የመጽሐፍ ቅዱሱ ኢየሱስና የቁርአኑ ‹ኢሳ›

በJay Smith

[ክፍል አንድ] [ክፍል ሁለት]

ትርጉም እና ቅንብር በAI ቡድን

ይህ የሚወደድና በጣምም አስፈላጊ ርዕስ ጉዳይ ነው፡፡ ሙስሊሞች ስለ ‹ኢሳ› ለማውራትና ለመነጋገር በጣም ደስተኞች ናቸው፡፡ እኛም ክርስቲያኖች በተለይ ወንጌላውያን ደግሞ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መነጋገርን እንወዳለን፡፡ እኛ ክርስቲያኖች ኢየሱስ ጌታ ነው ብለን ንግግራችንን የምንጀምር ከሆነ ሙስሊም ምሁራንም ሆኑ ሌሎች ለክርክርና ለሙግት የተመቸ ሁኔታ ውስጥ የገባንላቸው ስለሚመስላቸው ሐሳባችንን ለማጣጣል የሚችሉ ሆነው ይታያሉ፡፡

ይሁን እንጂ በሃይማኖታቸው ስለ ኢየሱስ የተሰጣቸው ትምህርት የተሳሳተ በመሆኑ እኛ አንገረምም እንደነቅምም፡፡ እነሱ ኢየሱስን የሚመለከቱ ናቸው ያሏቸውን ጥያቄዎች ለመጠየቅና ለመሟገት ድፍረት እንዳገኙት ሁሉ፣ እኛም አግባብ ያለውን መልስና ጥያቄ ማቅረብ ይኖርብናል፡፡

አትመልሱልን ብትመልሱልንም አንሰማም ማለት አያዋጣቸውም፡፡ እርግጥ ነው የእውነት ሁሉ ባለቤት፣ የልብን የሚያውቅ የተደረጉና የተባሉ ነገሮችን ብቻ ሳይሆን፣ እነዚያን ንግግሮች የተናገረውን፣ ጽሑፎች የጻፈውን፣ ያናገረውንና ያስጻፈውን ሰውና ከሰውየው በኋላ ግፊትን የሚሰጠውን ማንነትና ኃይል የሚያውቅ የመጨረሻው ዳኛ እግዚአብሔር እንደሆነ እናምናለን፡፡

ይሁን እንጂ እንድንድንበት፣ እንድንመራበትና እንድንኖርበት እግዚአብሔር በሰጠን ዘላለማዊ ቃልና እውነት ላይ የሚሰነዘሩ ስህተቶችን ዝም ብለን መኖር አለብን ማለት አይደለም፡፡ ሌላው ቢቀር ያልሆነው እንደሆነ ያልተጻፈውን እንደተጻፈ አድርገው ለተናገሩት ለጻፉት ለሼህ አህመድ ዲዳት፣ ለዶ/ር ዛኪር ናይክ እና ለእነ መሐመድ አጧኡረሂም እውነቱ መነገር እንዳለበት እርግጠኞች ነን፡፡

ሰዎች ገሃድ የሆነው ስህተታቸው ሲነገራቸው ከተፀፀቱና ከተመለሱ ያ በእርግጥ በየዋህነት የፈፀሙት ስህተት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሌላውም ወገን የእነዚህ ሰዎች የነገር ጅማሬ ምን እንደሆነ ለማወቅ ግልጥ ማስረጃ ይሆናል፡፡

በግልፅ ከዘላለማዊው የእግዚአብሔር ቃል ያፈነገጠ ያልተጻፈው እንደተጻፈ፣ ትክክል የሆነው ጠማማ ሆኖና ተደርጐ የሚነገርና የሚጻፍ መልዕክት መታረም ይኖርበታል፡፡ ስህተት ሁልጊዜ ብቻውን ስፍራ ስለማይኖረው በእውነት ጀርባ ላይ መፈናጠጥ ይወዳል፡፡ ስለዚህም ይህንን ለይቶ ለማሳወቅ ይህ የእውነት ዘገባ ቀርቦልናል፡፡

የመጽሐፍ ቅዱሱ ጌታ ኢየሱስ የቁርአኑ ‹ኢሳ› ነው ብለው የሚያምኑት ሙስሊሞች፣ ‹ኢሳ› በእርግጥ ታላቅ ነብይ እንደሆነ እናምናለን ይላሉ፡፡ በእስላም ትምህርት መሠረት ከመሐመድ ቀጥሎ በጣም ታላቅ ነቢይ ‹ኢሳ› እንደሆነ ነው፡፡ እዚህ ላይ ነው እንግዲህ የመጀመሪያው ጥያቄ የሚነሣው፡፡ ‹ኢሳ› የምትሉት የመጽሐፍ ቅዱሱን ኢየሱስ ከሆነ፣ እንዲሁም እርሱ ታላቅ ነቢይ እንደሆነ ካመናችሁ ስለምን እኛ ክርስትያኖች እሱን አዳኛችን አድርገን እንደተቀበልነው አትቀበሉትም? ብለን እንጠይቃለን፡፡

በቁርአን የተጠቀሰው ‹ኢሳ› በመጽሐፍ ቅዱስ ከተገለጠው ጌታ ኢየሱስ ጋር መጠነኛ መመሳሰል እንዳለው ቁርአንና ሊቃውንቱ የሚግሩንን መመልከት ይቻላል፡፡ ለምሳሌም በቁርአን ከ114 ምዕራፎች በአስራ አምስቱ ምዕራፎችና በዘጠና ሦስት አንቀፆች ውስጥ ‹ኢሳ› የሚለው ስም ተጠቅሷል፡፡

ተመልከቱ በአዲስ ኪዳን (የወንጌል መጽሐፍቶች) በሙሉ የኢየሱስ ክርስቶስ ስም ያልተነሳበት ያልጠቀሰበት ክፍል የለም፡፡ ቁርአን ግን ከ114 ምዕራፎች በ15ቱ ውስጥ ብቻ ነው ‹ኢሳ› እያለ የሚነግረን፡፡ በዚህም ቁርአን የትኩረት ነጥቡ ምን እንደሆነ ያሳየናል፡፡

የቁርአን ሊቃውንት ‹ኢሳ› የሚሉት የመጽሐፍ ቅዱሱን ኢየሱስ ከሆነ ቢያንስ በአወላለዱ እንኳን ከፍተኛ ልዩነት  ስለምን ሊኖር ቻለ? በማለት እንጠይቃለን፡፡ ምክንያቱም ስለ ቁርአኑ ‹ኢሳ› አወላለድ (በመርየም 16-23 እና 29-33 አልኢምራን 42-47 እና 59) ስንመለከት የሚያወራው መርየም በመልአኩ አማካይነት ብሥራትን እንደተነገራት ነው፡፡ ይህ የብስራት አቀራረብ ከሉቃስ ወንጌል 1.26-29 ደግሞም 1፡31-33 ጋር ይቀራረባል፡፡

የ‹ኢሳ› አወላለዱ ከሰዎች ልዩ መሆኑን ለማጣጣልም ቁርአን እንዲህ ይላል፣ ‹ኢሳ እንደ አዳም ብጤ ነው› አል-ኢምራን 59፡፡ እዚህ ነጥብ ላይ አስተውሉ እሱ ‹ኢሳ› መለኮታዊነት የለውም ለማለት አዳምን ከአፈር የሠራው አላህ ‹ኢሳንም› መርየም ማህፀን ውስጥ ፈጠረው ይላል፡፡ መርየም በድንግልና ፀንሳ መውለዷን ግን ይተርካል፡፡ መርየም 2ዐ፡፡ ይህንን በተመለከተ ለንፅፅር የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ አንድን ለማየት ይቻላል፡፡

ይህ ታሪክ ለሙስሊሞች አስፈላጊ ነው ከተባለ፣ እንዲሁም ደግሞ መርየም የመጽሐፍ ቅዱሷ ማርያም ነች ከተባለ፣ በተጨማሪም ደግሞ ‹ኢሳ› ኢየሱስ ነው ከተባለ ስለምን አዲስ ስያሜና የተለወጠ ታሪክን የያዘ መገለጥ ለማምጣት አስፈለገ? የራሳቸሁን መልእክትስ ለማረጋገጥ ብቻ ስለምን መጽሐፍ ቅዱስን ትጠቅሳላችሁ? በማለት ሙስሊሞችን እንጠይቃለን፡፡

አስደሳቹ ጉዳይ በቁርአን ከተጠቀሱትና ነቢይ ከተባሉት ውስጥ ከሴት ብቻ የተወለደ ያውም ድንግል ከሆነች ሴት ብቻ የተወለደ ‹ኢሳ› መሆኑ ያለመካዱ ነው፡፡ በስነ ፅንስ ምርምር መሠረት አንድ ሰው ወንድ ወይም ሴት ሆኖ ለመፈጠር የ XY እና XX ክሮሞዞም ትንታኔ እንደሚከተል ይታወቃል፡፡ ኢየሱስ ወንድ ስለሆነ ያለው የ XY ክሮሞዞም ነው፡፡ እንግዲህ ተመልከቱ መርየም ያላት XX ክሮሞዞም /ሀብለበራሂ/ ነው፡፡ ‹ኢሳ› ወንድ ሆኖና XY ክሮሞዞም /ሀብለበራሂ/  መኖሩ ከታምራት የላቀ ታምራት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ቁርአን ‹ኢሳን› ቀዳሚ ታላቅ ነቢይ አላደረገውም፡፡

አህመድ ዲዳትና ዶክተር ዛኪር ናይክ መጽሐፍ ቅዱስንና ክርስቲያናዊውን አስተምህሮት ስህተተኛ ለማድረግ በጣም ፀያፍ ንግግርን ተጠቅመዋል፡፡ እነርሱም ‹እግዚአብሔር ከማርየም ልጅ ወለደ በማለት ክርስቲያኖች ታምናላችሁ› ብለው ይናገራሉ፡፡ ከዚያም ቁርአን 5.116 ይጠቅሳሉ፡- ‹አላህም የመርየም ልጅ ኢሣ ሆይ አንተ ለሰዎቹ እኔንና እናቴን ከአላህ ሌላ ሁለት አምላኮች አድርጋችሁ ያዙ ብለሃልን? በሚለው ጊዜ፣ (አስታውስ) ጥራት ይገባህ ለኔ ተገብዬ ያልሆነን ነገር ማለት ለኔ አይገባኝም፣ ብዬው እንደሆነም በእርግጥ አውቀኸዋል በነፍሴ ውስጥ ያለውን ሁሉ ታውቃለህ ግን አንተ ዘንድ ያለው አላውቅም አንተ ሩቆችን ሁሉ በጣም አዋቂ አንተ ነህና ይላል፡፡›

ቁርአን፣ ‹ኢሳ› በማለት የሚጠራው ኢየሱስ ባልነበረበት ዘመን ማለትም ከእሱ 6ዐዐ ዓመታት ወዲህ የመጣ መጽሐፍ ነው፡፡ ታዲያ ‹ኢሳና› አላህ በሚነጋገሩበት ጊዜ (ጸሐፊው) የት ሆኖ ነው ያደመጠው? በእርግጥ ይህ ጥቅስ ትንቢታዊ ነው የሚመስለው ማለትም ወደፊት አላህና ኢሳ እንደዚህ ይነጋገራሉ የሚለን ከሆነ ደግሞ ቁርአን አላህ ስለሚጠይቀው ጥያቄና ስለ ኢሳ መልስ ቀድሞ ያውቃል እንዴ? ወይስ ይህ ትምህርት ቀድረላህ ይሆን? ብለን እንጠይቃለን፡፡

የቁርአኑ ኢሳ ታምራትን እንደሠራ ከተናገረው ቁርአን በአሊ-ኢምራንና በመርየም ምዕራፍ ያሉት ታምራቶች መጽሐፍ ቅዱስ የማያውቃቸው ናቸው፡፡ ለምሳሌ በእናቱ እቅፍ እያለ ለሰው በሚባ ቋንቋ መናገሩ ቁጥር 4ዐ እንዲሁም ቁጥረ 49 ከጭቃ ወፍ መፍጠሩን የሚያወራው ክፍል ማለታችን ነው፡፡ ወደ ኋላ ተመልሰን ስንመለከት በቁርአን ውስጥ ያለው ‹የኢሳ› አወላለዱም የተለየ ነው፡፡ በመርየም 22-26 ስለውልደቱ ተጽፏል፡፡ ቁጥር 22 ወዲያው አረገዘች ጽንሱን ተሸክማ ሩቅ ወደ ሆነ ሥፍራ ተገለለች፡፡ ምጡም ወደ ዘንባባይቱ ግንድ አስጠጋት ቁጥር 23 ወይኔ ምነው ከዚህ በፊት በሞትኩና የተረሳሁ በሆንኩ አለች፡፡ ቁጥር 24 ከበታችዋም አትዘኚ ጌታሽ ከበታችሽ ትንሽ ወንዝ አድርጓል፡፡ ቁጥር 25 የዘንባባይቱን ግንድ ወዝውዥው የበሰለ የቴምር እሸት ያረግፈልሻልና ቁጥር 26 ተመገቢ ጠጪም ደስታ ይሰማሽ ሰዎች ባዩሽ ጊዜ ለአምላኬ ፆም ተስያለሁ ሰው አላናግርም በይ ይላል፡፡

ይህ የቁርአኑ ‹ኢሳ› የአወላለድ ትረካ ከመጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ክርስቶስ አወላለድ ትረካ ልዩ ነው፡፡ ስለ መወለዱ በነቢዩ ኢሳያስ ከ7ዐዐ ዓመታት በፊት ከተነገረው ትንቢት ኢሳያስ 9.1-9 በተለይ ቁጥር 6-7 ማለትም ‹ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል። ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘላለም ድረስ በፍርድና በጽድቅ ያጸናውና ይደግፈው ዘንድ በዳዊት ዙፋንና በመንግሥቱ ላይ አለቅነቱ ይበዛል፥ ለሰላሙም ፍፃሜ የለውም። የእግዚአብሔር ቅንዓት ይህን ያደርጋል።› ተብሎ የተነገረለት ይህ ጌታ ኢየሱስ ታዲያ የቁርአኑ ‹ኢሳ› ነው ወይ?

በሉቃስ ወንጌል 2.2-5 ዮሴፍ ወደ ቤተልሔም ለመመዝገብ የተጓዘው የመውለጃ ጊዜዋ ከተቃረበው ከእጮኛው ከማርያም ጋር ነበር በዚያም እንዳሉ የምትወልድበት ጊዜ ደረሰ የበኩር ልጇ የሆነውን ወንድ ልጅ ወለደች በጨርቅም ጠቀለለችው የእንግዶችም ማረፊያ ቦታ ስላላገኙ በግርግም አስተኛችው፡፡ ግርግም ማለት በከብቶች በረት ውስጥ የሚገኝ የከብት ምግብ መመገቢያ እንደ ገንዳ ያለ ቋት ነው፡፡

በቁጥር 8 - 12 ላይ ደግሞ በሌሊት መንጋቸውን የሚጠብቁ እረኞች በመልአክ እንዲህ ተባሉ፣ ‹በዚያም ምድር መንጋቸውን በሌሊት ሲጠብቁ በሜዳ ያደሩ እረኞች ነበሩ። እነሆም፥ የጌታ መልአክ ወደ እነርሱ ቀረበ የጌታ ክብርም በዙሪያቸው አበራ፥ ታላቅ ፍርሃትም ፈሩ። መልአኩም እንዲህ አላቸው። እነሆ፥ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና። ይህም ምልክት ይሆንላችኋል፤ ሕፃን ተጠቅልሎ በግርግምም ተኝቶ ታገኛላችሁ።›

ቀጥሎም በቁጥር 13 ድንገት ብዙ የሰማይ ሠራዊት ከመልአኩ ጋር ታዩ እግዚብሔርን እያመሰገኑ በቁጥር 14 ላይ እንዲህም አሉ፡- ‹ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ አሉ።› ከዚያም በቁጥር 15 እረኞቹ መልአኩ የገለጠላቸውን ሄደው ለማየት ወሰኑ፣ ሄደውም እንደተባለው ሆኖ ህፃኑን አገኙት ቁጥር 16-18፣ ደግሞም እጅግ ተደነቁ፡፡   

እንግዲህ ተመልከቱ በቁርአን ውስጥ ያለው የኢሳ ታሪክ እና የመጽሐፍ ቅዱሱ የኢየሱስ ታሪክ ፈፅሞ ተመሳሳይ አይደሉም፡፡ ምናልባት መርየም የሚለው ባለ አራት ፊደል ስም ማርያም ተብሎ ካልተወሰደ በስተቀር ሌላው ነገር ሁሉ የተመሣሳይነት ሒሣብ የለበትም፡፡

በቁርአን ውስጥ ያለው ጠቅላላው የኢሳ ትረካ ስለ ጌታ ኢየሱስ ከሆነም የሚያትተው ስለ ምድራዊ ጉዳዮች ብቻ ሲሆን፣ ከ7ዐዐ ዓመታት በፊት ከነበረው ትንቢት ጀምሮ እስከ ውልደቱ የመጽሐፍ ቅዱሱ ታሪክ የሚነግረን ኢየሱስ መለኮታዊ (ማለትም አምላክ) መሆኑን ነው፡፡ እኛ አሁን የቱን እንቀበል ብለን አንጠይም የተቀበልነውን እውነት እናውቃለንና፡፡ ነገር ግን ይህንን የሚሰማ ጉዳዩን ደጋግሞ መመርመር ይገባዋል እንላለን፡፡ 

በመቀጠል ቁርአን የኢየሱስን ውልደት የሚያወራ ከሆነ ታዲያ ስለምን ተሳሳተ? ብለን ከጠየቅን መልሱ ቁርአን ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘመን 7ዐዐ-8ዐዐ ዓመታት ወዲህ የተጻፈ መጽሐፍ በመሆኑና የተጠቀመው መረጃ የሲሪያ ክርስቲያን ዶክመንቶችን ስለሆነ ነው፡፡

ለምሳሌ ቁርአን ‹ኢሳ› (Issa) ሲል መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ (Jesus) ነው የሚለው፡፡ ትክክለኛው የዕብራይስጥ መጠሪያው ደግሞ /የሹዋ/ (Yeshuah) ነው፡፡ ቁርአን ግን ‹ኢሳ› (Issa) ብሎ የተጠቀመበት ስም “Esau” ኤሣው የተባለው የያዕቆብ ወንድም ስም ጋር በጣም ተቀራራቢ ነው፡፡

ስለዚህ እነዚህን ስሞች የተዋሰው ከሶሪያ ክርስቲያን እንደሆነ የሚጠቁመው ይህ ዶክመንት ኢየሱስ /Jesus/ የሚለው /ኢሱስ/ Iesous በማለት ነው የሚጠራው፡፡ እንግዲህ Issa ‹ኢሳ›፣ /ኢሱስ/ Iesous ከለሚለው ስም ጋር በድምጽ ተቀራራቢ እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ጥያቄችን የሚሆነው የሹዋ /በአረብኛ - የሱዋ/ ከሆነ ስለምን ‹ኢሳ› ከማለት የሹዋ ወይንም የሱዋ ብለው አልጠሩትም? የሚል ነው፡፡

ይህንን ጉዳይ ለማጠቃለል ስንመጣ መሐመድ አንድም ተሳስቶ የኤሣውን ስም ተጠቅሟል፡፡ ወይም ደግሞ የሶሪያ ክርስቲያኖች የሚጠቀሙበትን ‹ኢሱስ› የሚለውን ስም ለውጦ ተጠቅሟል፣ ወይም ደግሞ መልስ በሌለው ጥያቄ ምክንያቱን በአጠቃላይ ግምገማ የምንረዳውና ቁርአን የሚነግረን ስለ ሌላ ኢሣ ነውን? ቁርአን ለ93 ጊዜ ያህል ‹ኢሳ› እያለ ሲናገር፣ ‹ኢሳ› የመርያም ልጅ የሚለውንም አባባል ሲጠቀም፣ ከእርሱ የቀደመውን መጽሐፍ እርባና ቢስ አድርጐ ኢየሱስ የእግዚአብሔር መለኮታዊ ልጅ የሚለውን እውነታ ለመቃወም ጭምር ነውን?

ሊቃውንቶች እንዳጠኑት 75% ከመቶ ሰባ አምስት እጅ የቁርአን ንግግሮች ከሶርያ ክርስቲያን ዶክመንቶች የተቀዱ ስለመሆናቸው ተረጋግጧል፡፡ ሌላው የቁርአን የስህተት ምንጭ ከ7ተኛ እስከ ዘጠነኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ በመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮት ላይ የተነሱ የስህተት ትምህርቶች እንደሆኑ ሊጠቀሱ የሚችሉ ጉዳዮች ናቸው፡፡

ለምሣሌ፡-

1ኛ ሞናርኪያኒስቶች የተባሉት ቡድኖች እግዚአብሔር ልጅ የለውም ብለው ነበር፡፡ ቁርአንም አል-ኒሳዕ 171 አላህ ልጅ ያለው ከመሆን የጠራ ነው ይላል መርየም 34 ደግሞ ‹ኢሳ› የመርየም ልጅ ነው ይላል፡፡

2ኛ ዶክቲስትስቶች 1ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበሩ ሲሆኑ ኢየሱስ በፍፁም አልሞተም ብለዋል ቁርአንም በአል-ኢሳዕ 156-158 ይህንኑ የመርየምን ልጅ ኢሳን አልገደሉትም አልሰቀሉትም በማለት ጽፏል፡፡

3ኛ ሞኖፊስተስ እና ኮሎሪዲያን /ሚሪዬሊትሪ ተብለውም ይታወቃሉ/ የተባለው ቡድን በ4ኛው ክፍለ ዘመን ስለ ማርያም አብዝተው ስለሚያትቱ ማርያምን እንደ ስላሴ አካል አድርገው የሚያምኑ ነበሩ፡፡ ቁርአንም በአል-ማኢዲህ 116-117 እኔ እና እናቴን ከአላህ ሌላ አምላኮች አድርጋችሁ ያዙ ብለሀልን? ተብሎ የተጠቀሰው ከእነዚህ ጋር የሚሄድ ነው፡፡ እንዲሁም፣

4ኛ ኒስቶሪያንስ የተባለው ክፍል ደግሞ በ5ኛው ክፍለ ዘመን ኢየሱስ በእግዚአብሔር የተመረጠ ብቻ ነው ብለው መለኮታዊነቱን ክደው የሚያምኑ ነበሩ፡፡ ይህንንም ሐሳብ ቁርአን በአሊ-ኢምራን 42-48፣ 59፣ በአል-ኢሣዕ 171፣ በአል-ማአኢዳህ 116-117፣ እንዲሁም በመርየም 3ዐ 34-35 ከጠቀሰው ጋር ተመሣሣይ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

ከመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢታዊና እውነተኛ የወንጌል ቃል በመፃረር በአፈንጋጭነትና በስህተት ከሚታወቁት፣ መለኮታዊነት ከሌላቸው ምንጮች ጋር ቁርአን ስለምን ተመሳሳይ ሆነ? ይልቁንም ቁርአን እራሱ መጠየቅ አለበት፣ ምሁራኑም ሆኑ ተከታዮቹም በእውነተኛ አዕምሮ ሊመረምሩት ይገባል እንላለን፡፡

ስለ መርየም መመልከትን ብንቀጥል የቁርአንዋ መርየም የአሮን እህት እንደሆነች ቁርአን ይናገራል፡፡ የመጽሐፍ ቅዱሷ የኢየሱስ እናት ብፅዕት የተባለችውና በእግዚአብሔር የተመረጠችው ማርያም አሮን የተባለ ወንድም እንዳላት አይታወቅም፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ የተጠቀሰው አሮንም በብሉይ ኪዳን የጌታ ኢየሱስ እናት ማርያም ከኖረችበት ዘመን በጣም በጣም በራቀ ዘመን የነበረ ነው፡፡ በአሊ-ኢምራን 35-37 የኢምራን ታሪክ ባለበት /ሃና/ ዘካርያ፣ የማርያም አሳዳጊ፣ የሚለውን ክፍል አንብቡት፡፡ ይህ ታሪክ በቀጥታ ቃል በቃል በማለት በሚያስደፍር ሁኔታ የተቀዳው /The proto-evengelion’s James the lesser/ (ፕሮቶ ኢቫንጀቢያን ጀምስ ዘ ሌሰር) ከተባለው የ2ኛው ክፍለ ዘመን ክርስቲያን የተረት ጽሑፍ ላይ ነው፡፡

ቀደም ሲል በሌሎችም መልእክቶች የተነገረውም የመርየምና የቴምር ዛፍ ትርካ ምንጭ፣ ማለትም መርየም 22-26 በ2ኛ ክፍለ ዘመን የክርስቲያን ተረት (the lost Books of the Bible. New York. ህትመት 1970 ገጽ 38 እንዲሁም Gospel of the Infancy of Jesus Christ ምዕራፍ 24) የተገለበጠ መሆኑን መመልከት ይቻላል፡፡

በተጨማሪም መርየም 29-33 ‹ኢሳ› በዕቅፍ እያለ ማውራቱን ሰው በትክክል በሚረዳው ቋንቋ መናገሩን የአላህ ባሪያ ነኝ፣ ነቢይ አድርጐኛል፣ መጽሐፍ ሰጥቶኛል፣ ብሩክ አድርጐኛል፣ ሶላትን በመስገድ፣ ዘካንም በመስጠት አዞኛል፣ ለእናቴ ታዛዥ አድርጐኛል፣ ትዕቢተኛና እንቢተኛ አላደረገኝም እንዳለ ይተርካል፡፡

በመጽሐፍ ቅድስ የኢየሱስ የውልደቱንና ከ12 ዓመት ጀምሮ በቤተ መቅደስ ያደረገውን እንጂ ይህንን የቁርአን ትርካ አናገኝም፡፡ ይህንን ታሪክ እንዳለ የምናገኘው (the first Gospel of the Infancy of Jesus Christ (Chap.24) በሚለው መጽሐፍ ነው፡፡ የተጻፈውም በ5ኛው ክፍለ ዘመን እንጂ በቁርአን ዘመን አይደለም፣ (በመገለጥም የመጣ አይደለም) ለነገሩም እሱም ቢሆን እውነተኛ አይደለም፡፡

ቁርአን መርየምን የኢምራን ልጅ ይላታል፣ ምንጩ ግን ምንድነው? በአል-ተሃሪም 12 በጣሃ 3ዐ የኢምራን ልጅ መርየምን ይጠቅማል ሙሳ፣ ሃሩንን ወንድሜ እያለ የተናገረውን ጽፏል፡፡ በመጀመሪያ ‹የኢሳ› እናት መርየምና የአሮን እህት ማርያም ሁለት የተለያዩ ሰዎች ናቸው ደግሞም የ157ዐ ዓመታት የእድሜ ልዩነት አላቸው፡፡ ማርያምና አሮን የነበሩት ከክርስቶስ ልደት በፊት በ14ዐዐ ዓመት ነው፡፡ ቁርአን በኢየሱስ ዘመን አልነበረም፡፡ ባይኖርም እውነት ካለው እንቀበላለን ነገር ግን የሚያቀርበው መረጃ ሁሉ ተዛብቷል ጥያቄችንን አጠንክረን ስንሔድ ደግሞ የሙስሊም ሊቃውንት ማርያም የአሮን ዘር ነች ወደማለት ይመጣሉ፡፡ በሉቃስ ወንጌል 3.23 ማርያም የኤሊ እንጂ የአሮን ትውልድ እንደሆነች አይነግረንም፡፡ (ስለዚህ የአሮን ዘር ነች የሚለውም የሊቃውንቱ አዲስ ገለጣም አያስኬድም)፡፡

በመሆኑም እነዚህ የቁርአን ታሪኮች በሙሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ያለውን እውነት የሚደግሙ እንዳይደሉ አውቀናል፡፡ ስለዚህም ቁርአን ከመጽሐፍ ቅዱስ የተለየ መጽሐፍ ነው፣ ወይስ ተሳስቷልና መታረም ይገባዋል? ይሉን ይሆን?!

ቁርአን ለዚህ ዓይነት ልዩነት የተጋለጠው ከ2ኛው እስከ 5ኛ መቶ ክፍለ ዘመን ከተጻፉት 'Infancy of Jesus’ የተባሉትን የሶሪያ ክርስቲያን ጽሑፎች ለመረጃ መጠቀሙ እንዳልቀረ መገመት ብቻ ሳይሆን ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ እነዚህ ደግሞ ከክርስቲያን ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ጋር ክርክር የተነሳባቸው አዋልድ መጽሐፍቶች ጋር የሚጨመሩ ናቸው፡፡ የተገኙበት አካባቢም ምሥራቅ ሶሪያ ሲሆን፣ በወንጌላውያን ቤተክርስቲያናት ተቀባይነትን ያላገኙ እስከዛሬም ድረስ አዋያይ ሆነው ያሉ ጽሑፎች ናቸው፡፡

ለመሆኑ የቁርአኑ ‹ኢሳ›፣ አል-መሲሁ የተባለው ስለምንድነው? የሚለውም ጥያቄ ሌላው አነጋጋሪ ጉዳይ ነው፡፡ በቁርአን ከአስራ አንድ ጊዜ በላይ መሲህ የሚል ቃል ተጽፎ እናገኝለን ይህም ‹ኢሳ› መሲህ እንደሆነ የሚያስረዳ ነው፡፡ ‹ኢሳ› ኢየሱስ ከሆነ በቁርአን አል-መሲህ ሲባል ምን ማለቱ ይሆን? ብለን መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ መጠሪያው ‹ለኢሳ› ብቻ ከመሰጠቱም ሌላ የሙስሊም ሊቃውንት ለዚህ ጥያቄ የሚሰጡት መልስ የላቸውም፡፡

የቁርአን ሊቃውንት ናቸውና ቁርአናቸው በዩኑስ 94፣ በአል-አንቢያ 7፣ በአል-አንከቡት 46 እንዲሁም በአል-ኢሣዕ 136 የሚያዛቸው መልስ ለማግኘት ወደ ክርስቲያኖች መምጣት ወይም መጽሐፍ ቅዱስን መመርመር እንዳለባቸው ነው፡፡ እኛም እርግጡ ምን እንደሆነ እንነግራቸዋለን፡፡ እኛም የምንናገረው ልብወለድን ሳይሆን መጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን ብቻ ነው፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስተምረን አይሁድ ለዘመናት መሲሁን ይጠባበቁ ነበር፡፡ መሲህ በዕብራይስጥ ቋንቋ የተቀባ ማለት ሲሆን ክርስቶስ ከሚለው የግሪኩ ቃል ጋር ትርጉሙ አንድ ነው፡፡

አይሁድ መሲሁ ሲመጣ ያልተቀበሉት ምክንያት እሱ በምድር ላይ የተወሰነ ኃላፊነት እንዳለው ንጉስ አድርገው በመጠበቃቸውና ልክ በብሉይ ኪዳን ትምህርት መሠረት እንደሚያውቋቸው ነቢያት በመጠበቃቸው ነበር፡፡ እውነተኛው መሲህ፣ (እራሱ እግዚአብሔር በሰው አካል ስጋ ለብሶ እና ዝቅ ብሎ) በመካከላቸው እንደሚገለጥ የቀደመው ኪዳን እንደሚያስተምር በፍፁም አልተረዱትም፡፡ መሲህ በእግዚአብሔር የተቀባ እንደሆነ እንረዳለን፣ ኢሳያስ 11.1-5 እና 53.4-6 የተነገረበት በአዲስ ክዳን ደግሞ በገላትያ 4፡4-5 ላይ ተገልጧል፡፡ እርግጥ ነው ሙስሊሞች ይህንን የተለየ እንደሆነ በመናገር ይህንን የሚያስረዳ እውነት ለመቀበል ይቅርና መስማትም አንፈልግም ይላሉ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በእግዚአብሔር የተቀባው እኛ የሰው ልጆች ከገባንበት ኃጢአት ለማውጣት ነው፡፡ ተመልከቱ የመሲሁ የኢየሱስ ስም ሥልጣን ሁሉን ወደ ገሃድ ያወጣ ነው፡፡

በኢየሱስ ክርስቶስ በመሲሁ በተቀባው በኢየሱስ ስም አጋንንት ይወጣል፣ ደዌም ይፈወሳል፣ ህሙማን ይድናሉ፣ ሽባዎች ይነሳሉ፣ አንካሶች ይዘልላሉ፡፡ ሌላም፣ ሌላም፣ ይህ የቅባት ትርጉም መታወቅ አለበት፡፡ በቁርአን ‹ኢሳ› ተብሎ የተጠራው የመጽሐፍ ቅዱሱ ኢየሱስ ከሆነ፣ እንኳን ከመሐመድ ቀጥሎ የሚደረግ ነቢይ ሊባል ይቅርና ሰው ብቻ ከሆነ ከማንም ነቢይ ጋር ሊወዳደር በፍፁም አይገባውም፡፡ ኢየሱስ ጌታ ነው፣ ኢየሱስ የጌቶች ጌታ ነው፣ በሰማይም ቢሆን በምድርም ቢሆን ሥልጣኑ ከማንም የላቀ ነው፡፡ እርሱ የሰላም አለቃ ነው፡፡ ‹እኔ የምሰጠው ሰላም ዓለም እንደሚሰጠው አይደለም› በማለት የተናገረው፣ ደግሞም ይህንን ሰላም ለብዙ ሚሊዮኖች ሰጥቶ ያሳየው፣ እሱ ብቻ ነው፡፡ ቁርአንም እንዳረጋገጠው በመጨረሻው ዘመን ሰላምን ያሰፍናል ያለውም ለዚህ አይመስላችሁምን? ነው እንጂ፡፡

በሙስሊሟ አገር በሞሮኮ ንጉሳቸውን መሲህ ብለው ይጠሩታል፡፡ ለምን ይመስላችኋል?  የንግስናውን ታላቅነት ለመግለጥ ነው፡፡ እዚህ ላይ አንድ ጉዳይ ማስታወስ እንወዳለን፡፡ ስለ ኢየሱስ መወለድ፣ ሩህ-አላህ በመርየም ውስጥ እፍ አለባት የሚለውን ሐሳብ በ923 የነበረው አል-ታብሪ የተባለው የእስላም ሊቅ ሲተረጉም ‹እፍ አለባት› የሚለውን በምሳሌ ሲያስረዳ - ‹በሰው ልብስና በገላው ክፍተት እንደሚነፍስ ነፋስ ነው› ብሏል፡፡ ይሁን እንጂ ይህንን እውነታ እንኳን አምኖ ለመቀበል ይቅርና ለማስረዳትም ግራ የገባቸው ይመስላል፡፡ እናም መለኮታዊ ጉዳይን ከምድራዊ አስተሳሰብ ጋር ማደበላለቅ አይጠቅምም እንላለን፡፡

ወደ ክፍል ሁለት ይቀጥሉ።

 

Jesus of the Bible and Issa of the Quran, Jay Smith

ለእስልምና መልስ አማርኛ  ዋናው ገጽ