የቁርዓኑ አላህ የመጽሐፍ ቅዱሱ እግዚአብሔር ነውን?

Sam Shamoun

[ክፍል አንድ[ክፍል ሁለት] ክፍል ሦስት [ክፍል አራት]

በአዘጋጁ የተቀናበረ

አላህ ሥላሴ አይደለም

የሙስሊሞች አላህ የመጽሐፍ ቅዱሱ እግዚአብሔር ላለመሆኑ ሌላው ማረጋገጫ አላህ ሥላሴ አለመሆኑ ነገር ግን የመጽሐፍ ቅዱሱ እግዚአብሔር ሥላሴ መሆኑ ናቸው፡፡ በእግዚአብሔር ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ዘዳግም 6.4 እና ገላትያ 3.20 አንድ አምላክ ብቻ እንዳለ የጌታ ቃል ይናገራል፡፡

ነገር ግን በተመሳሳይ መንገድ ይኸው አንዱ እግዚአብሔር ለዘላለም የኖረው በሦስት እኩል በሆኑ አካልነት ነው፡፡ እነዚህም፡-  

እግዚአብሔር አብ፡- ‹የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ጴጥሮስ፥ እግዚአብሔር አብ አስቀድሞ እንዳወቃቸው በመንፈስም እንደሚቀደሱ፥ ይታዘዙና በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ይረጩ ዘንድ ለተመረጡት በጳንጦስና በገላትያ በቀጰዶቅያም በእስያም በቢታንያም ለተበተኑ መጻተኞች፤ ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ።›1ጴጥሮስ 1.2፡፡

እግዚአብሔር ወልድ፡- ‹ይህም ጸጋ፥ ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊን ምኞት ክደን፥ የተባረከውን ተስፋችንን እርሱም የታላቁን የአምላካችንንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ እየጠበቅን፥ ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር ያስተምረናል፤› ቲቶ 2.13፡፡

እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ፡- ‹ጴጥሮስ፤ ሐናንያ ሆይ፥ መንፈስ ቅዱስን ታታልልና ከመሬቱ ሽያጭ ታስቀር ዘንድ ሰይጣን በልብህ ስለ ምን ሞላ? ሳትሸጠው የአንተ አልነበረምን? ከሸጥኸውስ በኋላ በሥልጣንህ አልነበረምን? ይህን ነገር ስለ ምን በልብህ አሰብህ? እግዚአብሔርን እንጂ ሰውን አልዋሸህም አለው።› ሐዋርያት 5.3-4፡፡

ሥላሴ (ሦስት በአንድ):- መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሥላሴ በማቴዎስ 28.19፡፡ ‹እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።› በማለት ይናገራል፡፡ ይሁን አንጂ የቁርዓኑ አላህ ከዚህ በላይ ከተጠቀሱት ከሦስቱም አካላት አንዱንም አይደለም፡፡ ለምሳሌም ያህል ‹በል፡- እርሱ አላህ አንድ ነው፡፡ አላህ (የሁሉ) መጠጊያ ነው፡፡ አልወለደም አልተወለደምም፡፡ ለርሱም አንድም ብጤ የለውም› በማለት ቁርዓን 112 ይናገራል፡፡ አላህ አልወለደም ማለትም በመንፈሳዊም ሆነ በስጋዊ መንገድ ልጅ የለውም፡፡ ስለዚህም አላህ አባት ሊሆን በፍፁም አይችልም፡፡ እንዲሁም እራሱንም ልጅ እንዲደረግ አይፈቅድም እንዲሁም እግዚአብሔር ወልድ ለእኛ ከኃጢአት መዳን እንድንችል፤ የሰውን ተፈጥሮ እንደወሰደው ዓይነት አላህ የሰውን ተፈጥሮ ለመውሰድ አይችልም፡፡ በመጨረሻም በእስልምና አስተምህሮ መሠረት መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር አይደለም፤ እሱንም የሚጠቅሱት መልአኩ ገብርኤል በማለት ነው፡፡ እነዚህም እውነቶች የሚያመለክቱት ክርስትያኖች በሚያመልኩት እግዚአብሔርና በአላህ መካከል ትልቅ የተፈጥሮ ልዩነት የመኖሩን እውነታ እንዲሁም አንድ አምላክ አለመሆናቸውንም ነው፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በ1 ዮሐንስ 2.22-23 ላይ የሚከተለውን እናነባለን፤- ‹ክርስቶስ አይደለም ብሎ ኢየሱስን ከሚክድ በቀር ውሸተኛው ማን ነው? አብንና ወልድን የሚክድ ይህ የክርስቶስ ተቃዋሚ ነው። ወልድን የሚክድ ሁሉ አብ እንኳ የለውም፤ በወልድ የሚታመን አብ ደግሞ አለው።› ስለዚህም ለእውነተኛ ክርስትያኖች አላህ የመጽሐፍ ቅዱሱ እግዚአብሔር አይደለም፡፡ ምክንያቱም በመንፈስ ቅዱስ ምሪት የተጻፈው የአዲስ ኪዳን ትምህርት የሚያሳየው አብንና ወልድን አምላክ አይደለም ብሎ የሚክድ ማንም ቢኖር ሐሰተኛው ክርስቶስ ነው በማለት ነውና፡፡

ይህንን ክፍል ከማጠናቀቃችን በፊት እዚህ ጋ ሙስሊሞች ብዙውን ጊዜ ስለሚያቀርቡት ክስ መመልከት በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ እነሱም ዘፀዓት 31.17 ላይ ያለውን ቃል ‹እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን በስድስት ቀን ስለ ፈጠረ፥ በሰባተኛውም ቀን ከሥራው ስላረፈና ስለ ተነፈሰ፥ በእኔና በእስራኤል ልጆች ዘንድ የዘላለም ምልክት ነው።› ይጠቅሱና እግዚአብሔር በፍፁም ስለማይደክምና እረፍትም ስለማያስፈልገው ይህ ገለፃ ለእግዚአብሔር የሚስማማ አይደለም ይላሉ፡፡ ለዚህም የምንሰጠው መልስ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እግዚአብሔር ሲናገር ከሰው ጋር ያለውን ግንኙነት እና መንፈሳዊ የሆኑት ስራዎቹ በሰዎች ዘንድ መረዳትን እንዲያገኙ በሰዋዊ ቃላት (አንትሮፖ-ሞርፊዝም) መግለጫ እንደሚጠቀም ነው፡፡ የዚህም ዓረፍተ ነገር ዓውድ የሚያስረዳው ሰንበትን የማክበር አስፈላጊነትንና በእግዚአብሔርና በሕዝቡም መካከል እንደ ምልክት የሆነ ነገር መሆኑን ነው ስለዚህም እንዲህ ዓይነቱ አምላክ ከቃል ኪዳን ሕዝቡ ጋር ግንኙነታዊ እና ሰው ሊገባው በሚችል አነጋገር እራሱን የሚገልጥ መሆኑን ነው፡፡

እንዲሁም ልክ እግዚአብሔር በሰባተኛው ቀን እንዳረፈው እስራኤላውያን፤ በተለይ የተመረጡ ሕዝቦቹ ከመሆናቸው የተነሳ እሱ ያደረገውንና ያዘዘውን ትዕዛዝ በሙሉ እንዲፈፅሙ የሚያሳስብ ነበር፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ሰንበት የሚለው ቃል በሒብሩ ቋንቋ ሻባት የሚል ሲሆን፡፡ ትርጉሙም የሚያሳየው ማቆም፣ መጨረስ፣ ማረፍ፣ መፈፀም ማለትንም ነው፡፡ ተነፈሰ የሚለውም ቃል እግዚአብሔር እንደደከመ ምንም የሚያሳየው ጥቆማ የለም፡፡ ነገር ግን የሚጠቁመው እግዚአብሔር በፍጥረት የፈጠራ ክንዋኔው መልካምነት እንደተደሰተና እንደረካ ነው እነዚህም ቃላት ከድካም እንደማረፍን ነው የሚያመለክቱት የሚለው ሐሳብ የማንቀበለው ስለ ፍጥረት ከተገለጠውም ከዘፍጥረት 1.31 ላይ ካለው ሐሳብ ጋር ስለማይሄድም ነው፡፡ እግዚአብሔር በፍፁም አይደከምም ይህም የቅዱስ ቃሉ ወጥ አስተምህሮ ነው፡፡ ‹እግርህን ለመናወጥ አይሰጠውም፤ የሚጠብቅህም አይተኛም። እነሆ፥ እስራኤልን የሚጠብቅ አይተኛም አያንቀላፋምም።› መዝሙር 121.3-4፡፡ እንዲሁም ደግሞ በኢሳያስ 40.28 ላይ የሚከተለውን እናነባለን፡- ‹አላወቅህምን? አልሰማህምን? እግዚአብሔር የዘላለም አምላክ፥ የምድርም ዳርቻ ፈጣሪ ነው፤ አይደክምም፥ አይታክትም፥ ማስተዋሉም አይመረመርም፡፡› በመሆኑም በዘፀዓት 31.17 ላይ ያለውን ከዓውዱ ውስጥ አውጥቶ በመጽሐፍ ቅዱስ አጠቃላይ ትምህርት ላይ እንደ ተቃራኒ ማረጋገጫ ለመጠቀም መሞከር ዝቅተኛ አቀራረብና ያለ አዋቂነትን የሚያሳይ ነው ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ በግልጥ እንደሚያሳየው እግዚአብሔር ወሰንና ልክ የሌለው ነገር ግን ከፍተኛ ኃይልና ችሎታ ያለው አምላክ ነውና፡፡

እንግዲህ በቁርአን ላይ አላህ ከተገለጠበት ገለጣ በመጠኑ ያየነው እውነታ የሚያመለክተን፤ እሱ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተገለጠውና በአብርሃም ይመለክ የነበረውን እግዚአብሔርን በምንም መልኩ ሊሆን እንደማይችል ነው፡፡ በቁርአኑ አላህና በመጽሐፍ ቅዱሱ እግዚአብሔር ተፈጥሮና ባህርይ መካከል ያለው ልዩነት ሊታረቅና ሊታለፍ የማይችል እጅግ በጣም ብዙ ነው፡፡ ስለዚህም አላህ የመጽሐፍ ቅዱሱ እግዚአብሔር ሊሆን በፍፀም አይችልም፡፡

ይህንን በአዕምሮአችን ይዘን በሁለቱ መካከል ያለውን ሌላ ትልቅ ልዩነት የግድ መመልከት አለብን፡- የመጽሐፍ ቅዱሱ እግዚአብሔር ለሚያምኑቱ የደኅንነትን እርግጠኝነት ይሰጣል የቁርአኑ አላህ ግን ይህንን በጭራሽ ሲያደርገው አይታይም፡፡ አላህ መንግስተ ሰማይ የመግባትን እርግጠኝነትን በፍፁም አይሰጥም፡፡ የመጽሐፍ ቅዱሱ እግዚአብሔር ግን በሚከተሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች የደኅንነት እርግጠኝነትን እንደሚሰጥ ግልፅ ነው፡- ‹በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።› ዮሐንስ 3.16፡፡ ‹እውነት፤ እውነት እላችኋለሁ፥ ቃሌን የሚሰማ የላከኝንም የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፥ ከሞትም ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም።› ዮሐንስ 5.24፡፡ ‹ዓለምን ላድን እንጂ በዓለም ልፈርድ አልመጣሁምና ቃሌን ሰምቶ የማይጠብቀው ቢኖር የምፈርድበት እኔ አይደለሁም።› ዮሐንስ 12.47፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጥ እንደሚያስተምረው ከሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ የዘላለምን ሕይወት ዋስትና እስካልሰጠ ድረስ ለሰው ልጅ ምንም ሌላ የመዳኛ መንገድ እንደሌለው ነው፡፡ ይህን ዓይነቱን ተስፋና ማረጋገጫ ደግሞ ለተከታዮቹ የሚሰጥ መሆኑን ቁርአን በምንም መንገድ ወይንም ቃል የማይናገረው ነገር ነው፡፡ ማለትም የቁርአን አምላክ አላህ የሚሰጠው ምንም ዓይነት የደኅንነት እርግጠኝነት ቃል ኪዳን የለም፡፡ የመጽሐፍ ቅዱሱ እግዚአብሔር ግን ‹ኢየሱስም። እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም።› ዮሐንስ 14.6፡፡ ደግሞም ‹መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና።› ሐዋርያት 4.12 በማለት ይናገራል፡፡

በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ግልጥ እንደሆነው ደኅንነትን ክርስቶስ ብቻ የሚያስገኘውና የሚሰጠው ለመሆኑ የተነገረበት ምክንያት እሱ ብቻ ለኃጢአት ቅጣት ፍርድ የሆነውን የዘላለምን ሞት ዋጋ የከፈለው በመሆኑ ነው፡፡ በመስቀል ላይ በመሞቱ ክርስቶስ በኃጢተኞች ምትክ በመሆን በእግዚአብሔር ዘንድ ብቸኛ ተቀባይነት ያለውን መስዋዕትነት አቀረበ፡፡ ‹በኢየሱስ ክርስቶስም በሆነው ቤዛነት በኩል እንዲያው በጸጋው ይጸድቃሉ። እርሱንም እግዚአብሔር በእምነት የሚገኝ በደሙም የሆነ ማስተስሪያ አድርጎ አቆመው፤ ይህም በፊት የተደረገውን ኃጢአት በእግዚአብሔር ችሎታ ስለ መተው ጽድቁን ያሳይ ዘንድ ነው፥› ሮሜ 3.24-25፡፡ ‹የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፤ የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የዘላለም ሕይወት ነው።› ሮሜ 6.23፡፡

ስለዚህም ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ እግዚአብሔር ልጅ እና ብቸኛ አዳኝ አድርጎ በማመን ወደ እርሱ በመምጣትና ኃጢአትንም በመናዘዝ የዘላለምን ሕይወት ዋስትና ማግኘት የሚወሰነው ይህንን ጽሑፍ በሚያነቡት ሙስሊሞች ልብ ውስጥ ነው፡፡ እነሱም አላህን በማምለክ በመቀጠል ቁርአን እንደሚያዘው ያለምንም የዘላለም የሕይወት ተስፋ፣ ያለምንም የኃጢአት ይቅርታ እውቀትና መረዳት፣ ከኃጢአት ይቅርታ የሚገኘውን ደስታ ሳያዩ መኖርን መምረጥ ነው፡፡ ምርጫው የሚተወው ለሚያነበው ለሙስሊም አንባቢ ነው፡፡

የአዘጋጁ ማሳሰቢያ፡-

አንባቢ ሆይ! ከዚህ በላይ ያሉትን እውነተኛ ንፅፅሮች በሚገባ አይተሃል፡፡ በእርሱ ለሚታኑት አማኞቹ እግዚአብሔር መንግስተ ሰማይ ገብተው ከእርሱ ጋር ለዘላለም እንደሚኖሩ የእርግጠኝትን ቃል ኪዳን ገብቷል፡፡ ስለዚህም ይህንን የተስፋ ቃል ክርስትያኖች በማመናቸው መንግስተ ሰማይ መግባታቸውን እርግጠኞች ናቸው፡፡ አንባቢ ሆይ አንተስ? የኃጢአትህን ይቅርታ ሳታገኝ ያለምንም ተስፋ ለምን ትኖራለህ? ወደ እርሱ ወደ ጌታ ኢየሱስ ብትመጣና ኃጢአትህን ተናዘህ በእሱ የመስቀል መስዋዕትነት ለሚያምኑት የኃጢአት የዘላለም ቅጣት እንደተወሰደ ብታምን ዛሬውኑ የኃጢአት ይቅርታ እርግጠኝነትና የዘላለም ሕይወትን ደስታ ታገኛለህ ና ወደ ኢየሱስ አትዘግይ ጌታ እግዚአብሔር እንዲረዳህ ፀሎታችን ነው፡፡

ወደ ክፍል አራት ይቀጥሉ::

 

የትርጉም ምንጭ: IS ALLAH THE GOD OF BIBLE?

 ለእስልምና መልስ አማርኛ  ዋናው ገጽ