውም እስልምና ተበክሏል በሚል አስተምህሮው ጭምር ነው፡፡ ይህም ልክ መሐመድ (ሙስሊሞች) ክርስትና ተበክሏል በማለት እንደሚናገሩት ማለት ነው፡፡ ስለዚህም አህመዲያዎች የሚያምኑት እግዚአብሔር በእስልምና የተፈፀመውን ስህተት የሚያስተካከል እና የትክክለኛውን የእግዚአብሔርን እምነት የሚያመጣውን ሌላ ነቢይን እንደላከ ነው፡፡ ሙስሊሞች ይህን አይቀበሉትም ምክንያቱም እስልምና እንደተበከለ አያምኑምና፡፡ ስለዚህም እነሱ የደመደሙት ሚርዛም ጉላም አህመድ የሐሰት ነቢይ መሆን አለበት በማለት ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ደግሞ ክርስትናም የተከተለው እና መሐመድን አልቀበልም ያለበት ተመሳሳይ ምክንያት ነው፡፡ ስለዚህም ክርስትና እንደተበከለ መረጃ ስለሌለ እኛ ይህንን የተበክሏል ጥያቄ አናምንም አንቀበልምም ስለዚህም መሐመድ የሐሰት ነቢይ መሆን አለበት፡፡)
እስላሞችም ክርስትያኖችም ሁለቱም እንዲህ የሚለውን ሰው አይቀበሉትም፡፡ ነገር ግን ይህ አዲስ ነቢይ ‹ወንድሞች በመሐመድ ትምህርት እምናችኋል ነገር ግን እኔ እዚህ ጋ ያለሁት እስልምና ሰዎችን ለማታለል በእግዚአብሔር የተጀመረ ሃይማኖት ነው፡፡ በአረቢያ ውስጥ ያሉት አረቦች እጅግ በጣም አሳዛኝን ነገር ያደርጋሉ ለምሳሌም ሴት ልጆቻቸውን መግደልን፣ እንዲሁም በመቶ የሚቆጠሩ ሴቶችን ማግባትን የመሳሰሉትን ሁሉ ያደርጋሉ፡፡ እግዚአብሔር እነሱን ለማጥፋት ወስኗል እነሱንም በኃጢአታቸው እንዲቀጥሉ በማድረግ እና እናንተንም ደግሞ ሁላችሁንም እውነት ያልሆነን ነገር እንድታምኑ በማድረግ ነው፡፡ ነገር ግን እኔ እዚህ ያለሁት እውነትን ልነግራችሁ ነው፤ እኔ የእግዚአብሔር ታላቅ ነቢይ ነኝ እኔም የተላክሁት እናንተን ከክፉ ለማዳን ነው፡፡› በማለት ቢናገር እስላሞች ይቀበሉታልን? በጣም በእርግጠኛነት ሊቀበሉት አይችሉም፡፡ ነገር ግን ለምንድነው ሙስሊሞች ይህንን አዲስ ነቢይ የማይቀበሉት? ይህንን መቀበል የለባቸውም፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር እያወቀ ወይንም ሆነ ብሎ እጅግ በጣም ብዙ ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎችን በምንም ምክንያት አያታልልምና፡፡ ነገር ግን የኢየሱስ ክርስቶስን መሞት በተመለከተ ሙስሊሞች በሙሉ በትክክል ያመኑት እንዲህ ዓይነቱን ጭፍን ነገር ነው፡፡ ስለዚህም ሙስሊሞች ሰዎችን በሚያታልል አላህ የሚያምኑ ከሆነ፣ የአታላዩንም አላህ ነቢይ ነኝ የሚለውንም ሰው የሚከተሉት ከሆነ፣ እነሱ እውነት ያላቸውና እውነትን ያመኑ ለመሆናቸው፣ እንዴት እርግጠኞች መሆን ይችላሉ? መልሱን ሊያስቡበት ይገባቸዋል ምክንያቱም የዚህ ጥያቄ መልስ የዘላለምን ሕይወትን የማግኘትና ያለማግኘት ጉዳይን ይወስነዋልና፡፡
ሙስሊሞች እግዚአብሔርን እንደሚፈሩና ነቢያትንም እንደሚያከብሩ በከፍተኛ ትምክህት ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን በቅርብ ምርመራ ሲታዩ - እስልምና እምነት ግልጥ የሚያደርገው እግዚአብሔርን በሃይማኖት ማታለል ወደር የሌለው አታላይ አድርጎ ሲከሰው (ሲወነጅለው) ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለጥቂት ጊዜ ቆም እንድንልና እንድናስብ ያደርገናል፡፡ አንድ ሃይማኖት እግዚአብሔርን አመልካለሁ፤ አከብራለሁ እያለ የሚናገር ሆኖ እያለ፤ ለምንድነው እግዚአብሔር የሐሰት ሃይማኖትን ጀምሯል በማለት ስለ እግዚአብሔር የሚናገረው? ኢየሱስ ክርስቶስን እናከብራለን ብለው የሚናገሩ ሰዎች እጅግ ያልተሳካለት ነቢይ እንደሆነ ስለምን ይናገራሉ? እንግዲህ እስልምና የሚመስለው ሊታመን በማይቻል ሁኔታ ክርስትናን ለማጥፋት ቆርጦ የተነሳ ሃይማኖት እንደሆነ ነው፡፡ እንዲሁም ደግሞ እራሱንም ለማጥፋት እንኳን ምንም ቅርም የማይለውም ነው፡፡ በሌላ አነጋገር እስልምና የኢየሱስን ሞትና ትንሳኤ ለመግለጥ ወይንም ለማስረዳት የሚችለው እግዚአብሔርን አታላይ ነው በማለት (እግዚአብሔርን አታላይ በማድረግ) ብቻ ነው፡፡ ይህ ደግሞ እስላሞች ለእግዚአብሔር ያላቸውን አመለካከት ሙሉ በሙሉ ያበላሸዋል፡፡ ይህ ውጥረት ደግሞ እውነተኛ መልስን ሊያገኝ የሚችለው ክርስትና እውነት ከሆነ ብቻ ነው፤ ክርስትና ደግሞ እውነት ነው፡፡
የትርጉም ምንጭ: Deceptive God, Incompetent Messiah: What Islam Really Teaches About Allah and Jesus by David Wood
ለእስልምና መልስ አማርኛ ዋናው ገጽ