አላህ የመጽሐፍ ቅዱሱ እግዚአብሔር ነውን?

አጠቃላይ እይታ

ትርጉምና ቅንበር በአዘጋጁ  

በእስልምና የዜና ቡድን ጽሑፍ ላይ አንድ ሰው እንደሚከተለው ጽፎ ነበር፡- ‹... በቁርአን ላይ ያሉ አንቀፆች ከተዋቀሩበት አወቃቀር ግልጥ እንደሆነው እግዚአብሔር ለነቢዩ መሐመድ እራሱን ይገልጥ የነበረው፤ ወይንም መሐመድ እራሱን ያይ የነበረው ለቀደሙት ነቢያት የተገለጠውን እግዚአብሔር እየተገለጠለት እንደሆነ በመቁጠር ነበር፡፡ በመሆኑም የቁርአኑ አላህ በትክክል የብሉይ ኪዳኑ እና የአዲስ ኪዳኑ እግዚአብሔር ነው፡፡ አሁን በእርግጥ እናንተ አንድን የንባብ ክፍል ወይንም ሌላውን ሐሰት ነው ብላችሁ የምታስቡ ከሆነ የተጠቀሱት ሁለት የተለያዩ አማልክት ናቸው ማለት ነው፡፡ ማለትም አንዱ ትክክል አንዱ ደግሞ የውሸት ናቸው፡፡ ነገር ግን ቅዱስ ቁርአን በጽሑፉ በቀጥታ የተያያዘው (ሰዎችንና ክስተቶችን በመጥቀሱ) ከአዲስ ኪዳንና ከብሉይ ኪዳን ጋር ነው›

ቁርአን ከእግዚአብሔርም ባይሆን እንኳን እኔ ከእነዚህ ጸሐፊዎች ከዚህ ሌላ ምንም ነገርን አልጠብቅም፡፡ ይህንን ግልጥ ለማድረግ የሚከተለውን ማብራሪያ ልስጣችሁ፡-

እንበልና እናንተ እጅግ በጣም ጠቃሚ የሆነ ሰው (የአሜሪካ ፕሬዜዳንት ወይንም ትልቅ ሰው ነው ብላችሁ የምታስቡትን ማንንም ሰው) ጋር ተደረጉ የተባሉ ሁለት ቃለ መጠይቆችን በሁለት የተለያዩ ጋዜጦች ላይ አነበባችሁ፡፡

ሁለቱንም በጣም በጥንቃቄ ስታነቡ እጅግ በጣም የሚቃረኑ ሆነው ታገኟቸዋላችሁ ስለዚህም እነዚህ የተቃረኑ ዓረፍተ ነገሮች ከአንድ ምንጭ ስለመምጣታቸው እና ስለአለመምጣታቸው ታስባላችሁ፡፡ ነገር ግን ሁለቱም ከአሜሪካው ፕሬዜዳንት ጋር በኋይት ሃውስ የተደረጉ መሆናቸውን ይናገራሉ እናም የሚመስለው ፕሬዜዳንቱ በቀጥታ የተናገረውን ነገር እንደያዙ ነው፡፡ ነገር ግን ሁለቱንም አንድ ላይ ስታዩአቸው ወጥ የሆነ ትርጉምን አይሰጡም፤ ማለትም የተቃረኑ ናቸው፡፡ ስለዚህም ትንሽ ምርምር አደረጋችሁና አንደኛው ጋዜጠኛ በትክክል ቃለ መጠይቅ እንዳደረገ፤ ሁለተኛው ጋዜጠኛ ግን ከፕሬዜዳንቱ ጋር ቃለ መጠይቅ ማድረግ እንዳልተፈቀደለት አረጋገጣችሁ፡፡ ይሁን እንጂ በአንድ በሆነ ምክንያት (ምናልባትም ከጋዜጣው አዘጋጆች ግፊት አለበለዚያም ከስራ እንደሚባረር ወይንም በሌላ ምክንያት ተገዶ ይህንን ቃለ መጠይቅ ጋዜጠኛው እራሱ ጽፎታል)፡፡ ይህንን ቃለ መጠይቅ ፈልጎታል እናም ልክ ፕሬዜዳንቱን ቃለ መጠይቅ እንዳደረገ በማስመሰል ይህንን እራሱ ፈጥሮ ያዘጋጀዋል፡፡ ነገር ግን በእርግጥ ልክ ትክክል እና እውነትም ቃለ መጠይቅ እንዳደረገ አድርጎ ነው ያዘጋጀው፡፡ ፕሬዜዳንቱም የቀደመውን ስኬቶቹን ወደ ኋላ መለስ በማለት ጠቅሷቸዋል፤ ቀደም ሲል ያደረጋቸውን ቃለ መጠይቆችና የጠበቃቸውን ቃል ኪዳኖች ወ.ዘ.ተ ልክ እውነተኛ ቃለ መጠይቅ ሊይዝ እንደሚችለው ተደርገው ቀርበዋል፡፡

ቃለ መጠይቁ በሙያ በጣም የተዋጣለት ሆኖ ከመሠራቱ የተነሳ እውነተኛ ቃለ መጠይቅ ባይኖር ኖሮ ማንም ይህ አስመሳይ ነው ብሎ ሊጠረጥር አይችልም፡፡ ስለዚህም አሁን እነዚህ በጣም የማይጣጣሙ ቃለመጠይቆች አሉ፤ ይሁን እንጂ ሁለቱም እውነት ሊሆኑ አይችሉም፤ በምንም ዓይነት፡፡ ትክክለኛውም ሆነ ሐሰተኛው የጻፉት ስለአንድ ፕሬዜዳንት ነው፡፡ ልዩነቱ ርዕሱ ላይ አይደለም እንዲሁም የቃለመጠይቁ የምንጭም ጥያቄ ላይ አይደለም ልዩነቱ ያለው አንዱ በፕሬዜዳንቱ የታወቀ ሌላው ደግሞ በፕሬዜዳንቱ ያልታወቀ በመሆኑ ላይ ነው፡፡ አንዱ ትክክለኛ ሌላው የፈጠራ በመሆኑ ላይ ነው፡፡

ቁርአንም የሚያወራው ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ተመሳሳይ ስለሆነ እግዚአብሔር ነው፡፡ እናም ይህንን እግዚአብሔርን ከዚህ በፊት መገለጦችን ሰጥቶ የሚያውቅ ከሆነ ሊል የሚችለውን ነገር ለማያያዝ ከፍተኛ ጥረትን አድርጓል፡፡ በእርግጥ ሁለቱም መጽሐፍት የሚናገሩት ስለ ተመሳሳይ እግዚአብሔር ነው ልንል እንችላለን፤ ነገር ግን እዚህ ላይ የሚመጣው ጥያቄ በእርግጥ እነሱ ከአንድ ምንጭ ነው ወይ የመጡት የሚለው ነው፡፡ እነሱ ሁለቱም የሚናገሩለት እግዚአብሔር በእርግጥ የሁለቱም መጽሐፍት ምንጭ ነውን?

ደህና ቁርአንና መጽሐፍ ቅዱስ በብዙ ነገሮቻቸው በጣም ይመሳሰላሉ፣ ልክ ከፕሬዜዳንቱ ጋር ቃለ መጠይቅን እንዳያደርግ እንደተከለከው ጋዜጠኛ ከቀደሙ ነገሮች በማውጣጣት ከምርምር ስራዎች በመነሳት ወይንም ከጥሩ ስሜት ነገሮችን መልካም እና ማራኪ በራሱ ፈጠራ እውነት አስመስሎ እንዳዘጋጀው ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ያ ሁሉ ጥረት እውነተኛ ቃለ መጠይቅ ሊያስደርገው አልቻለም፡፡

ቁርአን የሚናገርለት እግዚአብሔር ከክርስትያኖች እግዚአብሔር ጋር አንድ ዓይነት ነው፡፡ ሙስሊሞችም ይህንን እና ብቻውን ፈጣሪ የሆነውን አምላክ ነው የሚያመልኩት ብለን ስናስብ እዚህ ላይ ጥያቄ የሚሆነው ነገር ሙስሊሞችና ክርስትያኖች አንድ ዓይነት አምላክ አላቸው ወይንስ የላቸውም አይደለም (ምክንያቱም አንድ ብቻ ፈጣሪ ነውና ያለው) እዚህ ጋ ጥያቄው እነሱ ያላቸው መጽሐፍ ከዚህ አምላክ ነው የመጣው ወይንስ አይደለም የሚለው ነው፡፡ ቁርአን ስለ እግዚአብሔር ይናገራል ነገር ግን እሱ እራሱ የመጣው ከእግዚአብሔር ነው ወይ?

ርዕሱ አንድ ዓይነት ነው ነገር ግን ምንጩ አንድ ነውን? በመጽሐፍ ቅዱሱ እግዚአብሔርና በቁርአኑ አላህ መካከል ያሉት እጅግ በጣም ብዙ የሆኑትና መፍትሄ የማይገኝላቸው ቅራኔዎች ይህንን ሐሳብ ይክዱታል፡፡ አሁን ያ ጋዜጠኛ ምንም ስህተትን (ማጭበርበርን) የሰራ አይመስልም፡፡ እስቲ የጋዜጠኛውንም ታሪክ ትንሽ (በመጠኑ) ልቀይረው! ይህም ነገሩን የበለጠ (የተሻለ ሊገልጠው) ይችላል ብዬ እንደማስበው ነው፡፡ እንበልና የጋዜጣው አዘጋጅ ከፕሬዜዳንቱ ጋር ለመገናኘት ፈልጓል፤ ነገር ግን የፕሬዜዳንቱ አማካሪ ነኝ የሚልን ሰው አግኝቷል ስለዚህም እንደሚከተለው፡- ‹ፕሬዜዳንቱ በአሁኑ ጊዜ አይገኝም ነገር ግን እኔ የምትፈልገውን መረጃ እንድሰጥህ ስልጣን ተሰጥቶኛል› ብሎታል፡፡ ስለዚህም ይህ ጋዜጠኛ ባዶ እጁን ባለመመለሱ እጅግ በጣም ደስተኛ በመሆን ይህንን የፕሬዜዳንቱን አማካሪ ቃለ መጠይቅ አድርጎለታል እሱም እጅግ በጣም ብዙ መረጃዎችን ለመስጠት በጣም ደስተኛ ነበር ይህም ሳይጠይቅም እንኳን ሁሉ ጭምር ነበር፡፡

ሪፖርተሩም በቅንነት ያመነውና የተገነዘበው የፕሬዜዳንቱን እጅግ በጣም የታመነ ተወካይን ድምፅ በወቅቱ እንዳገኘ አድርጎ ነበር፡፡ በኋላ ቆይቶ ግልፅ እንደሚሆነው ችግሩ የፕሬዜዳንቱ የቅርብ አማካሪ ነኝ በማለት ቃለ መጠይቁን የሰጠው ሰው የውሸት ነበረ፡፡ ጋዜጠኛው የጻፋቸው ነገሮች በሙሉ በራሱ በዚያ ውሸታም የተቀነባበሩ ነበሩ፡፡ ጋዜጠኛው እውነተኛ ነበር፤ ምንጩ ግን የተሳሳተ ነበር፡፡ ከውሸቱ ምንጭ እንደ እውነት የተወሰዱት ነገሮች ሙሉ በሙሉ እውነት እንደሆኑ የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች ነበሩባቸው፡፡ የውሸቱ ምንጭ በፍፁም የማይቻሉ ነገሮችን ጠቅሶ ቢሆን ኖሮ ወዲያውኑ ይነቃበት ነበርና፡፡

እንግዲህ አሁን እዚህ ጋ የሚመጣው ዋና ጥያቄ፡- ቁርአን ከእግዚአብሔር ነውን? የሚለው ነው፡፡ ወይንም እኩል ጥያቄ የሚሆነው መሐመድ በአንዱና በእውነተኛው ሕያው እግዚአብሔር የተላከ ነቢይ ነውን? የሚሉት ናቸው፡፡

በዚህ ቦታ ላይ እንደሚከተለው ያለውን ጥያቄ ‹ከእግዚአብሔር ካልሆነ ከየት ሊሆን ይችላል?› የሚለውን እንኳን እዚህ ጋ አላመጣሁም፡፡ ይህም ለእኔ በጣም የሚያሳስበኝ ጥያቄ አይደለም፡፡ ቁርአን ከእግዚአብሔር አለመሆኑን ካረጋገጥሁ ታዲያ በምን ኃይልና እንዴት መጣ እንዲሁም ኖረ? ስለሚለው ብዙም አልጨነቅም፡፡ ከሌሎች ሰዋዊ መረጃ ነውን? ከመሐመድ አዕምሮ መሳት የፈለቀ ሃሳብ ነውን? የአጋንንት ተፅዕኖ ነውን? ወይንስ የእነዚህ የሦስቱ ድብልቅ ወይም ጥምር ውጤት ነውን? ወይንስ ሌላ አሁንም ሌላ ምንጭ? ይህ ሁሉ በእርግጥ እጅግ በጣም ብዙ ጠቃሚ አይደለም፡፡ ምንጩ እግዚአብሔር ካልሆነ በእርግጥ አላምንበትም እናም ከምንም እንደሆነ እኔን አያስጨንቀኝም፡፡

ይህንን ያልኩበት ምክንያት የቁርአን አምላክ እና የመጽሐፍ ቅዱስ አምላክ አንድ ሊሆኑ ይችላሉ ነገር ግን የአንዱ መገለጥ እውነተኛ የሌላው ደግሞ የውሸት ነው፡፡ ሙስሊሞችም እራሳቸው ስለመጽሐፍ ቅዱስ በትክክል የሚጠይቁትና የሚከራከሩት ይህንን በተመለከተ ነው፡፡ ሙስሊሞች መጽሐፍ ቅዱስ አሁን ባለበት በትክክለኛ ሁኔታ ከእግዚአብሔር እንደሆነ አያምኑም (ለዚህም ነው መጽሐፍ ቅዱስ ተበክሏል) እያሉ የሚሉት፡፡ ብዙዎቹም ሙስሊሞች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉት አንዳንዶቹ መጽሐፍትም ከመጀመሪያውም እዚያ እንዳሉ አይቀበሉም፡፡ ስለዚህም የእነሱ ክስ ከዚህ በላይ እኔም እንዳቀረብኩት ዓይነት ነው የሚሆነው፡፡ እናንተ ምናልባትም መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገርለት እግዚአብሔርና ቁርአንም የሚናገርለት እግዚአብሔር አንድ ናቸው ብላችሁ ልትስማሙ ትችሉ ይሆናል ነገር ግን እንደ እናንተ አባባል የመጽሐፍ ቅዱስ ምንጩ የእናንት እግዚአብሔር አይደለም ስለዚህም መጽሐፍ ቅዱስ ሌላ ምንጭ ሊኖረው ይገባል፡፡ የሆነው ሆኖ እሱስ ማነው?

ይህንን ሁኔታ በእናንተ ክስ ውስጥ በማስቀመጥ እናንተ የሙስሊም አንባቢዎች እንደምትጠይቁት ሁሉ ክርስትያኖችም በቁርአን ላይ ተመሳሳይ ጥያቄ ቢኖራቸው ቅር እንደማይላችሁ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ በእርግጥ ሌላ ምንም አማራጭ ሊኖር አይችልም፡፡ ምንም እንኳን ይህንን በተመለከተ ሁልጊዜ ልንናገር ባንችልም፣ ሊኖር የሚችለው ውጤት ይህ ብቻ ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ካልሆነ መሆን ያለበት እጅግ ብልሃት የተሞላበት አንድ ዓይነት ማጭበርበር ነው እንዲሁም ሌላ ምንጭ ነው፡፡ ነገሩም ቅንነት የሞላው ምናልባትም እውነተኛ የመሰለ ነገር ሊሆን ይችላል ነገር ግን ምንጩ ሌላ ነው፡፡ ይህም ደግሞ ማንም ይሁን ምን ማወቁ ያን ያህል ጠቃሚ አይደለም፡፡

ስለዚህም ወደ መጀመሪያው ጥያቄ እንደገና ለመምጣት (ለመመለስ) ያህል፣ እኔ እንደማምነው ከሆነ ቁርአንና መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገሩት ስለተለያየ አምላክ ነው ብለው የሚናገሩት ሰዎች ‹ርዕስን› እና ‹ምንጭን› ወይንም ‹ርዕስን› እና ‹ይዘትን› አምታትዋል ብዬ ነው፡፡ ምክንያቱም ይዘት (ገለጣው) የተለያየ ስለሆነ ይህ የተለየ እግዚአብሔራዊ መረዳት ነው በማለት አንድ ሰው ሊናገር ይችላልና፡፡ ይህም ደግሞ ከሞላ ጎደል ሁለቱም የሚናገሩት ስለ ተለያየ አምላክ ነው ወደማለት ለመውሰድ የሚያበቃ ነውና፡፡

በሙስሊሞችና በክርስትያኖች የሚነገረውን የተለያየ እግዚአብሔራዊ መግለጫዎችን አንዳንዶች አዳምጠው የምትናገሩት ስለተለያዩ አምላኮች መሆን አለበት ይህም ደግሞ ግልጥ ነው ማለት ይችሉ ይሆናል፡፡ ሌሎች ደግሞ የምትነጋገሩት ስለ ተመሳሳይ አምላክ ነው (ምክንያቱም ያለው አንድ ፈጣሪ ብቻ ነውና ምክንያቱም ሁለቱም አንድ አምላክ ብቻ እንዳለ ያምናሉና ስለዚህም የሚናገሩት ስለዚያው አንድ አምላክ ነው) በማለት ሊናገሩ ወይንም መደምደሚያ ላይ ሊደርሱ እንኳን ይችሉ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ከሚናገሩት ልዩነት የተነሳ ነው አንዳቸው የተሳሳተ ወይንም የውሸት መረጃ ያላቸው፡፡ ቢያንስ፣ ቢያንስ ጥቂት የተሳሳተ መረጃ ምናልባትም ብዙው እንኳን አንድ ዓይነትና ተመሳሳይ ሊሆን ቢችልም እንኳን ነው፡፡ ስለዚህም እኔ ‹ይህ ቤት በሙሉ በቀይ ቀለም የተቀባ ነው ብል› ሊኖሩ የሚችሉት አማራጮች ሁለት ናቸው፡ እኛ የምንወስደው ሁለት የተለያዩ ቤቶችን ነው (ሁለት የተለያዩ አምላኮች) ወይንም እኛ በእርግጥ የምንጠቁመው ወደ አንድ ቤት ነው (አንድ አምላክ) ነገር ግን ከሁለት አንዳችን የተሳሳተ መረጃን እየሰጠን ነው ማለት ነው፡፡

ነገር ግን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የምናውቀው ነገር ሁሉ የመጣው በአንድ ዓይነት መረጃ ስለሆነ (የተጻፈ ወይንም በቃል የተላለፈ) መረጃው የተለየ ከሆነ ስለ እግዚአብሔር ሊኖረን የሚችለውም የእኛ መረዳት የተለየ ነው ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔርን እናመልከዋለን ይህም የሚሆነው ስለ እሱ ባለን መረጃ መሰረት ላይ ተመስርቶ ነው፡፡ ስለ እግዚአብሔር ያለን የመረዳት ዓይነት የተለያየ ከሆነ  ሊሆን የሚችለው የተለያዩ አማልክትን እንደምናመልክ ነው፡፡ ስለ አንድ ቀይ ቤት ብሰማ የኔ ግምት የሚሆነው ቀይን ቤት ማየት ነው፡፡ ስለ አረንጓዴ ቤት ደግሞ ብሰማ በአዕምሮዬ የምገምተው አረንጓዴ ቤትን ነው እነዚህም ነገሮች የሚሆኑት በቤቱ ላይ ካለው ተጨባጭ ከለር ሁኔታ በተለየ መልኩ ነው፡፡ የማየው ቤት ግን በአዕምሮየ ከገመትኩት የተለየ ነው፡፡ ስለዚህም ስለ እግዚአብሔርም የሚኖረን የተለየ መረጃ በአዕምሮአችን ውስጥ የተለየ አምላክን ነው የሚያስቀምጠው ስለዚህም እግዚአብሔርን የምናመልከው በአዕምሮአችን ውስጥ እንዳወቅነው መጠን ነው፡፡ በዚያ አመለካከት የተነሳ የእኛ አምላኮች የተለያዩ ናቸው (በዚያም መሰረት የሚታሰቡት አማልክት በሙስሊሞች በራሳቸውም መካከል እንኳን እንዲሁም ክርስትያኖችም በራሳቸው መካከል የቀረፁት አምላክ የተነሳ የተለያየ አምላክ ሊኖራቸው ነው ማለት ነው፡፡) ወይንም ያላቸው መረዳት የተለያየ ነው ማለት ነው፡፡

አሁን ከዚህ በመቀጠል ያንን ቃለ መጠይቅ (መገለጥ) እንመርምረው፡፡ ከትክክለኛ ምንጭ ለመምጣታቸው ወይንም ካስመሳይ ምንጭ ለመምጣታቸው እራሳቸውን ጽሑፎቹን በማስተዋልና በጥሞና ማንበብ እጅግ ብልሃት ነው፡፡ ለማንኛውም የሚከተሉትን እናስተውል፡-

ይህንን ጥያቄ ምናልባት ግልጥ ሊያደርግ የሚችለው ሌላው ማብራሪያ የሚሆነው የሚከተለው ነው፡፡ የተለያዩ ሰዓሊዎች የአንድን ሰው ስዕል ይሳሉ ብላችሁ አስቡ፡፡ አንዱ ሰዓሊ ሐቀኛ በመሆን የውጭውን ሁኔታ እንዳለ በዝርዝር ጥቃቅኗን ነገር ሁሉ ልቅም አድርጎ ነው ያስቀመጠው፡፡ ሌላው ደግሞ የሚሳለው ሰው በጣም የቅርብ ጓደኛ ሊሆን ይችላል እናም ስዕሉን ሲስል የውጪውን ብቻ ሳይሆን የሚያውቀውን የውስጥ ባህርዩን በሚያንፀባርቅ መልኩ የሚማርክ አድርጎ ሳለው ይህም በውጪ ካለው አካላዊ ዝርዝር ለየት ባለ መለኩ ማለት ነው፡፡ ሦስተኛው ደግሞ የአብስትራክት ሰዓሊ ስለሆነ የሰውየውን ማንነት ምንም ሳያውቅ ያቀረበው ሰውየውን በተመለከተ ያለውን የራሱን ስሜት እና ሐሳብ ብቻ ነበር ይህም ሰውየው በእውነት ከሆነው ውጪ በሆነ መልኩ ነበር፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጌታ ኢየሱስ የሚናገረው ነገር እግዚአብሔር ስለ እሱ በሕይወትና በእውነት ስለተናገረው ነገር ነው፡፡ የሚከተሉትን እንመልከት፡- ዮሐንስ 14.9 ፊሊጲሲዩስ 2.6-7፣ ቆላስያስ 1.15፣ ዕብራውያን 1.3 ፡፡

መጽሐፍ ቅዱሳዊ መጽሐፎችም የእግዚአብሔርን፣ የጌታ ኢየሱስን የነቢያትን ምስል ያቀርቡልናል (ይስሉልናል) .. ይህም ጓደኛቸውን እንደሚስሉ ሰዓሊዎች ሰዎች በመሆን ነው፡፡ የእራሳቸውን ጥልቅ የሆነ ልምምድ እና እውቀት በተጨማሪም በመንፈስ ቅዱስ በመመራት የእግዚአብሔርን ትክክለኛ ባህርይ በማወቅና በማግኘት ነው፡፡ ለምሳሌም ያህል ስለ ክርስቶስ ባህርያት በወንጌሎች ውስጥ እጅግ ብዙ ነገሮችን እንማራለን ነገር ግን እሱን በተመከተ አንድም አካላዊ መግለጫን አናይም፡፡

ስለዚህም የእኔ አረዳድ ቁርአን የእግዚአብሔር ምስል ያለበት መጽሐፍ ነው ሰዓሊው ደግሞ ልክ አብስትራክቱን ስዕል የሳለውን ዓይነት ሰዓሊ ነው ማለትም እግዚአብሔርን በቅርብ በማያውቅ እና እግዚአብሔር ምን መምሰል ስላለበት የራሱን ሐሳብ ያስቀመጠውን ወይንም የሳለውን ሰው ነው የሚመስለው፡፡ ስለ እግዚአብሔር ያለን የእኛ የሰዋዊ ፍልስፍና ሐሳብና ግምት በብዙ መንገድ የሚመስለው ተመሳሳይ ስለሆነ ስለዚህም ስዕል ሰዎች የራሳቸውን ሐሳብ እንዲሰጡ ብዙ ጊዜ ስንጠይቅ እንገኛለን፡፡ ነገር ግን ይህ ሁሉ እውነት ነው ማለት አይደለም፡፡ ሊሆን የሚችለው ብዙ ሰዎች ስለ እግዚአብሔር ያላቸው አመለካከት አንድ ዓይነት መሆኑንና እሱንም ሊያዩት የሚፈልጉት በዚያው መንገድ መሆኑን ብቻ ነው፡፡

የአብስትራክት ሰዓሊው ምናልባትም ስለሚስለው ሰው አንድ አሮጌ የሆነን እና በብዙ ቦታ ላይ የተበላሸ ስዕልን አይቶ ሊሆን ይችላል እሱም አንዳንድ እውነተኛ የሆኑ ዕይታዎች ሊኖሩት ይችላሉ ነገር ግን በብዙ ቦታዎች ላይ የራሱን አስተሳሰብና ግምት መሙላት ይኖርበታል፡፡

በተመሳሳይም መንገድ መሐመድ የቀደሙትን የእግዚአብሔርን ቃላት በራሱ ለራሱ ሊያነብ አልቻለም ነበር፣ ነገር ግን ከአይሁዶች እና ከክርስትያኖች ብዙ ጥሩ ጥሩ ታሪኮችን ሰምቷል፡፡ ስለዚህም እሱ የሚያስታውሰው አንድ ትክክለኛ ስዕል አለው እነዚህንም የሚያስታውሳቸውን የሰማቸውን ነገሮች በመጠቀም ለሚያስበው ነገር የራሱን ሐሳብ እየሞላባቸው አስቀመጣቸው፡፡ በቁርዓን ውስጥ ላሉት ለብዙ ተመሳሳይ ነገሮች መገኘት ዋናው ምክንያት ይህ የስማ-በለው ታሪክ ነው፡፡ እሱም ስለእግዚአብሔር ላይ ላዩን የሆነውን ነው የሚያሳየው፡፡ ነገር ግን መሰረታዊው ልዩነት የመጣው ይህንን እግዚአብሔር በግል ካለማወቅ እና የግልም ግንኙነትን ከእሱ ጋር ካለማድረግ የተነሳ ነው፡፡ ሌሎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ያደረጉት ግን ከእግዚአብሔር ጋር የግል ግንኙነትና ትውውቅ ለጻፉት ነገር ወጥነት ሰጥቶታል ማለት ነው፡፡

አንድን ነገር ወይንም አንድ ሰው ምን ይመስላል ብለን በምናስብበት ጊዜ (ለምሳሌም አንድ ልብ ወለድ የሆነን ጽሑፍ ምንም ስዕል የሌለውን) በአዕምሮአችን የሚሳልብን የእነሱ ስዕል ብዙውን ጊዜ የሚሆነው በእኛ የቀደም የሕይወት ልምምዳችን መሰረት ይሆንና ይህንን መጽሐፍ ከሚያነቡት ሌሎች ሰዎች ምስል ቀረፃ በጣም የተለየ ይሆንብናል በተለይም ጸሐፊው ሲጽፈው በአዕምሮው ካለው (ከቀረፀው) ከጻፈው በጣም የተለየ ነው የሚሆነው፡፡ ይህም ደግሞ በብዙ የሰዎች ታሪክ መጽሐፍትና እና ባዮግራፊዎች ውስጥ ልክ እንደ ልብ ወለዱም እውነት ነው፡፡

ከዚህ የተነሳ ከዚህ በላይ ያየነው ሰዓሊ ምንም እንኳን የእውነተኛውን ሰው ስዕል ለመሳል ቢያቅድም እንኳን ከሰውየው እውነተኛ እውቀት በመነሳት ስለማያደርገው የሚስለው ስዕል በሐሳቡ ያሰበውን እና ባደገበት አካባቢ ካለው አመለካከት እና አስተሳሰብ በሰበሰበው መረጃ መሠረት የሆነውን ነው ስለዚህም ስዕሉ ትክክለኛውን ሰው የሚያሳይ ሊሆን አይችልም፡፡ እኔ እንደማስበው ይህ ምሳሌያዊ ማብራሪያ ‹አላህ የጨረቃው አምላክ› የሚለውን መጽሐፍ የጻፉትን የዶ/ር ሞሬን እና የሌሎችን አቋም ለመረዳት በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ እነሱም በመሐመድ ማኅበረ ሰብ ውስጥ ስለ እግዚአብሔርና ስለምስሎች ያለውን መረዳትና (ከእውነተኛ እውቀት ማጣት የተነሳ) በተመለከተ ማስረጃዎችን ይመራመሩ ነበር፣ ይህ ስለእግዚአብሔር መሐመድ ያስተማረው ትምህርት ምንጭ የሚሆነው፡፡ በመሐመድ ጊዜ የነበረውን የጣዖት አምልኮ የጀርባ እውነት መሠረት በማድረግ የተሰጠው ትንተና እንደሚከተለው ነበር፡ መሐመድ ያስተዋለው እጅግ ብዙ አማልክትን (የጣዖት) ማምለክ ጥሩ ሊሆን አለመቻሉን፣ ነገር ግን እነዚህን ትናንሽ አማልክት/ጣዖታት ለማስወገድ ደግሞ መሐመድ ከልጅነቱ ጀምሮ ስለ እግዚአብሔር ሲቀባው የነበረው ምስል ማለትም በአደገበት አካባቢ ሲሰማ ከነበረው የሱ ማኅበረሰብ ከነበረው ጣዖታዊ መረዳት ጭምር አገልለግሎት ላይ ዋለ፡፡ በተለይም ከነዚህ ውስጥ ከፍተኛ ጠቀሜታ ደረጃ ላይ ደርሶ የነበረው ‹የጨረቃ አምላክ› ነበር፡፡ ዶ/ር ሞሬ እንዳስተዋለው መሐመድ ከእነዚህ አማልክት ውስጥ ትልቁን (ዋነኛውን) በመውሰድ እሱን እንደብቸኛ ማወጅና ሌሎቹን ትናንሾችን ማጥፋት የሚለውን ነበር ነገር ግን የዚህን ከፍተኛ ጣኦት ባህርያትን በመያዝና በመጠበቅ ነበር ያደረገው፡፡

የዚህን አቀራረብ እረዳዋለሁ ነገር ግን ከሙስሊሞች ጋር በሚደረግ ክርክራዊ ውይይት ውስጥ በጣም ጠቀሜታ የሚኖረው አይመስለኝም፡፡ ይህ ደግሞ ሙስሊሞች የሚቀበሉት አይደለም፡፡ ነገር ግን እሱም ሙስሊሞች ይህንን ያምናሉም አላለም፡፡ እሱ ያለው የሙስሊሞች እምነት ምንጭ ይህ ነው ነገር ግን ምንጩ ከየት እንደሆነ አያስተውሉትም ነው፡፡  

በእርግጥ ሙስሊሞች የሚያደርጉት በትክክል ተመሳሳይን ነገር ነው ይህም የአንዳንድ ዶክትሪኖችን ምንጭ ሲናገሩ ለምሳሌም ያህል ‹የክርስቶስን ስጋ ለብሶ መምጣትን›፣ የጌታ ኢየሱስን የእግዚአብሔር ልጅነት፣ ስላሴን ወ.ዘ.ተ ሁሉም ቤተክርስትያን ከአይሁድ ወደ አሕዛብ ዓለም ስትስፋፋ የገቡ እና የተቀላቀሉ ፓጋናዊ ፅንሰ ሃሳብ ናቸው በማለት ነው፡፡ ሙስሊሞች ክርስትያኖችን የሚከሱት ፓጋናዊ ፅንሰ ሃሳብን በመውሰድ እንዳጠመቁ ነው ይህም ልክ እንደ ዶ/ር ሞሬ እና ሌሎችም መሐመድ የአረብን የጨረቃ ባህርይ ነው ወደ አንድ አምላክ ትምህርት ውስጥ ያመጣው እንደሚሉት ማለት ነው፡፡

እኔ እንደማስበው ከሆነ ይህ አቀራረብ ለውይይት እንዲሁም ደግሞ ለክርክር ብዙ ጠቀሜታ የሌለው ነው፤ እንዲሁም ደግሞ ሙስሊሞች፣ ክርስትያኖች ስለ እግዚአብሔር ያላቸውን አመለካከት ሲሰሙ ለምን እጅግ በጣም እንደሚቆጡም ምንም ምክንያትን ለማግኘት አልችልም፡፡ አንድን ነገር ሳይ የምመለከትበት የኔ ክርስትያናዊ አመለካከት ከዚህ በላይ የተናገርኩት ነው፡፡ ሙስሊሞች ይህንን ምሳሌያዊ አቀራረብ ወስደው እንዲህ ሊሉ ይችላሉ መሐመድ በፍፁም ስዕልን አልሳለም፣ ነገር ግን የሆነው ነገር እሱ ሰማያዊውን ኦሪጅናል ነገር በትክክል የሚያሳይን ፎቶ ግራፍ ነው የተሰጠው፡፡ አሁንም እንደገና በቁርአን ውስጥ አለ የሚባለው ሰማያዊ ነገር እንደፎቶ ግራፍ ልወስደው እችላለሁ ነገር ግን እሱ የሚሆነው ከላይ የተሳለው የአብስትራክት ስዕል ፎቶ ነው የሚሆነው ይህም ከመጀመሪያው ጀምሮ በእውነት ላይ ያልተመሰረተው ምስል ፎቶ ነው፡፡

በእርግጥ በጣም በጥንቃቄ በእጅ የተገለበጠ የአንድ እውነተኛ ምስል ከውሸት (እውነት ካልሆነ) ምስል ላይ ከተወሰደ ፎቶ ግራፍ ወደ እውነቱ በጣም በተሻለ መንገድ የቀረበ ነው የሚሆነው፡፡ ቁርአንም መጽሐፍ ቅዱስም ሁለቱም በየራሳቸው የጽሑፍ ልነቶች እንዳሏቸው ማሳየት ይቻላል በሁለቱም መጽሐፍት በኩል መቶ በመቶ በሆነ ጥበቃ ቆይተዋል ማለት አይቻልም፣ ነገር ግን ሁለቱም በደህና ተጠብቀዋል ስለዚህም እኛ ልናምን ልንተማመን የምንችለው አሁን ያሉት ጽሑፎች ከመጀመሪያዎቹ ቅጅዎች ጋር አንድ ዓይነት መሆናቸውን ነው፡፡

ተጠብቆ መቆየት በራሱ ስለ እውነት ምንም የሚናገረው ነገር ያለመኖሩ እውነታ እንዲሁም ብዙ ስህተት ኖሮባቸው እጅግ በጣም ተጠብቀው የቆዩ መጽሐፍት መኖራቸው፣ እንዲሁም ሁለቱም መጽሐፍ ቅዱስም ቁርአንም በደህና ሁኔታ ተጠብቀው የመቆየታቸው ነገር መታየት እንደገና የሚመልሰን እጅግ በጣም ጠቃሚ ወደሆነው ጥያቄ ነው፡፡

ያም የምታምኑበት መጽሐፍ (ቁርአን ወይንም መጽሐፍ ቅዱስ) በመጀመሪያ ከእግዚአብሔር ለመሆኑ በምንድነው የምታውቁት? ወይንም እውነተኛውን ምስል መወከሉን የምታውቁት?

የአዘጋጁ ማሳሰቢያ፡-

አመልከዋለሁ ወይንም የሃይማኖቴ መሠረት ነው ስለምንለው ስለ አምላካችን ትክክለኛ ግንዛቤ ማግኘት ከምንም ነገር የበለጠ ነው፡፡ እግዚአብሔር ማን ነው እንዴት ነው ላመልከው የምችለው፡፡ ከእሱስ ጋር አንድ የሚያደርገኝ የሕይወት ገፅታ በእርግጥ አለኝ ወይ? እሱ ሊታወቅ የሚችለው እንዴት ነው? ከሰው ልጆች የሚፈልገው ነገር አለ ወይ? የመሳሰሉት ጥያቄዎች ዘለዓለምን የት እንደምናሳልፈው የሚወስኑ ናቸው፡፡ የምናመልከው አምላክ ትክክለኛው አምላክ ካልሆነ መጨረሻችን በቀልድ ሊታለፍ የሚችል አይሆንም፡፡

ስለዚህም በዚህ ገፅ ላይ የሚወጡትን ጽሑፎችን ማንበብና መጽሐፍ ቅዱስን መመርመር በጣም እሰፈላጊ እንደሆነ ለአንባቢዎች ለማስታወስ እንወዳለን፡፡ ጌታ ወደ እውነተኛው አምላክ አምልኮ ያምጣችሁ አሜን፡፡

 

የትርጉም ምንጭ:  Is Allah the God of the Bible?

 

ለእስልምና መልስ አማርኛ ዋናው ገጽ