መሐመድ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ?
ለመጽሐፍ ቅዱሳዊ ትንቢት ሙስሊሞች ለሚያቀርቡት ጥያቄ ትንተና
በ David Wood
ትርጉምና ቅንብር በአዘጋጁ
ብዙ ሙስሊሞች እንደሚሉት ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መሐመድ በሚናገሩ ትንቢቶች የተሞላ ነው፡፡ የክርስትያን ዓቃቤ እምነታዊዎች ግን እነዚህን ነገሮች በመቃወም ብዙ ጊዜዎችን አሳልፈዋል፡፡ የሚከተለው ዘገባ (ማለትም ይህ ጽሑፍ) እንደሚያሳየው ግን መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መሐመድ ግልፅ የሆኑ ማስረጃዎችን የያዘ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ሙስሊሞች እስልምናን የሚደግፍ ትንቢት የመፈለግ ጥረታቸው መላቅጡ የጠፋበት ሆኗል፣ በውጤቱም የእስልምና እምነት ተከራካሪዎች ስለነቢዩ የተሰጠ የመጽሐፍ ቅዱሳዊ ትክክለኛ ማስረጃ ያለውን ምሳሌ አንድ ጥቅስ እንኳን መስጠት አልቻሉም፡፡ ስለዚህም ቁርአን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድጋፍ እንዳለው ያቀረበውን ጥያቄ በመጠኑ ከተመለከትን በኋላ የማሳየው 1. ሙስሊሞች ይህንን ጥያቄ ለመደገፍ የሚያቀርቧቸው መሰረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ለእስልምና እጅግ በጣም ከፍተኛ ችግር አስከታይ መሆናቸውንና፣ 2. የክርስትያን ተከራካሪዎች እስልምናን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ ምንም ነገር አይናገርም የሚሉት ስህተት መሆኑን ነው፡፡
ቁርአን በግልፅ የሚናገረው ሁለቱም የብሉይ ኪዳንና የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት መሐመድን በተመለከተ ድጋፍ የሚሆን የማስረጃ ጥቅስ እንዳላቸው ነው፡፡ የሚከተሉት የቁርአን ሁለት ጥቅሶች ይህንን በግልጥ ያሳዩናል፡-
‹ለነዚያ ያንን እነሱ ዘንድ በተውራትና በኢንጂል ተጽፎ የሚያገኙትን የማይጽፍና የማያነብ ነቢይ የኾነውን መልእክተኛ የሚከተሉ ለኾኑት (በእርግጥ እጽፋታለሁ) በበጎ ሥራ ያዛቸዋል፤ ከክፉም ነገር ይከለክላቸዋል መልካም ነገሮችንም ለነርሱ ይፈቅድላቸዋል፣ መጥፎ ነገሮችንም በነርሱ ላይ እርም ያደርግባቸዋል፡፡ ከነሱም ላይ ሸክማቸውንና እነዚያንም በነሱ ላይ የነበሩትን እንዛዝላዎች (ከባድ ሕግጋቶች) ያነሳላቸዋል እነዚያም በርሱ ያመኑ ያከበሩትም የረዱትም ያንን ከርሱ ጋር የተወረደውን ብርሃን የተከተሉ እነዚያ እነሱ የሚድኑ ናቸው›፡፡ ቁርአን 7.157፡፡
‹የመርየም ልጅ ዒሳም፡- የእስራኤል ልጆች ሆይ እኔ ከተውራት በፊቴ ያለውን የማረጋግጥና ከኔ በኋላ በሚመጣው መልክተኛ ስሙ አሕመድ በኾነው የማበስር ስኾን ወደናንተ (የተላክሁ) የአላህ መልክተኛ ነኝ ባለ ጊዜ (አስታውስ) በግልጽ ታምራቶች በመጣቸውም ጊዜ ይህ ግልጽ ድግምት ነው አሉ፡፡› ቁርአን 61.6
በተመሳሳይም ሁኔታ የቀደሙት የሙስሊም ጽሑፎች የሚያመለክቱት መጽሐፍ ቅዱስ ስለመሐመድ ብዙ ትንቢቶች እንዳሉት በመጠቆም ነው፡፡
አታ ኢብን ያሳር እንደተረከው፡- ‹እኔ አብዱላህ ቢን ኡማር ቢን አምር ቢን አል-አስን አገኘሁትና የሚከተለውን ጠየቅሁት፡- ‹ስለ አላህ ሐዋርያ (የአላህ በረከትና ሰላም በእሱ ላይ ይሁን) በቶራህ (በብሉይ ኪዳን) የተጠቀሰውን መግለጫ ንገረኝ፣› እርሱም ሲመልስ፡- ‹አዎን በአላህ በብሉይ ኪዳን ውስጥ በቁርአን በተገለጡት አንዳንድ የእሱ ባህርያት ተገልጧል› አለኝ፡፡ Sahih Al-Bukhari, Dr. Muhammad Matraji, tr. (New Delhi: Islamic Book Service, 2002), Number 2125.
የአብዱላ ቢን ሳላም፣ የተማረው ራባይን (የአይሁድ አስተማሪ) ታሪክ ከቤተሰቦቹ በአንዱ ተነግሮኝ ነበር፡፡ እርሱም ያለው፡- ‹ስለ ሐዋርያው በሰማሁበት ጊዜ በመግለጫው ስም አወቅሁኝ፣ እንዲሁም እርሱ የተገለጠበት ጊዜ እኛ (አይሁዶች) የምንጠብቀው እርሱ እንደሆነ አወቅሁኝ፣ በእርሱም እኔ በጣም ደስ ተሰኘሁኝ፣ ... ከዚያም ወጥቼ እንደሚከተለው አልኩኝ፡ ‹ኦ አይሁዶች እግዚአብሔርን ፍሩ እና የላከላችሁንም ተቀበሉ፡፡ በጌታም እናንተ እርሱ የእግዚአብሔር ሐዋርያ መሆኑን ታውቃላችሁ፡፡ እርሱንም በቶራችሁ ውስጥ ተገልጦ ስሙም እንኳን ሳይቀር ተገልጦ ታገኙታላችሁ፡፡› Ibn Ishaq, Sirat Rasul Allah (The Life of Muhammad), A. Guillaume, tr. (New York: Oxford University Press, 1980), pp. 240-241.
የማርያም ልጅ ኢየሱስ ለተከታዮቹ ከእግዚአብሔር ዘንድ በተቀበለው ወንጌል ውስጥ ስለ እርሱ ማለትም ስለ እግዚአብሔር ሐዋርያ ተገልጧል ተብሎ የተነገረኝ ነገር ቃል የሚከተለው ነው፡፡ ይህም ሐዋርያው ዮሐንስ ወንጌልን በሚጽፍላቸው ጊዜ ከማርያም ልጅ ከኢየሱስ ቃል ኪዳን ለእነሱ ካስቀመጠው ውስጥ የተወሰደ ነው፡ ‹እኔን የሚጠላ ጌታን ይጠላል፡፡ እኔም እነሱ ባሉበት ከእኔ በፊት ማንም ያልሰራውን ሰርቼ ባይሆን ኖሮ እነሱ ኃጢአት ባልሆነባቸውም ነበር ነገር ግን ከአሁን በኋላ እነሱ በትዕቢታቸው ተነፍተዋል (ተሞልተዋል) እንደዚሁም እኔንና ጌታን የሚያሸንፉ እንደሆኑ ያስባሉ፡፡ ነገር ግን በሕጉ ውስጥ ያለው ቃል መፈፀም ይኖርበታል፡፡ ‹እኔንም ያለ ምክንያት ጠልተውኛል› (ያም የለምንም ምክንያት ነው)፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ከእራሱ ስፍራ ወደ እናንተ የሚልከው አፅናኙ በሚመጣበት ጊዜ፣ የእውነት መንፈስ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወጥቶ የሚመጣው እርሱ ስለ እኔ እንዲሁም ስለ እናንተም ይመሰክራል ምክንያቱም እናንተ ከመጀመሪያው ጀምሮ ከእኔ ጋር ነበራችሁና፡፡ ስለዚህም ነገር ይህንን ለእናንተ ተናግሬያለሁኝ እናንተ በጥርጥር ውስጥ እንዳትሆኑ›፡፡ Ibid., pp. 103-104.
ስለዚህም ሄራክሊየስ የሮማን ጦር አዛዦችን (ክርስትያኖች የነበሩትን) በአንድ ክፍል ውስጥ እንዲሰበሰቡና በሩ በጥብቅ እንዲዘጋ አዘዘ፡፡ ከዚያም ከላይኛው ክፍል ወደ ታች ወደ እነሱ ተመልክቶ (እነሱን በጣም ፈርቷቸው ነበርና) እንዲህ አለ፡- ‹ኦ ሮማውያን፣ እኔ እዚህ ያመጣኋችሁ ለመልካም ነገር ነው፡፡ ይህ ሰው (ማለትም መሐመድ) ወደ እርሱ ሃይማኖት እንድሰበሰብ ደብዳቤን ጽፎልኛል፡፡ በእግዚአብሔር እርሱ በመጽሐፋችን ውስጥ የምንጠብቀውና የምናገኘው እውነተኛ ነቢይ ነው፣ ስለዚህም ኑና እርሱን እንከተለው በእርሱም እንመን ስለዚህም በዚህም ዓለም በሚመጣውም ለእኛ መልካም ይሆንልናል፡፡› Ibid., p. 656.
ከዚህ በላይ ባየነው መሠረት መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መሐመድ ግልፅ የሆነን ትንቢት ይናገራል የሚለውን በቁርአንን ውስጥ የተቀመጠውን አባባል በመቀበል ሙስሊሞች ለአስራ አራት መቶ ዓመታት ያህል እነዚህን ትንቢቶች ለማግኘት ጥረትን ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ በመቶ የሚቆጠሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ለዚህ እንደ ምርጫ የሚቀርቡ ቢሆንም፣ አሁን ግን በጣም ጥቂቶች ጥቅሶች ናቸው ስለ መሐመድ ማስረጃ ይሆናሉ ተብለው የሚቀርቡት፡፡ ከእነዚህም በጣት ከሚቆጠሩ ጥቅሶች ውስጥ ሁለቱ በጣም የተለመዱ ናቸው፡፡ እነዚህም አንደኛው ሙሴ እንደኔ ያለ ነቢይ ይነሳል ያለው ትንቢትን እና ሁለተኛው ደግሞ ጌታ ኢየሱስ ይመጣል ብሎ የተነበየው አፅናኝ ናቸው፡፡ እነዚህ በእስልምና በጣም ጠቃሚ የመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃ ተብለው ስለሚወሰዱ እነዚህን ሁለቱን ጥቅሶች እኛ ‹ዋና ትንቢቶች› በማለት እንጠራቸዋለን፡፡ የሚቀሩት ሌሎቹ ጥቅሶች ግን ጠቀሜታቸው ዝቅተኛ ስለሆነ ‹አነስተኛ ትንቢቶች› በማለት እንጠቅሳቸዋለን፡፡
ዋናዎቹ ትንቢቶች
የቁርአን ተንታኝ ዩሱፍ አሊ በቁርአን 7.157 የትንተና ማስታዎሻው ላይ መሐመድ ‹በሕግና በወንጌል ላይ› ተጠቅሷል ስለሚባለው ነገር የሚከተለውን ማስረጃ ሰጥቷል፡-
በዚህ ጥቅስ ሙሴን የመሰለ የአረቢያን መልክተኛ ከአላህ መልክተኞች መካከል የመጨረሻውና ታላቁ እንደሚመጣ ያሳያል፡፡ ስለ እርሱም በሕግና በወንጌል ውስጥ ትንቢቶች ይገኛሉ፡፡ አሁን አይሁዶች እንደተቀበሉት በቶራ ትምህርት ውስጥ ሙሴ የተናገረው፡- ‹አምላክህን እግዚአብሔርን በኮሬብ ስብሰባ ተደርጎ በነበረበት ቀን። እንዳልሞት የአምላኬን የእግዚአብሔርን ድምፅ ደግሞ አልስማ፥ ይህችን ታላቅ እሳት ደግሞ አልይ ብለህ እንደ ለመንኸው ሁሉ፥ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ መካከል ከወንድሞችህ እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሣልሃል፤ እርሱንም ታደምጣለህ።› ዘዳግም 18.15 ነው፡፡ ሻሪያን ወይንም ሕግን እንደሙሴ ያመጣ ብቸኛ ነቢይ መሐመድ አል ሙስታፋ ነው እርሱም የመጣው ከእስማኤል ቤት ከይስሐቅ ወንድም ከእስራኤል አባት ቤት ውስጥ ነው፡፡ በወንጌልም ትምህርት ውስጥ ደግሞ አሁን በክርስትያኖች ተቀባይነት እንዳለው ክርስቶስ ቃል የገባው ሌላ አፅናኝ (ዮሐንስ 14.16) የግሪኩ ፐራክሌት የሚለው ክርስትያኖች መንፈስ ቅዱስን የሚያመለክት ነው በማለት የሚተረጉሙት ሲሆን በእኛ ዶክተሮች ግን ፐሪክላይት ተብሎ የሚወሰደውና ከግሪኩ ሲወሰድም አህመድ ማለት ነው፡፡ Yusuf Ali, Note 1127. (አሊ እንደሌሎቹ ብዙ የሙስሊም ተንታኞች የግሪኩ ፐራክቶስ (አፅናኝ፣ እረዳት፣ እና መካሪ) መነበብ ያለበት ፐራክላይቶስ ተብሎ ነው (ይህም አሕመድ ለሚለው የግሪክ አባባል ነውና በማለት ነው)፡ ይሁን እንጂ ከ5000 በላይ የሆኑ የዮሐንስ ወንጌል የግሪክ ጥንታዊ ኮፒዎች የሚገኙ ሲሆን አንዳቸውም እንኳን ከአሊ አባባል ጋር አይስማሙም፡፡ የሙስሊም አቃቤ እምነታውያን ያላስተዋሉት ነገር አንድ ነገር ሲባል ማስረጃ የመስጠት አስፈላጊ መሆኑን ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህም ጥቅሱ ፐራክላይቶስ ነው የሚለው ለሚለው አባባል በአጭሩ ምንም የማስረጃ ድጋፍ የለም፡፡)
ስለዚህም በዚህ ጉዳይ ላይ ቁርአን ተቀባይነት እንዲኖረው ለማስረዳት፣ አሊ ያቀረበው ከብሉይ ኪዳን ላይ አንዲት ትንቢትን እንዲሁም ደግሞ ከአዲስ ኪዳን ላይ ደግሞ ሌላ አንድ ትንቢትን ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ላይ ለተመሰረተው ክርክር እነዚህ ሁለቱ ትንቢቶች አንድ ላይ ሆነው የሚሰጡት ነገር ቢኖር (ተከራካሪዎቹን የሚያሳፍር) ‹ተከታታይ ጡጫ› (ወይንም ተከታታይ ምት) ነው፡፡ ሆኖም ግን ሙስሊሞች ከእስላማዊው ትርጓሜያቸው ጋር እንዲስማማ እነዚህን ሁለቱንም ትንቢቶች ከዓውዳቸው ውስጥ ቆርጠው ማውጣት ይኖርባቸዋል፡፡ (ለዚህ ነው እስላማዊ ጽሑፎችና ትራክቶች አንድ አንቀፅን እንዳለ የማይጠቅሱት፣ ይህንን የሚያደርጉ ከሆነ ዓውዱ ግልፅ ይሆንና ክርክራቸው ይወድቃልና)፡፡ ነገር ግን ጥንቃቄ የተሞላበት ምርመራ ስለ እነዚህ ክፍሎች ያለውን እውነታ ግልጥ ያደርገዋል፡፡
ዋና ዋና ትንቢቶች በማለት ከሰየምናቸው መካከል አንደኛው ከዘዳግም ነው የመጣው፣ ይህም ሙሴ ሌላ ነቢይ ይነሳል በማለት ትንቢት የተናገረበት ነው፡-
‹አምላክህን እግዚአብሔርን በኮሬብ ስብሰባ ተደርጎ በነበረበት ቀን። እንዳልሞት የአምላኬን የእግዚአብሔርን ድምፅ ደግሞ አልስማ፥ ይህችን ታላቅ እሳት ደግሞ አልይ ብለህ እንደ ለመንኸው ሁሉ፥ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ መካከል ከወንድሞችህ እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሣልሃል፤ እርሱንም ታደምጣለህ። እግዚአብሔርም አለኝ። የተናገሩት መልካም ነው፤ ከወንድሞቻቸው መካከል እንደ አንተ ያለ ነቢይ አስነሣላቸዋለሁ፤ ቃሌንም በአፉ አደርጋለሁ፥ ያዘዝሁትንም ቃል ሁሉ ይነግራቸዋል፤ በስሜም የሚናገረውን ቃሌን የማይሰማውን ሰው እኔ እበቀልለታለሁ› ዘዳግም 18.15-19፡፡
ሙስሊሞች የሚከራከሩት ይህ ትንቢት ሊፈፀም የቻለው በመሐመድ ብቻ ነው በማለት ነው፡፡ እንደ ሙሴ ሕግ ሰጪ፣ ነቢይ እና የጦር መሪ በነበረው በመሐመድ ነው ይላሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ይህ ነቢይ መምጣት የነበረበት ከእስራኤላውያን ወንድሞች መካከል ነበር፣ ይህም ማሳየት ያለበት ለእስማኤላውያን መሆን አለበት (የመሐመድ አባቶች በሚባሉት፣) እስማኤል የእስራኤል አባት ይስሐቅ ወንድም ነውና ይላሉ፡፡ እነዚህ እውነታዎች በመሐመድና በሙሴ መካከል ካሉት ከሌሎቹ መመሳሰሎች ጋር የሚደግፉት ነቢይ ተብሎ የተጠቀሰውን መሐመድን ነው በማለት ለማቅረብ ይጥራሉ፡፡
የሌላውን የመጽሐፉን ሐሳብ ሙሉ ለሙሉ ዘግተን ዘዳግም 18.15 በራሱ ብቻ የምንወስድ ብንሆን ኖሮ ከሙስሊም ተከራካሪዎች ጋር በዚህ ጉዳይ ልንስማማ የምንችልበት አንዳንድ ምክንያቶች ይኖሩን ነበር፡፡ ነገር ግን በዓውዱ ላይ ፈጣን ምርመራ እንኳን ቢደረግ ይህ ትንቢት የእስላሞችን አቋም እጅግ ስህተት እንዳለበት የሚያስረዳ ነው፡፡
በመጀመሪያ፡- ክፍሉ የሚናረው እርሱ እንደ ሙሴ ያለ ነቢይን እንደሚያስነሳ ነው፣ ምክንያቱም እስራኤላውያን ከእግዚአብሔር ጋር በቀጥታ ለመነጋገር ስላልፈለጉ ነው፡፡ እስራኤላውያንም አሉ፡- ‹እንዳልሞት የአምላኬን የእግዚአብሔርን ድምፅ ደግሞ አልስማ፥ ይህችን ታላቅ እሳት ደግሞ አልይ ብለህ እንደ ለመንኸው ሁሉ፥› በለመኑት መሠረት እግዚአብሔር ደግሞ ሲመልስ፡- ‹ከአንተ መካከል ከወንድሞችህ እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሣልሃል፤› በማለት ነው፡፡ የምንመለከተው ነገር አይሁዶች ለአማላጅ ወይንም ለመካከለኛ ጥያቄን እንዳቀረቡ ነበር፣ ይህም እራሱ ሙሴ በእነሱና በእግዚአብሔር መካከል እንዲቆም ነበር፡፡ ስለዚህም የዚህ ቃል ዘለቄታዊ ፍፃሜ የሚሆነው አንድ ሰው በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ለዘላለም የሚቆም ሰው ከመጣ ነው፣ ይህም እንደ አማላጅ የሚሆን ሰው ነው፡፡ መሐመድ እንደ አንድ ዓይነት መካከለኛ የሆነ ነገር ነው ተብሎ ሊቆጠር ቢቻልም እንኳን (እንደ ሙስሊሞች) ይህ ክፍል ግን በትክክል ያለምንም ችግር ሊሟላ የሚችለው ለነቢዩ ለጌታ ኢየሱስ ብቻ ከሆነ ነው፡፡ አንድ ሰው ከቁርአን ተነስቶ መሐመድ በማስተላለፉ ሰንሰለት (ሂደት) ውስጥ ነበር በማለት ሊከራከር ይችላል፡፡ ይህም ከአላህ ወደ ገብርኤል፣ ከገብርኤል ወደ መሐመድ፣ ከመሐመድ ወደ ሰው ልጆች ሰንሰለት ውስጥ በማለት መከራከር ይችላል፡፡ ነገር ግን ይህ አባባል በዘዳግም ላይ የተሰጠውን ትንቢት አያሟላውም፡፡ ሙስሊሞች በዘዳግም 18 ላይ እንዳለው መካከለኛነት አይነት መኖር አያምኑምና፡፡ በክርስትና ግን፣ ኢየሱስ ቋሚ የሆነ አማላጅ ነው፡፡ ‹አንድ እግዚአብሔር አለና፥ በእግዚአብሔርና በሰውም መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ፥ እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤› 1ጢሞቲዎስ 2.5፡፡
ቀጥሎም፡- ሙሴ የተናገረው እግዚአብሔር ‹እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሣልሃል፤› አለና ግን - በመቀጠል ‹ከአንተ መካከል ከወንድሞችህ› በማለት ነው፡፡ እርሱ ለእስራኤላውያን ይናገር ስለነበር ነገሩ የሚመስለውም እርሱ ከእስራኤላውያን መካከል ነቢይን እንደሚያስነሳ ነው፡፡ በምንም ዓይነት መንገድ መሐመድ ከአይሁዶች መካከል በእርግጥ አልተነሳም፡፡ ኢየሱስ በሌላው ጎኑ የተወለደውና ያደገው በእስራኤል ውስጥ ነው ስለዚህም ዓውዱ በትክክል የሚያሳየው ሙሴ የተናገረው ስለ ኢየሱስ ነው ለሚለውን ነው፡፡
ሦስተኛ፡- ምንም እንኳን ሙስሊሞች ‹ወንድሞች› የሚለው ቃል የሚያመለክተው ለእስማኤላውያን ነው በማለት ብዙ ጊዜ ቢናገሩም፣ የዘዳግም መጽሐፍ የሚያመለክተው ግን ይህ የሙስሊሞች አባባል ሙሉ በሙሉ ስህተት መሆኑን ነው፡፡ በእርግጥ ‹ወንድሞች› የሚለው ቃል ከአይሁድ ውጭ ያሉትን ሕዝቦችም ለመጥቀስ ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል፣ በዚህም መንገድ ለኤዶማውያን በዘዳግም 2.4 ላይ አገልግሏል፡፡ ይሁን እንጂ ‹ወንድሞች› የሚለው ቃል በጣም ብዙውን ጊዜ ጥቅም ላይ ይውል የነበረው ሌሎች እስራኤላውያንን በመጥቅስ ነበር፡-
‹አምላክህ እግዚአብሔር በሰጠህ በአገርህ ደጅ ውስጥ ከሚኖሩ ከወንድሞችህ አንዱ ቢደኸይ፥ ልብህን አታጽና፥ በድሀው ወንድምህ ላይ እጅህን አትጨብጥ።› ዘዳግም 15.7፡፡
ይህ ጥቅስ ከተከተሉት ጥቅሶች የሚያሳየው እና ግልፅ የሆነው የሚናገረው ስለ ሌላው እስራኤላዊ ነው ምክንያቱም ሙሴ ለአዳማጮቹ የሚናገረው ነገር የዕዳ መሰረዣው ዘመን በሚመጣበት ጊዜ በዚያ የተነሳ ወንድሞቻቸውን ችላ እንዳይሉ ነበር (የዕዳ መሰረዣው ዘመን የነበረው ለአብረው ላሉት እስራኤላውያን ነበርና)፡፡
‹ወንድሞች› የሚለውም በተጨማሪ ያገለግል የነበረው ንጉስንም ለመምረጥ ነበር፡፡ ‹አምላክህ እግዚአብሔር ወደሚሰጥህ ምድር በገባህ፥ በወረስሃትም ጊዜ፥ በተቀመጥህባትም ጊዜ። በዙሪያዬ እንዳሉት አሕዛብ ሁሉ በላዬ ንጉሥ አነግሣለሁ ስትል፥ አምላክህ እግዚአብሔር የመረጠውን በላይህ ታነግሣለህ፤ ከወንድሞችህ መካከል የሆነውን በአንተ ላይ ንጉሥ ታነግሣለህ፤ ወንድምህ ያልሆነውን ከሌላ ወገን ሰው በላይህ ንጉሥ ታደርግ ዘንድ አይገባህም።› ዘዳግም 17.14-15፡፡
እዚህ ላይ አይሁዶች እየታዘዙ ያሉት የአረብን ንጉስ እንዲፈልጉ አልነበረም፡፡ ነገር ግን እየታዘዙ ያሉት ‹ከወንድሞቻቸው› መካከል ንጉስን እንዲሾሙ ነበር፣ ማለትም ከራሳቸው ከአይሁዶች መካከል ነው፡፡ ስለዚህም ‹ወንድሞች› የሚለው ቃል ለሌሎች እስራኤላውያን ነበር እንደዚሁም በዘዳግም 18 ላይ ይህ ትንቢት ከተወሰደበት ላይ ያመለክት የነበረው፡፡ ‹ለሌዋውያን ካህናት፥ ለሌዊም ነገድ ሁሉ ከእስራኤል ጋር ድርሻና ርስት አይሆንላቸውም፤ በእሳት ለእግዚአብሔር የሚቀርበውን መሥዋዕቱንና ርስቱን ይበላሉ። በወንድሞቻቸውም መካከል ርስት አይሆንላቸውም፤ እርሱ እንደተናገራቸው ርስታቸው እግዚአብሔር ነው።› ዘዳግም 18.1-2፡፡
ሌዋውያን በወንድሞቻቸው (በሌሎቹ የእስራኤል ነገዶች) መካከል ምንም እርስት እንዳይኖራቸው የሚናገር ነው፣ እንግዲህ ምዕራፍ 18 የሚጀምረው እንዲህ በማለት ነው፡፡ ስለዚህም ‹ወንድሞች› የሚለው ቃል በቁጥር 15 ላይ ደርሶ ትርጉምን እንደሚለውጥና ስለ እስማኤላውያንን እንደሚናገር የሚያሳይ ምንም ነገር እስካሁን እንደማስረጃ (ጥቆማ) አልተሰጠንም፡፡ ስለዚህም የዚህን ‹ወንድሞች› የሚለውን ቃል ተደጋጋሚ አጠቃቀም ካየን እንዲሁም የሚናገረው ስለ እስራኤላዊ መሆኑን ካየን፣ የሙስሊም ተከራካሪዎች የሚያቀርቡት የዚህ ቃል ትርጉም ሊሆን የሚችለው ‹እስማኤላዊ› ብቻ የሚለውን አተረጓጎም መመልከት በጣም የሚረብሽ ነው፡፡ ለምሳሌም ያህል ‹ወንድሞች› ስለሚለው ቃል አህመድ ዲዳት የተናገረውን ተመልከቱ፡-
‹የእስራኤል ልጆች የእስማኤላውያን ወንድሞች ናቸው፡፡ በተመሳሳይም መንገድ መሐመድ ከእስራኤላውያን ወንድሞች መካከል ነው ምክንያቱም እርሱ የእስማኤል ዘር የአብርሃም ልጅ ነውና፡፡ ይህ ደግሞ ትንቢቱ በትክክል እንዳለው ነው፡- ‹ከወንድሞቻችሁ መካከል› ዘዳግም 18.18፡፡ እዚያም ትንቢቱ በግልፅ ያሳየው ሙሴን የሚመስል ነቢይ ይመጣል በማለት የተናገረው ከእስራኤል ሕዝቦች መካከል መነሳት የለበትም ወይንም ከመካከለቸው ከእነሱ መሆን የለበትም ነገር ግን ከእነሱ ወንድሞች መካከል ነው፡፡ ስለዚህም መሐመድ ከእነሱ ወንድሞች መካከል የመጣ ነው፡፡ Ahmad Deedat, What the Bible Says About Muhammad (New Dehli: Islamic Book Service), p. 13.
የሙሴ ትንቢት የሚያሳየው ግን የዲዳትን ተቃራኒ ሐሳብ ነው፣ ትንቢቱም ነቢዩ ከእስራኤል ልጆች መካከል መምጣት የለበትም አይልም፡፡ ‹ወንድሞች› የሚለው ቃል በተደጋጋሚ በዘዳግም ውስጥ እንደሚያሳየው በተለይም በምዕራፍ 18 ላይ ግልፅ እንደሆነው የሚያመለክተው ለእስራኤላውያን ብቻ ነው፡፡ ስለዚህም አንድ ሰው ይህንን በተለየ መልኩ (ከዓውዱ ውጪ) መተርጎሙ አስደናቂ ነው የሚሆነው፡፡ ዲዳት ‹ወንድሞች› የሚለው ቃል በዘዳግም ውስጥ እንዴት አገልግሎት ላይ እንደዋለ ሙሉ ለሙሉ አያውቅም ወይንም የሙስሊም አንባቢዎቹን ሆነ ብሎ ለማሳሳት ተጠቅሞበታል (ይህም የእሱን የማይረባ አጠቃቀም በጥንቃቄ ሊመረምሩ የሚችሉት ጥቂቶች ብቻ ናቸው ብሎ ነው)፡፡
አራተኛ፡- የዘዳግም መጽሐፍ መደምደሚያ ‹እንደኔ ያለ› የሚለውን ሐረግ እንዴት መተርጎም እንዳለብን ይነግረናል፡- ‹ሙሴም እጆቹን ስለ ጫነበት የነዌ ልጅ ኢያሱ የጥበብን መንፈስ ተሞላ፤ የእስራኤልም ልጆች ታዘዙለት፥ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው አደረጉ። እግዚአብሔርን ፊት ለፊት እንዳወቀው እንደ ሙሴ ያለ ነቢይ ከዚያ ወዲህ በእስራኤል ዘንድ አልተነሣም፤ በግብፅ ምድር በፈርዖንና በባሪያዎቹ ሁሉ ላይ በምድሪቱም ሁሉ ላይ ምልክትንና ድንቅን ያደርግ ዘንድ እግዚአብሔር እንደ ላከው ያለ፥ በእስራኤል ሁሉ ፊት በጸናች እጅ ሁሉና በታላቅ ማስደንገጥ ሁሉ እንዳደረገው እንደ ሙሴ ያለ አልተነሣም።› ዘዳግም 34.9-12፡፡
እዚህ ላይ ‹እንደ ሙሴ ያለ› የሚለው ሐረግ የሚያሳየው ከእግዚአብሔር ጋር ፊት ለፊት የሚናገር ነቢይ እና ድንቅና ተዓምራትንም ‹በእስራኤል ልጆች ፊት› ስለሚያደርግ ነቢይ ነው፡፡ መሐመድ ከእነዚህ መስፈርቶች ውስጥ አንዳቸውንም አያሟላም፡፡ እርሱም መገለጡን እንዳገኘ የተናገረው ከገብርኤል ነው፣ ከእግዚአብሔር በቀጥታ አይደለም፣ እርሱም እራሱ እንዳመነው ምንም ተዓምራትንም ማድረግ አልቻለም፡፡ ‹እውነቱም ከእኛ ዘንድ በመጣላቸው ጊዜ ለሙሳ የተሰጠው ብጤ አይሰጠውም ኖሯልን? አሉ፣ ከዚህ በፊት ሙሳ በተሰጠው አልካዱምን? የተረዳዱ ሁለት ድግምቶች ናቸው አሉ፣ እኛ በሁሉም ከሓዲዎች ነንም አሉ፡፡› ቁርአን 28.48፡፡ በዚህም ላይ ኢብን ኢሻቅ የጨመረው፡ ‹‹(መሐመድ አለ)፡ ‹የአቡ ኡማ ሞት ምን ዕድለ ቢስነት ነው! የአይሁድና የአረብ ግብዞች በእርግጥ ማለት አለባቸው ‹‹እርሱ ነቢይ ቢሆን ኖሮ ጓደኛው ባልሞተም ነበር›› በእርግጥ እኔ እራሴንም ሆነ የጓደኛዬን ሞት ለማስቀረት ከእግዚአብሔር የሆነ ምንም ኃይል የለኝም› ገፅ 235፡፡ ይሁን እንጂ ኢየሱስ ተዓምራትን አድርጓል (ቁርአንም እራሱ እንደሚያምነው ቁርአን 3.49 ይመልከቱ) እንዲሁም ከእግዚአብሔር ጋር በቀጥታ ተነጋግሯል፡፡
‹ስለዚህ ኢየሱስ መለሰ እንዲህም አላቸው። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብ ሲያደርግ ያየውን ነው እንጂ ወልድ ከራሱ ሊያደርግ ምንም አይችልም፤ ያ የሚያደርገውን ሁሉ ወልድ ደግሞ ይህን እንዲሁ ያደርጋልና። አብ ወልድን ይወዳልና፥ የሚያደርገውንም ሁሉ ያሳየዋል፤ እናንተም ትደነቁ ዘንድ ከዚህ የሚበልጥ ሥራ ያሳየዋል።› ዮሐንስ 5.19-20፡፡
‹ስለዚህም ኢየሱስ። የሰውን ልጅ ከፍ ከፍ ባደረጋችሁት ጊዜ እኔ እሆን ዘንድ አባቴም እንዳስተማረኝ እነዚህን እናገር ዘንድ እንጂ ከራሴ አንዳች እንዳላደርግ በዚያን ጊዜ ታውቃላችሁ።› ዮሐንስ 8.28፡፡ ‹እኔ ከራሴ አልተናገርሁምና፤ ነገር ግን የላከኝ አብ እርሱ የምለውን የምናገረውንም ትእዛዝ ሰጠኝ።› ዮሐንስ 12.49፡፡ ‹የማይወደኝ ቃሌን አይጠብቅም፤ የምትሰሙትም ቃል የላከኝ የአብ ነው እንጂ የእኔ አይደለም።› ዮሐንስ 14.24፡፡
በመጨረሻም፡- ሙስሊሞች ዘዳግም 18.15-19 ለነቢያቸው ማስረጃነት የሚጠቅሱ ቢሆንም፣ ከዚያ የሚቀጥለውን ጥቅስ በማንበብ መልካምን ያደርጋሉ፣ ይህም ከመሐመድ አንዳንድ አሳፋሪ የሕይወት ታሪኮች ጋር ሲደባለቅ የሚያሳየው ነገር ቢኖር ለእስላም ነቢይ ሐሰተኛነት ማረጋገጫ ሆኖ ነውና፡፡ ስለዚህም በዘዳግም 18.20 ላይ የምናነበው ነገር እግዚአብሔር የተናገረው፡- ‹ነገር ግን ይናገር ዘንድ ያላዘዝሁትን በስሜ በድፍረት የሚናገር ወይም በሌላ አማልክት ስም የሚናገር ነቢይ፥ እርሱ ይገደል።› ዘዳግም 18.20፡፡
እዚህ ላይ እግዚአብሔር የሐሰት ነቢይን የሚያሳዩ ሁለት መስፈርቶችን ሰጥቷል፣ እነዚህም፡- አንደኛ፡- አንድ ሰው ከእግዚአብሔር ያልመጣን መልእክት የሚያስተላልፍ ከሆነ እርሱ የሐሰት ነቢይ ነው፣ እንዲሁም ደግሞ፣ ሁለተኛ፡- አንድ ሰው በሌሎች አማልክት ስም ከተናገረ እርሱ የሐሰት ነቢይ ነው፡፡ በሚያስገርም ሁኔታ፣ መሐመድ ሁለቱንም መስፈርቶች አሟልቷቸዋል፣ እርሱ የታወቁትን ‹ሰይጣናዊ ጥቅሶች› (የቁርአን ክፍል ናቸው በማለት ለተከታዮቹ የሰጣቸውን በኋላ ግን ሰይጣናዊ ወይንም ከሰይጣን የመጡ የተባሉትን ጥቅሶች) የሚባሉትን አስተላልፏልና፡፡ እነዚህ ጥቅሶች ከእግዚአብሔር ባለመምጣታቸው መሐመድ የመጀመሪያውን መስፈርት አሟልቷል፡፡ እንዲሁም ደግሞ እነዚህ ጥቅሶች ፖሊቲዝምን ወይንም የብዙ አማልክትን አምልኮ ስለሚያስተላልፉ መሐመድ ሁለተኛውን መስፈርት አሟልቷል፡፡ ስለዚህም ሙስሊሞች ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ መሐመድ ተናግሯል የሚሉትና የሚጠቅሱት ዋና ክፍል እራሱ በተቃራኒው የሚናገረውና የሚያስረዳው መሐመድ እራሱ በጭራሽ ነቢይ አለመሆኑን ነው፡፡ (ይህንን ሙሉ በሙሉ ለማየት የዘዳግም ትንተናን ዘዳግም 18፣20 መሐመድን ነቢይ አለመሆን እንዴት እንደሚያስረዳ የተጻፈውን ተመልከቱ)፡፡
በእርግጥ ሙሴና መሐመድ ጥቂት መመሳሰል አሏቸው፡፡ ይሁን እንጂ የዘዳግምን ዓውድ በምንመረምርበት ጊዜ የምናገኘው ነገር መመሳሰሎቹ በጣም ጥቂቶች ሆነው ነው፡፡ ሙሴ ለእስራኤላውያን የነገራቸው ሌላ አማላጅ እንደሚላክላቸው ነው በአዲስ ኪዳን ደግሞ የተገለጠው ያ አማላጅ ኢየሱሰ ክርስቶስ ነው እርሱም በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ያለው መካከለኛ ነው፡፡ ሙሴ ለእስራኤላውያን የነገራቸው ከመካከላቸው ነቢይን እንደሚያስነሳላቸው ነው፣ ኢየሱስ በእስራኤል ሲወለድ፣ መሐመድ ግን አሁን ሳውዲ አረቢያ በተባለው ቦታ ነው የተወለደው፡፡ ሙሴ ለእስራኤላውያን የነገራቸው ነገር ‹ከወንድሞቻቸው› መካከል ነቢይን እንደሚልክላቸው ነው፣ ይህም ቃል በተደጋጋሚ ያገለገለው ለእስራኤላውያን ብቻ ነው፣ ኢየሱስ አይሁዳዊ መሐመድ ግን አረብ ነበር፡፡ ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋር በቀጥታ የተነጋገረና እንዲሁም ተዓምራት አድራጊ ነበር ኢየሱስም እንደዚሁ ነበር፣ መሐመድ ግን እንደዚህ አልነበረም፣ ስለዚህም በእነዚህ ሁሉ ነገሮች ውስጥ ማንኛው ነው - እንደሙሴ የነበረው? ከእነዚህ ሁሉ እውነቶች በተጨማሪ ደግሞ ዘዳግም 18.20 መሐመድ በፍፁም ነቢይ ሊሆን እንደማይችል ያሳየናል፡፡
በእርግጥ ሙስሊሞች በዘዳግም 18 ላይ ያለውን ትንቢት ለመሐመድ ነው የሚያገለግለው በማለት ለማመን ነፃ ናቸው፡፡ ነገር ግን ይህ ጥቅስ የመሐመድን ነቢይነት ያስረዳል በማለት ሲያቀርቡ ማስረጃ የመስጠቱ ሐላፊነት በእነሱ ላይ ነው የሚሆነው፡፡ በዘዳግም ላይ ያለው ዋና የነቢይነት ገፀ ባህርይ በቀጥታ የሚያለመለክተው ለኢየሱስ በመሆኑ ሙስሊሞች የቁርአንን አባባል ለመደገፍ የሚያስችላቸው ሌላ ዋና ትንቢት ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መስጠት አስፈልጓቸዋል፡፡
በዚህኛው ነጥብ ላይ ሙስሊሞች የመጡት ወደ ዮሐንስ ወንጌል ላይ ነው፡፡ ይህም ጌታ ኢየሱስ የአፅናኝ መምጣትን አስመልክቶ በተናገረው ትንቢት ላይ ነው፡፡ ‹ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ። እኔም አብን እለምናለሁ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤ እርሱም ዓለም የማያየውና የማያውቀው ስለ ሆነ ሊቀበለው የማይቻለው የእውነት መንፈስ ነው፤ ነገር ግን ከእናንተ ዘንድ ስለሚኖር በውሥጣችሁም ስለሚሆን እናንተ ታውቃላችሁ። ወላጆች እንደ ሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም፤ ወደ እናንተ እመጣለሁ። ዮሐንስ 14.15-18፡፡ ‹ከእናንተ ዘንድ ስኖር ይህን ነግሬአችኋለሁ፤ አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል እኔም የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል። ዮሐንስ 14.25-26፡፡ ‹ዳሩ ግን እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ አጽናኝ እርሱም ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ፥ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል፤ እናንተም ደግሞ ከመጀመሪያ ከእኔ ጋር ኖራችኋልና ትመሰክራላችሁ። ዮሐንስ 15.26-27፡፡
በሚገርም ሁኔታ ሙስሊሞች እነዚህን ጥቅሶች የሚያዩአቸው ስለ መሐመድ መምጣት ትንቢቶች እንደሆኑ አድርገው ነው፡፡ በእርግጥ ስለ አፅናኝ የተነገረባቸውን እነዚህን ሦስት ጥቅሶች በሙሉ ከጠቀሰ በኋላ፣ ሙላና መሐመድ አሊ የያዘው ‹ሁሉም እነዚህ የትንቢት ቃሎች ያለምንም መዛነፍ የሚናገሩት ነገር ከኢየሱስ በኋላ ስለሚመጣ ሌላ ነቢይ ነው›፡፡ የሚልን አቋም ነው፡፡ Maulana Muhammad Ali, Muhammad in the Bible, p. 27.
‹ኢየሱስ ወደ አባት ካልተመለሰ በስተቀር አፅናኙ አይመጣም› የሚለው ይህ ትንቢት ስለ መንፈስ ቅዱስ በፍፁም ሊናገር አይችልም በማለት ሙስሊሞች ይከራከራሉ፡፡ ምክንያቱም መንፈስ ቅዱስ በራሱ በኢየሱስ ውስጥ ስለነበረ ነው ይላሉ፡፡ ስለዚህም ኢየሱስ ይናገር የነበረው ስለ ሌላ ነቢይ መነሳት ወይንም መምጣት ነበረ፣ ስለዚህም (ለተወሰኑ ምክንያቶች) ተመራጭ ሊሆን የሚችለው ነቢይ መሐመድ ብቻ ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት አባባል ደግሞ የዮሐንስ ወንጌልን ለሚያውቅ ሰው እጅግ አስገራሚ ነው የሚሆነው፡፡
በመጀመሪያ ሙስሊሞች ይህንን ትንቢት ወሰድን የሚሉት ከመጀመሪያው ጀምሮ ኢየሱስ አምላክ መሆኑን እና ሁሉን ነገር የፈጠረ ነው ከሚለው መጽሐፍ ማለትም ከዮሐንስ 1.1-3 ላይ ነው፡፡ በዮሐንስ መጽሐፍ ኢየሱስ የተናገረው ከአብርሐም በፊት እርሱ እንደነበረ ነው 8.58፡፡ እንዲሁም እራሱን በሰማይና በምድር መካከል እንዳለ መሰላል አድርጎ ነው 1.51 ይህም በዘፍጥረት 28.10-17 ላይ እንዳለው ነው፡፡ ከዕውርነቱ የተፈወሰው እና ማየትን የተሰጠው ሰው ኢየሱስን አምልኮታል፣ እንዲሁም ቶማስ ኢየሱስን ‹አምላኬና ጌታዬም› ብሎ 20.28 ላይ ጠርቶታል፡፡ ጌታ ኢየሱስ በዚህ ወንጌል ዘገባ ውስጥ ተሰቅሏል፣ ሞቷል፣ እና ደግሞም ተነስቷል፣ እነዚህም ሁሉ ለቁርአን እጅግ ልዩ የሆኑ ወይንም ተቀባይነት የሌላቸው ነገሮች ናቸው፡፡ ከዚህም በላይ በዚያው በተመሳሳይ ምዕራፍ ውስጥ ሙስሊሞች ስለመሐመድ ትንቢት አለበት በማለት በሚጠቅሱት ውስጥ ኢየሱስ እርሱ ብቻ ወደ እግዚአብሔር የሚወስድ መንገድ እንደሆነ ተናግሯል 14.6፣ እርሱን ያየ ማንም ቢኖር አብን እንዳየ ተናግሯል፣ 14.9. እርሱ በአብ ውስጥ አብ ደግሞ በእርሱ ውስጥ እንደሆነም ተናግሯል፣ 14.11፣ እርሱ ፀሎትን እንደሚመልስ ተናግሯል፣ 14.14፡፡ እኛም በእርሱ ውስጥ የማንኖር ከሆነ ምንም ፍሬ ሊኖረን እንደማይችልም ተናግሯል፣ 15.4፡፡ እኛ እንደዚህ እስልምናን በጣም የሚቃወምን መጽሐፍ ሙስሊሞች ለመጥቀሳቸው በጣም እንደነቅ ይሆናል፣ ይሁን እንጂ ማስታወስ ያለብን ነገር መሐመድ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ስለ እርሱ የተነገሩ ትንቢቶች መኖራቸውን ስለመናገሩ መዘንጋት የለብንም፡፡ ስለዚህም ሙስሊሞች የተገደዱት የመሐመድን ትንቢት ወይንም ንግግር ሊደግፍላቸው ወይንም ሊያረጋግጥላቸው ይችላል ተብሎ የሚታሰበውን ማንኛውንም ነገር ሁሉ ለመጨበጥ መገደዳቸውን ነው፡፡
ሁለተኛ፡- በዮሐንስ ውስጥ ያሉት ሦስቱ ክፍሎች አፅናኙን የሚገልፁት መንፈስ ቅዱስ ነው በማለት ለይተው ነው፣ (ወይንም የእውነት መንፈስ) በማለት ነው፡፡ ነገር ግን ሙስሊሞች የሚከራከሩት እነዚህ ጥቅሶች ስለ መንፈስ ቅዱስ በምንም ዓይነት አይናገሩም በማለት ነው፡፡
እነሱ እንደሚሉት የትንቢቱ ቃሎች ለመንፈስ ቅዱስ ነው የሚያገለግሉት በማለት ወደ ድምዳሜ እንድምመጣ አያስችሉንም፡፡ ይሁን እንጂ ‹እኔ ባልሄድ አፅናኙ ወደ እናንተ አይመጣም› የሚሉት ቃላት ምንም መግለጫ የማያስፈልጋቸው በጣም ግልጥ የሆኑ ናቸው፡፡ አዲስ ኪዳን የሚለው መጥምቁ ዮሐንስ ገና ከመወለዱም በፊት በመንፈስ ቅዱስ እንደተሞላ ነው፡፡ ከዚያም ስለ ኢየሱስ ሲናገር እርሱ መንፈስ ቅዱስን በእርግብ መልክ እንደተቀበለ ነው፡፡ ስለዚህም መንፈስ ቅዱስ ከኢየሱስ ጊዜ በፊትና በኢየሱስ ጊዜ ሰዎችን ይጎበኝ እንደነበረ ነው፡፡ በመሆኑም የሙስሊሞች ክርክር ኢየሱስ የተናገረውን ትንቢት ነጥብ ሙሉ ለሙሉ በግልፅ ስቶታል፡፡ ኢየሱስ መንፈስ በእነሱ ውስጥ እንደነበረ ያውቃል ... በእናንተ ይኖራልና፡፡ ትንቢቱ ግን መንፈስ በእነሱ ይኖራል ከእነሱም ጋር ለዘላለም ይኖራል ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሙሉ፤ ለሙሉ አዲስ ነገር ነው፡፡ እናም መንፈስ ቅዱስ በኢየሱስ ውስጥ ስለነበረ ሊሆን አይችልም፣ ትክክልም አይደለም ተብሎ ሊነገር አይቻልም፡፡
ሦስተኛ፡- ከላይ እንዳየነው ሁሉ ጌታ ኢየሱስ የተናገረው አፅናኙ ከደቀመዛምርቱ ጋር ለዘላለም እንደሚሆን ነው፡፡ ስለዚህም መሐመድ ለዘላለም ከእነሱ ጋር መሆንን ቀርቶ ከኢየሱስ ደቀመዛምርት ጋር ሊሆን በምንም ዓይነት መንገድ አይችልም ነበር፡፡
አራተኛ፡- በትንቢቱ መሰረት ዓለም አፅናኙን ሊቀበለው አይቻለውም፣ ምክንያቱም ሊያየው አይቻለውምና፡፡ እጅግ ብዙ ሺ ሰዎች መሐመድን በሕይወት በነበረበት ጊዜ አይተውታል እርሱ ይታይ ነበርና፡፡ ስለዚህም የማይታየው አፅናኝ የሚታየው መሐመድ ሊሆን አይችልም፡፡
አምስተኛ፡- ኢየሱስ ለደቀመዛምርቱ የነገራቸው አፅናኙ አራሱ ከእነሱ ጋር እንደነበረ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ ከኢየሱስ ደቀመዛምርት ጋር የነበረ ሲሆን መሐመድ ግን ከአምስት መቶ ዓመታት በፊት ይህ ትንቢት ከተነገረ በኋላ ነበር የነበረው ስለዚህም ከእነሱ ጋር እርሱ ሊኖር አይችልም ነበር፡፡
ስድስተኛ፡- አፅናኙ በደቀመዛምርቱ ውስጥ መሆን ነበረበት፡፡ መሐመድ በኢየሱስ ደቀመዛምርት ውስጥ አልነበረም እንዲሁም ሊሆንም አይችልም፡፡ መንፈስ ቅዱስ በሌላ ጎኑ ደግሞ አማኞችን በጴንጤ ቆስጤ ቀን ሞላባቸው ከዚያን ጊዜ ጀምሮም በክርስትያኖች ሁሉ ውስጥ ይገኛል፡፡
ሰባተኛ፡- ኢየሱስ የተናገረው እርሱ አፅናኙን ከአብ ዘንድ እንደሚልከው ነው፡፡ ሙስሊሞች መሐመድ በኢየሱስ እንደተላከ አያምኑም እነሱም የሚያምኑት መሐመድ በእግዚአብሔር እንደተላከ ነበር፡፡ ስለዚህም ሙስሊሞች ኢየሱስ እግዚአብሔር ነው በማለት ካላመኑ በስተቀር ይህ ስለ መሐመድ የተነገረ ትንቢት ነው በማለት ሊቀበሉት አይገባቸውም፡፡
በመጨረሻም፡- ከእርገቱ በፊት ኢየሱስ ተከታዮቹ ከጥቂት ቀናት በኋላ በመንፈስ ቅዱስ እንደሚሞሉ ትንቢትን ተናግሮ ነበር ሐዋርያት 1.5፡፡ ወደ አባቱም ከአረገ ከጥቂት ቀናት በኋላ መንፈስ ቅዱስ በኢየሱስ ተከታዮች ላይ መጣ፡፡ ‹በዓለ ኀምሳ የተባለውም ቀን በደረሰ ጊዜ፥ ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው አብረው ሳሉ፥ ድንገት እንደሚነጥቅ ዓውሎ ነፋስ ከሰማይ ድምፅ መጣ፥ ተቀምጠው የነበሩበትንም ቤት ሁሉ ሞላው። እንደ እሳትም የተከፋፈሉ ልሳኖች ታዩአቸው፤ በያንዳንዳቸውም ላይ ተቀመጡባቸው። በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው፥ መንፈስም ይናገሩ ዘንድ እንደ ሰጣቸው በሌላ ልሳኖች ይናገሩ ጀመር።› ሐዋርያት 2.1-4፡፡
ስለዚህም የዚህ ትንቢት ፍፃሜ የሆነው በጥቂት ቀናት ውስጥ ነበር፡፡ መሐመድ ግን የመጣው ከአምስት መቶ ዓመታት በኋላ ነበር፡፡ እነዚህን ነገሮች ሁሉ በአንድ ላይ በማስቀመጥ መሐመድ አፅናኙ ሊሆን እንደማይችል እንመለከታለን፡፡ እርሱ ከደቀመዛምርቱ ጋር አልነበረም፣ እርሱ በሐዋርያቱ ውስጥ አልነበረም፣ እርሱ ከእነርሱ ጋር ለዘላለም አልነበረም፣ እርሱ የማይታይ አልነበረም፣ እርሱ በኢየሱስ አልተላከም ነበር እርሱ (መሐመድ) ጌታ ኢየሱስ እንደተናገረው ከተተነበየ በኋላ ወዲያውኑ አልመጣም ነበር፡፡ እነዚህ ሁሉ እውነታዎች የሚያሳዩት በጌታ ከተተነበየው ትንቢት ጋር ሙሉ ለሙሉ የሚገጥመው መንፈስ ቅዱስ ብቻ መሆኑን ነው፡፡ ኢየሱስ አፅናኙን ለይቶ የተናገረው መንፈስ ቅዱስ ነው በማለት ነው፡፡ እርሱም ከደቀመዛምርቱ ጋር ነበር፣ በጴንጤቆስጤም እለት በእነሱ ውስጥ ነበር እርሱ የማይታይ ነበር፣ የመጣውም በፍጥነት ነበር፡፡ መንፈስ ቅዱስ በጌታ በኢየሱስ ነበር የተላከው፡፡ እንዲሁም ከክርስትያኖች ጋር ለሁለት ሺ ዓመታት አብሮ ነው ያለው፡፡ እነዚህን ነጥቦች ሁሉ ስንመለከት ሙስሊሞች እነዚህ ጥቅሶች ለመሐመድ ነው የሚያመለክቱት በማለት መናገራቸው በእርግጥ እራሳቸውን የሚያሳፍራቸው ነገር መሆን ይኖርበታል፡፡
አነስተኛ ትንቢቶች
ምንም እንኳን በጣም ታዋቂ የሆኑት የሙስሊሞች የማስረጃ ትንቢቶች በጥንቃቄ ሲታዩ ሙሉ ለሙሉ ውድቅ ቢሆኑም፣ ሙስሊም ተከራካሪዎች ስለ መሐመድ ያስረዳሉ የሚሏቸውን በጣም ደካማ የሆኑ ብዙ ትንቢቶችን ሰጥተዋል፡፡ እነሱም በጣም ታዋቂዎች አይደሉም ምክንያቱም በዓውድ ውስጥ ሲታዩ ስለሚመጣ ነቢይ ወይንም ስለ ሌላ ሃይማኖት መነሳት የሚሰጡት ምንም ነገር የላቸውም፡፡ ስለዚህም ሙስሊሞች የራሳቸውን ትርጉም በእነዚህ ትንቢቶች ውስጥ አስገድደው ማስገባት ይኖርባቸዋል፣ ነገር ግን ይህንን የሚያደርጉት የእራሳቸውን ታማኝነት በማበላሸት ነው፡፡
ከዚህ በላይ ከታዩት ትንቢቶች በተጨማሪ ሙላና መሐመድ አሊ ስለ መሐመድ መነሳት ሌሎች ሦስት የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን ጨምሯል፡፡ ነገር ግን በሚያስገርም ሁኔታ እርሱ የጀመረው የመጨረሻውን ነቢይ መምጣት በተመለከተ የተሰጡትን የቁርአንን ጥቅሶች በመጥቀስ ነው፡፡ እናም በመቀጠል የተናገረው በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ ‹መልእክተኛ› የሚለውን አባባል ሊያሟላ የሚችለው መሐመድ ብቻ ነው በማለት ነው፡፡ ስለዚህም ስለ መሐመድ ነቢይነት በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ እንደተነገረ በመሐመድ የተሰጡትን ጥቅሶች ነው አሊ የጠቀሳቸው፡፡
በእንደዚህ ዓይነት ሽክርክሮሻዊ ክርክር ውስጥ ከቆየ በኋላም አሊ የሰጠው ለአብርሃም የተገባውን ቃል ኪዳን ነው (በቅልጥፍናም ስለ እስማኤል የተሰጠውን ኋለኛ የተስፋ ቃልን በማደባለቅ ነው) ይህም ለእስልምና መነሳት እንደመጀመሪያ ትንቢት ተደርጎ ተቆጥሮ ነው፡፡
‹እግዚአብሔርም አብራምን አለው። ከአገርህ ከዘመዶችህም ከአባትህም ቤት ተለይተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ውጣ። ታላቅ ሕዝብም አደርግሃለሁ፥ እባርክሃለሁ፥ ስምህንም አከብረዋለሁ፤ ለበረከትም ሁን፤ የሚባርኩህንም እባርካለሁ፥ የሚረግሙህንም እረግማለሁ፤ የምድር ነገዶችም ሁሉ በአንተ ይባረካሉ።› ዘፍጥረት 12.1-3፡፡ ‹ስለ እስማኤልም ሰምቼሃለሁ፤ እነሆ ባርኬዋለሁ፥ ፍሬያምም አደርገዋለሁ፥ እጅግም አበዛዋለሁ፤ አሥራ ሁለት አለቆችንም ይወልዳል፥ ታላቅ ሕዝብም እንዲሆን አደርገዋለሁ።› ዘፍጥረት 17.20፡፡
አሊ ይህንን የቆጠረው ለቅዱሱ ነቢይ መምጣት የተነገረው የመጀመሪያው ትንቢት ነው በማለት ነው፡፡ ይሁን እንጂ እኔ የመጀመሪያውን ክፍል (እንቀፅ) ስጠቅስ የሁለተኛውን አንቀፅ ልክ በአሊ መጽሐፍ ላይ እንዳለው ትቼዋለሁኝ፡፡ ከዚያ ዙሪያ ያሉትን ጥቅሶች ስንጨምር ምን እንደሚሆን ተመልከቱ፡፡
‹አብርሃምም እግዚአብሔርን። እስማኤል በፊትህ ቢኖር በወደድሁ ነበር አለው። እግዚአብሔርም አለ። በእውነት ሚስትህ ሣራ ወንድ ልጅን ትወልድልሃለች፥ ስሙንም ይስሐቅ ብለህ ትጠራዋለህ፤ ከእርሱ በኋላ ለዘሩ የዘላለም ቃል ኪዳን እንዲሆን ቃል ኪዳኔን ከእርሱ ጋር አቆማለሁ። ስለ እስማኤልም ሰምቼሃለሁ፤ እነሆ ባርኬዋለሁ፥ ፍሬያምም አደርገዋለሁ፥ እጅግም አበዛዋለሁ፤ አሥራ ሁለት አለቆችንም ይወልዳል፥ ታላቅ ሕዝብም እንዲሆን አደርገዋለሁ። ቃል ኪዳኔን ግን በሚመጣው ዓመት በዚሁ ጊዜ ሣራ ከምትወልድልህ ከይስሐቅ ጋር አቆማለሁ። ንግግሩንም ከእርሱ ጋር በፈጸመ ጊዜ እግዚአብሔር ከአብርሃም ተለይቶ ወጣ።› ዘፍጥረት 17.18-22፡፡
ስለዚህም የራሱን ሐሳብ ለመደገፍ አሊ ለአብርሃም እግዚአብሔር የገባውን ቃል ኪዳን ጠቀሰ፣ ከዚያም ስለእስማኤል የተነገረውን ጥቅስ አቀረበ፣ ይህም የተገባው ቃል ኪዳን ለእስማኤልና ለዘሩ ነው (ማለትም ለመሐመድ) በማለት ነው፡፡ ነገር ግን ጥቅሱን በሚጠቅስበት ጊዜ በዙሪያው ያለውን ነገር ሁሉ ትቶና አስቀርቶ ነው ይህም ቃል ኪዳኑ የተደረገው ከእስማኤል ጋር ሳይሆን ከይስሐቅ ጋር መሆኑን የሚያሳየውን ነው፡፡ ይህም ብዙዎች አንባቢዎቹ እርሱ የጠቀሳቸውን ማስረጃዎች ድፍረት አግኝተው ሄደው እንደማያነቡ በማወቅ ነው፣ አሊ ይህንን ጥቅስ ከዓውዱ ውስጥ ነጥሎ ሲያወጣውና በዘፍጥረት ውስጥ ካለው ትክክለኛ ትርጉም አውጥቶ ሌላ ትርጉም ሲሰጠው ምንም ችግር የለበትም፡፡
ይሁን እንጂ ሙስሊሞች አሁንም የሚከራከሩት ይህ ክፍል ከእስማኤል ዘር ውስጥ አንድ ሕዝብ እንደሚነሳ የሚናገር ትንቢት ነው በማለት ነው እንዲሁም ያ እንዲህ ዓይነቱ ትንቢት የሚናገረው ለእስልምና መነሳት በመጥቀስ ነው በማለት ነው፡፡ ነገር ግን የዚህ ትንቢት ፍፃሜ የተከናወነው በዚያው በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ ነው እንጂ ከሃያ መቶ ዓመታት በኋላ ቆይቶ በመካ አይደለም፡፡ ይህንንም የሚከተለው ጥቅስ ያሳያል፡-
‹የሣራ ባሪያ ግብፃዊቱ አጋር ለአብርሃም የወለደችው የአብርሃም ልጅ የእስማኤል ትውልድ ይህ ነው፤ የእስማኤልም የልጆቹ ስም በየስማቸውና በየትውልዳቸው እንዲህ ነው፤ የእስማኤል የበኵር ልጁ ነባዮት፥ ቄዳር፥ ነብዳኤል፥ መብሳም፥ ማስማዕ፥ ዱማ፥ ማሣ፥ ኩዳን፥ ቴማን፥ ኢጡር፥ ናፌስ፥ ቄድማ። የእስማኤል ልጆች እነዚህ ናቸው፥ ስማቸውም በየመንደራቸውና በየሰፈራቸው ይኸው ነው፤ በየወገናቸውም አሥራ ሁለት አለቆች ናቸው።› ዘፍጥረት 25.12-16፡፡
የአሊ የሚቀጥለው ምሳሌ የሙሴ ትንቢት እንደእርሱ ያለ ነቢይ እንደሚነሳ የተናገረው ነው፣ ይህንንም ከዚህ በላይ አይተነዋል፡፡ ሦስተኛው ትንቢትም የመጣው ከዘዳግም ውስጥ ነው፡-
‹የእግዚአብሔር ሰው ሙሴ ሳይሞት የእስራኤልን ልጆች የባረከባት በረከት ይህች ናት። እንዲህም አለ። እግዚአብሔር ከሲና መጣ፥ በሴይርም ተገለጠ፤ ከፋራን ተራራ አበራላቸው፥ ከአእላፋትም ቅዱሳኑ መጣ፤ በስተ ቀኙም የእሳት ሕግ ነበረላቸው።› ዘዳግም 33.1-2፡፡
እዚህ ላይ ማስታዎስ ያለባችሁ ይህ ክፍል ስለ ነቢያት ምንም የሚናገረው ነገር እንደሌለው ነው፡፡ ክፍሉ የሚናገረው እስራኤላውያንን ወደ ቅድስት አገር በማምጣት የተከናወነውን የእግዚአብሔርን ድል ነው፡፡ የሲናን ምድረ በዳ፣ ሴይርን እና ፋራንን ሲያልፉ እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ነበር፡፡ በእርግጥ የእግዚአብሔርን እርዳታ ለመግለፅ ሙሴ የተጠቀመበት እንደዚህ ዓይነት ቋንቋ በብሉይ ኪዳን ውስጥ የተለመደ ነው፡-
‹አቤቱ፥ ከሴይር በወጣህ ጊዜ፥ ከኤዶምያስም ሜዳ በተራመድህ ጊዜ፥ ምድሪቱ ተናወጠች፥ ሰማያቱም አንጠበጠቡ፤ ደመናትም ደግሞ ውኃን አንጠበጠቡ። ተራሮች ከእግዚአብሔር ፊት የተነሣ ቀለጡ፥ ያም ሲና ከእስራኤል አምላክ ከእግዚአብሔር ፊት የተነሣ።› መሳፍንት 5.4-5፡፡ ‹አቤቱ፥ በሕዝብም ፊት በወጣህ ጊዜ፥ በምድረ በዳም ባለፍህ ጊዜ፥ ምድር ተናወጠች፥ ከሲና አምላክ ፊት፥ ከእስራኤል አምላክ ፊት ሰማያትም አንጠበጠቡ። ... የእግዚአብሔር ሰረገላዎች የብዙ ብዙ ሺህ ናቸው፤ ጌታ በመቅደሱ በሲና በመካከላቸው ነው።› መዝሙር 68.7-8፣17፡፡
ነገር ግን የሙስሊም ተከራካሪዎች የሚሉት በእነዚህ የበረከት ቃላት ጅማሬ ላይ ያሉት የሙሴ ቃላት፣ የእግዚአብሔር ድል አድራጊነት መግለጫዎች አይደሉም፣ ነገር ግን እነሱ የሶስት ታላላቅ ትንቢቶች መግለጫዎች ናቸው በማለት ነው፡፡ አሊ የሚለውም፡- ‹ከሲና መምጣት› የሚለው የሚያመለክተው ለሙሴ መገለጥ ነው፣ ‹ከሴይር መውጣት› ደግሞ የሚያመለክተው ‹በዳዊት የተደገረውን የሴይርን ጦርነት ነው›፡፡ አሁን ደግሞ ፋራን እንምንቀበለው የሂጃዝ ምድር የጥንት ስም ነው ይህም መሐመድ (ሰላም በእርሱ ላይ ይሁንና) ከእስማኤል ዘር መካከል የተነሳበት ቦታ ነው፡፡› በማለት ነው፡፡
ይሁን እንጂ ብዙዎቹ የሙስሊም ተንታኞች የሚያምኑት ‹ሴይር› ለኢየሱስ ነቢይነት እንደሚያመለክት ነው፣ እንጂ ንጉሱ ዳዊት በሴይር ስላደረገው ጦርነት አይደለም፡፡ ስለዚህም ጃማል ባዳዊ የተናገረው፡- ዘዳግም 33.1-2 ስለ ሙሴ ኢየሱስና መሐመድ ጥቅል ማስረጃ በመሆን ነው የሚልን ነው፡፡ ስለ እግዚአብሔር ይናገራል (ማለትም ስለ እግዚአብሔር መገለጥ) ከሲና መምጣትን፣ ከሴይርም መውጣቱን (ምናልባትም የሴይር መንደር በኢየሩሳሌም አጠገብ) ከዚያም ከፋራን ሲያበራ፡፡ በዘዳግም 21.21 መሠረት የፋራን ምድረበዳ እስማኤል የተቀመጠበት ቦታ ነው (ማለትም አረቢያ በተለይም መካ)፡፡ See Jamal Badawi, ‘Muhammad in the Bible’፡፡
እነዚህ የባዳዊ ትርጉሞች በችግር የተሞሉ ናቸው፡፡ የሙሴ በረከት የጀመረው ጌታ በሚለው አባባል ነው እንጂ በነቢያት አይደለም፣ ጌታ ከሲና ይመጣል፣ ከሴይር ይወጣል፣ ከፋራን ተራራ ላይ ያበራል በማለት ነው፡፡ ይህ ስለ ነቢያት ነው የሚናገረው ብሎ መናገር የሚጠይቀው ነገር ቢኖር በምንም መንገድ ትክክል ወዳልሆነ ትርጉም ውስጥ መዝለልን ነው፡፡ በተለይም በተመሳሳይ አነጋገር በሌላ የብሉይ ኪዳን መጽሐፍት ውስጥ በእስራኤል ጠላቶች ላይ የተደረገውን የጌታን ድል የሚገልፁ ተመሳሳይ መግለጫዎች እያሉ ማለት ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ እግዚአብሔር በሲና መገለጥን በሚሰጥበት ጊዜም ይገኙበታል፡፡ የሙስሊሞች የሴይር ትርጉም በጣም ችግር ያለበት ነው፡፡ አሊ ያለው በሴይር የተደረገውን የዳዊትን ጦርነት ነው በማለት ነው፣ ታዲያ ይህ ከነቢይ መነሳት ወይንም ከመገለጥ መሰጠት ጋር ምን የሚያገናኘው ነገር ይኖራል? ባዳዊ ግን ያለው የሴይር መጠቀስ ምናልባት የሚያመለክተው በኢየሩሳሌም አጠገብ ስላለችው መንደር ነው በማለት ነው፡፡ ነገር ግን ይህ አመለካከት እርባና ቢስ ነው፡፡ ፔንታቱክ (አምስቱ ሙሴ መጸሐፍት) ሴይርን የሚጠቅሰው ብዙ ጊዜ ሲሆን ኤዶማውያን ያረፉበት ቦታ በማድረግ ነው ይህም ተመሳሳይ ቃል በዘዳግም 33 ላይም የተጠቀሰው ነው፡፡ ኤዶማውያን ደግሞ በኢየሩሳሌም አጠገብ ባለች መንደር ውስጥ አለመኖራቸው ምንም ሊባልለት የማያስፈልግ ነው (በጣም ግልጥ ነው)፣ ይህም ኢየሱስን ከሴይር ጋር ምንም ሊያዛምደው የማይችል ነገር ነው፡፡ በተጨማሪም ፋራን (በመካ አጠገብ ነው - በሙስሊሞች መሠረት) በቶራ (በብሉይ ኪዳን) ውስጥ እጅግ በጣም ብዙ ጊዜ ነው የተጠቀሰው፡-
‹የእስራኤልም ልጆች ከሲና ምድረ በዳ በየጉዞአቸው ተጓዙ፤ ደመናውም በፋራን ምድረ በዳ ቆመ።› ዘኁልቁ 10.12፣ ‹ከዚያም በኋላ ሕዝቡ ከሐጼሮት ተጓዙ፥ በፋራንም ምድረ በዳ ሰፈሩ።› ዘኁልቁ 12.16፣ ‹ሙሴም እንደ እግዚአብሔር ትእዛዝ ከፋራን ምድረ በዳ ላካቸው፤ እነርሱም ሁሉ የእስራኤል ልጆች አለቆች ነበሩ።› ዘኁልቁ 13.3፣ ‹በፋራን ምድረ በዳና በቃዴስ ወዳሉት ወደ ሙሴና ወደ አሮን ወደ እስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ ሄደው ደረሱ፤ ወሬውንም ለእነርሱና ለማኅበሩ ሁሉ ነገሩአቸው፥ የምድሪቱንም ፍሬ አሳዩአቸው።› ዘኁልቁ 13.26፣ ‹በዮርዳኖስ ማዶ በምድረ በዳ፥ በዓረባ ውስጥ በኤርትራ ባሕር ፊት ለፊት፥ በፋራን በጦፌልም በላባንም በሐጼሮትም በዲዛሃብም መካከል ሳሉ፥ ሙሴ ለእስራኤል ሁሉ የነገራቸው ቃል ይህ ነው።› ዘዳግም 1.1፡፡
የፋራን ተራራ ያለው በሲና ሰሜን ምዕራብ በኩል ሲሆን ከመካ ጋር በጣም ትልቅ ርቀት አለው፡፡ ይሁን እንጂ ባዳዊ እንደሚለው ፋራን የመሐመድም አገር እንኳን ቢሆን እንኳን ቶራ የሚግረን ግን እስራኤላውያን ከግብፅ ወጥተው ሲመጡ በዚያ የተወሰነ ጊዜን እንዳሳለፉ ብቻ ነው፡፡ እንዲሁም የእግዚአብሔር የእሳት ዓምድ ክብር በዚያም ለጥቂት ጊዜያት እንዳረፈ ነው፡፡ ስለዚህም ሙሴ የዘገበው ‹ከፋራን እግዚአብሔር ያበራል› የሚለውን ነው፡፡ ስለዚህም ትርጉም የሚሰጥ የሚሆነው ጌታ ከፋራን ያበራል ብሎ መናገር ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም ጌታ በግልፅ በሚታይ ሁኔታ ከፋራን ተራራ ላይ ያበራ ነበር እንጂ መሐመድ ከመካ ላይ ከቁርአኑ ጋር በምሳሌ ያበራል የሚል አይደለም፡፡
የአሊ መጨረሻው ትንቢት (ኢየሱስ ስለሚመጣው አፅናኝ ትንቢትን ተናግሯል ከሚለው ሌላ) የተወሰደው ከኢሳያስ ትንቢት ላይ ነው፡- ‹ስለ ዓረብ የተነገረ ሸክም። የድዳናውያን ነጋዴዎች ሆይ፥ በዓረብ ዱር ውስጥ ታድራላችሁ። በቴማን የምትኖሩ ሆይ፥ ወደ ተጠሙት ሰዎች ውኃ አምጡ እንጀራ ይዛችሁ የሸሹትን ሰዎች ተቀበሉአቸው። ከሰይፍ፥ ከተመዘዘው ሰይፍ፥ ከተለጠጠውም ቀስት ከጽኑም ሰልፍ ሸሽተዋልና።› ኢሳያስ 21.13-15፡፡
አሊ እንደሚለው ‹ስለ ዓረብ የተነገረ ሸክም።› ስለ መሐመድ የተነገረ ግልፅ ትንቢት ነው በማለት ነው፡፡ በመጀመሪያም አረቢያ የሚለው ቃል በራሱ በጣም ጠቃሚና ብቁ ነው ይላል፡፡ ከዚያም ‹የሸሸው› ሰው መጠቀስ ደግሞ አሁንም ትንቢቱ ስለሚነገርለት ሰው ሌላ ተጨማሪ ብርሃንን ይሰጣል፡፡ የዓለም ታሪክ የመዘገበው አንድ እንደዚህ ዓይነትን ሽሽት ነው ይህም በዓለም ላይ የተፈፀመን ታላቅ ክስተት ተብሎ እንዲመዘገብ አድርጎታል ይህም የቅዱሱ ነቢይ የመሐመድ ከመካ ያደረገው ሽሽት ነበር ይላል፡፡ እንደገናም በጣም ግልፅ የሆነው ምስክርነት በቃላቶቹ ውስጥ ይገኛል ‹ከሰይፍ፥ ከተመዘዘው ሰይፍ፥ ከተለጠጠውም ቀስት ከጽኑም ሰልፍ ሸሽተዋልና› በሚለው ቃል ውስጥ ነው፡፡ ታሪክ ያረጋገጠው ቅዱሱ ነቢይ መሐመድ ከመካ ሸሽቷል በደም የተጠሙ ጠላቶቹ ሰይፍን መዝዘው ቤቱ ገና ተከቦ እያለ ነው፣ ይህም እሱ ከቤቱ ውስጥ እንደወጣ በእርሱ ላይ ለመውደቅና ለመግደል ነው፣ እነዚህ ሁለቱ ስልጣን ያላቸው የታሪክ እውነታዎች የተጠቀሱት እና የተሞሉት የአረቢያን ምድር በመጥቀስ ጭምር ነው ይህም የነቢዩ መወለጃ ቦታ እንደሆኑ ተደርገው ነው፡፡ ስለዚህም ይህ ምንም ልንክደው የማንችለውን (ከክርክር ውጪ የሆነውን) ማስረጃ ስለ ነቢዩ መሐመድ ነቢይነት ይሰጣሉ፡፡ Maulana Muhammad Ali, Muhammad in the Bible, p. 26.
ይህ ትንቢት ከክርክር ውጪ ነው በማለት ከአሊ ጋር ከመስማማታችን በፊት ምናልባት የሚከተሉትን ሁለት ጥቅሶች ማንበብ ይኖርብናል፣ እነዚህም እርሱ ሆን-ብሎ ከጥቅሶቹ ውስጥ ያስወገዳቸው ናቸው፡- ‹ጌታ እንዲህ ብሎኛልና። እንደ ምንደኛ ዓመት በአንድ ዓመት ውስጥ የቄዳር ክብር ሁሉ ይጠፋል፤ ከቀስተኞች ቍጥር የቀሩት፥ የቄዳር ልጆች ኃያላን፥ ያንሳሉ፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ተናግሮአልና።› ኢሳያስ 21.16-17፡፡
አሊ የዘለላቸው ጥቅሶች ይህ ትንቢት መቼ መፈፀም እንዳለበት የጊዜ ሰሌዳን ይሰጣሉ፡፡ የትንቢቱ ፍፃሜ መሆን ያለበት ትንቢቱ በተነገረበት በአንድ ዓመት ውስጥ ነው፡፡ ትንቢቱ የተነገረበትን ሰዓት በትክክል መናገር ባንችልም የምናውቀው ኢሳያስ ይህንን ትንቢት የተናገረው የአሶራውያን መንግስት እየተስፋፋ ባለበት ጊዜ ውስጥ ነው እንዲሁም አሶራውያን አረቢያን መውረር የጀመሩት በ732 ዓ.ዓ ነው፡፡ በተጨማሪም የቴማ ነዋሪዎች ይኖሩ የነበሩት ከመካ አራት መቶ ማይልስ ወደሰሜን ርቀው ነበር፣ ስለዚህም ይህ ትንቢት ለመሐመድ ከመካ ላደረገው ሽሽት እንዴት ሊሆን እንደሚችል መገመት አስቸጋሪ ነው፡፡ ስለዚህም በጣም ተቀባይነት የሚኖረው ኢሳያስ የተነበየው አሶራውያን በራሱ ዘመን አረቢያን ስለመውረራቸው መሆኑን ነው እንጂ መሐመድ ከመካ ስላደረገውና ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ ስለሆነው ሁኔታ አይደለም፡፡
ይህ እንግዲህ አሊ ያቀረበውንና መጽሐፍ ቅዱስ ስለመሐመድ ይናገራል ስለሚለው ሐሳብ መደምደሚያን ይሰጠናል፡፡ ሌሎች የሙስሊም ተከራካሪዎችም ተጨማሪ የሆኑ ሌሎች ጥቂት ትንቢቶችን ይሰጣሉ፣ ነገር ግን ሁሉም ተመሳሳይ ችግሮችን ይሰቃያሉ፡፡ ስለ መሐመድ ተነገሩ የተባሉትን አምስት የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን ከመረመርን በኋላ፣ ሙስሊሞች በክርክራቸው ስለመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች የሚጠቀሙባቸው ዘዴዎች የሚያጠቃልሉት የሚከተሉትን ደረጃዎች ነው፡፡
አንደኛ ደረጃ፡- በግምት ውጠራ ስለ መሐመድ የተነገረ ትንቢት ነው ተብሎ ሊቆጠር የሚችልን ማንኛውንም ጥቅስ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መፈለግ፡፡
ሁለተኛ ደረጃ፡- ጥቅሱን ከዓውዱ ዙሪያ ውስጥ ነጥሎ (ቦጭቆ) ማውጣት ይህንንም ለማድረግ ከጥቅሱ የቀደሙትን እና ከዚያም የሚከተሉትን ሌሎች ጥቅሶችን መዝጋት፡፡
ሦስተኛው ደረጃ፡- ግልፅ የሆኑትን የትንቢቱን ስሜት ሰጭ ትርጉሞች ሁሉ መዝጋትና በተለይም ትንቢቱ ከተነገረ በኋላ የተፈፀሙትን ትክክለኛ ነገሮችን መዝጋት፡፡
አራተኛው ደረጃ፡- ትንቢቱን እና የሙስሊም ትርጉሙን በመጽሐፍት፣ በትናንሽ ጽሑፎች በስብከቶች እና በኢንቴርኔት ጽሑፎች ውስጥ በጣም ማስተዋወቅ ይህም ክፍሉን በጥንቃቄ የሚመረምሩት ጥቂቶች እንደሆኑ በማወቅና በማመን ነው፡፡
እንዲህ ዓይነቱ አቀራረብና ዘዴ ላልነቁት ምንም የማይመስል ቢሆንም ለብዙዎቹ ሙስሊም ተከራካሪዎች ግን በጣም የተለመደ ነገር ነው፡፡ ይሁን እንጂ በእርግጥ የእነሱ ስህተት አይደለም፡፡ መሐመድ የተናገረው መጽሐፍ ቅዱስ ስለእስልምና መነሳት የሚናገር ትንቢት የሞላበት መጽሐፍ ነው በማለት ስለተናገረ ነው፡፡ ስለዚህም ሙስሊሞች እነዚያን ትንቢቶች ለመፈለግና ለማግኘት የሚችሉትን ሁሉ ማድረግ አለባቸው፡፡ እነሱም ለአስራ አራት መቶ ዓመታት ሁለት የማይቃረኑ ትንቢቶችን (አንድ ከብሉይ ኪዳን አንድ ደግሞ ከአዲስ ኪዳን) ለማግኘት ሞክረዋል፣ ነገር ግን ጥረታቸው ሁሉ ውድቅ ሆኖባቸዋል፡፡ ይህም እጅግ በጣም ከፍተኛ ችግርን ለእስልምና አቅርቦበታል፡፡ ስለዚህም ይህ የማስረጃ እጥረት ወደ አሰቃቂ መደምደሚያ ላይ አምጥቷቸዋል፡፡ መሐመድ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እስልምና መምጣት ተናግሯል ስላለ የሚከተሉት ዋና ሐሳቦቸ (ጭምቅ የውጤት ሐሳቦች) የመሐመድን ነቢይነት የሚያፈርሱ ይሆናሉ፡-
ዋና ሐሳብ አንድ፡- መሐመድ እውነተኛ ነቢይ ቢሆን ኖሮ መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ እና በጣምም ግልጥ የሆኑ ስለመሐመድ የተነገሩ ትንቢቶችን ይዞ ይገኝ ነበር (ምክንያቱም ይህንን ነውና እርሱ የተናገረው)፡፡
ዋና ሐሳብ ሁለት፡- በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ መሐመድ የተነገሩና ግልፅ የሆኑ ምንም ትንቢቶች የሉም፡፡
መደምደሚያ፡- ስለዚህም መሐመድ እውነተኛ ነቢይ አልነበረም፡፡
በእርግጥ ይህም ማለት ደግሞ ሙስሊሞች ለመጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃ የሚያደርጉት ፍለጋ እራሱ በትክክል የሚያሳየው - ሃይማኖቱ ሐሰት መሆኑን ነው፡፡ ይሁን እንጂ እንደዚህ ዓይነቱ መደምደሚያ በጣም ችኩል ሊሆን ይችላል ምክንያቱም በእውነት መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መሐመድ የሚናገራቸው ትንቢቶች አሉትና፡፡ እነዚህንም ትንቢቶች ሙስሊሞች ዝም ብለው አልፈዋቸዋል፡፡
እውነተኛ ትንቢቶች
የሚከተሉትን ከአዲስ ኪዳን ላይ የተወሰዱትን ትንቢቶች ተመልከቱ፡- ‹የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ በውሥጣቸው ግን ነጣቂዎች ተኵላዎች ከሆኑ ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ። ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ። ከእሾህ ወይን ከኩርንችትስ በለስ ይለቀማልን?› ማቴዎስ 7.15-16፡፡
‹በዚያን ጊዜ ለመከራ አሳልፈው ይሰጡአችኋል ይገድሉአችሁማል፥ ስለ ስሜም በአሕዛብ ሁሉ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ። በዚያን ጊዜም ብዙዎች ይሰናከላሉ እርስ በርሳቸውም አሳልፈው ይሰጣጣሉ እርስ በርሳቸውም ይጣላሉ፤ ብዙ ሐሰተኞች ነቢያትም ይነሣሉ ብዙዎችንም ያስታሉ› ማቴዎስ 24.9-11፡፡
‹ይህም ድንቅ አይደለም፤ ሰይጣን ራሱ የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣልና። እንግዲህ አገልጋዮቹ ደግሞ የጽድቅን አገልጋዮች እንዲመስሉ ራሳቸውን ቢለውጡ ታላቅ ነገር አይደለም፤ ፍጻሜአቸውም እንደ ሥራቸው ይሆናል።› 2ቆሮንቶስ 11.14-15፡፡
‹መንፈስ ግን በግልጥ። በኋለኞች ዘመናት አንዳንዶች የሚያስቱ መናፍስትንና በውሸተኞች ግብዝነት የተሰጠውን የአጋንንትን ትምህርት እያደመጡ፥ ሃይማኖትን ይክዳሉ ይላል፤ በገዛ ሕሊናቸው እንደሚቃጠሉ ደንዝዘው፥› 1ጢሞቴዎስ 4.1-2፣
‹ሕይወት የሚገኝበትን ትምህርት የማይታገሡበት ዘመን ይመጣልና፤ ነገር ግን ጆሮቻቸውን የሚያሳክክ ስለ ሆነ፥ እንደ ገዛ ምኞታቸው ለራሳቸው አስተማሪዎችን ያከማቻሉ። እውነትንም ከመስማት ጆሮቻቸውን ይመልሳሉ፥ ወደ ተረትም ፈቀቅ ይላሉ።› 2ጢሞቴዎስ 4.3-4፡፡
በእርግጥ እነዚህ ጥቅሶች ለመሐመድ ብቻ አይደለም መዋል ያለባቸው፡፡ ነገር ግን ያለምንም ጥርጥር መሐመድ የብዙ የአዲስ ኪዳን ትንቢቶች ፍፃሜ ነው፡፡
አንደኛ፡- ጌታ ኢየሱስ የተናገረው የሐሰት ነቢያት የበግን ለምድ ለብሰው እንደሚመጡ ነው፣ ነገር ግን እነሱ በእርግጥ ነጣቂ ተኩላዎች ናቸው፡፡ በታሪክ ውስጥ ከተነሱት ሁሉ መሐመድ ይህንን ትንቢት በቀጥታ ይፈፅመዋል፡፡ እርሱ ተከታዮቹን ያሳመናቸው፣ እርሱ በታሪክ ውስጥ ታላቅ የሆነ የሞራል ምሳሌ እንደሆነ ነው ነገር ግን እርሱ እጅግ በጣም ብዙ ሰዎችን ገድሏል በባሪያ ንግድ ውስጥ ተሳትፏል፣ ባሎች ሚስቶቻቸውን እንዲደበድቡ ፈቅዷል፣ ተከታዮቹ ከባሪያ ሴቶች ጋር ግብረ ስጋ ግንኙነትን እንዲፈፅሙ ፈቅዶላቸዋል፣ በአንድ ጊዜ ቢያንስ ዘጠኝ የሚሆኑ ሚስቶች ነበሩት፣ እራሱ ያመነበትን ጥቅሶችን ከሰይጣን ተናግሯል፣ እንዲሁም ከዘጠኝ ዓመት ልጅ ጋር ግብረ ስጋ ግንኙነትን ፈፅሟል፣ ስለዚህም መሐመድ ጌታ ኢየሱስ የሐሰተኛ ነቢይ ይመጣል ተብሎ የተናገረለት ትንቢት ፍፃሜ ካልሆነ ታዲያ ማን ሊሆን ነው?
ሁለተኛው፡- ኢየሱስ የሐሰት ነቢያት እንደሚነሱ ተናግሯል እንደዚሁም እነሱ ብዙዎችን እንደሚያስቱ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በዓለማችን ላይ ከአንድ ቢሊዬን በላይ የሚሆኑ ሙስሊሞች አሉ፣ እንዲሁም እስላም በዓለም ላይ ከሉት በጣም አዳጊ ሃይማኖቶች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ይህም ማለት መሐመድ በሁሉም ጊዜ ውስጥ ታላቁ የሐሰት ነቢይ ነው ማለት ነው ይህም የኢየሱስ ክርስቶስ ትንቢት በጣም ግልጥ የሆነው የትንቢት ፍፃሜ ነው ማለት ነው፡፡
ሦስተኛ፡- ሐዋርያው ጳውሎስ የተናገረው ሰይጣን የብርሃንን መልአክ መስሎ እንደሚያስት ነው፡፡ መሐመድ ይህንን ተገንዝቦ ቢሆን ኖሮ መንፈስ ገብርኤል ነኝ በማለት በድንገት መጀመሪያ በተገለጠለት ጊዜ በመጀመሪያ የተሰማውን ስሜት ሊቀበለው ይችል ነበር፡፡ (መገለጥን እንዳገኘ መሐመድ የመጀመሪያው ስሜት እርሱ በሰይጣን ልክፍት ውስጥ የገባ ሆኖ እንደተሰማው ነበር)፡፡ (አስማት የተደገረበት ነቢይ የሚለውን ይመልክቱ)፡፡ ይህም የጳውሎስ ቃል ግልፅ የሆነ ፍፃሜ ነው፡፡
አራተኛ፡- ጳውሎስ የተናገረው ሰዎች ለሚያስቱ መናፍስት እና ለሰይጣን ትምህርት እራሳቸውን እንደሚሰጡ ነው፡፡ የመሐመድም የታወቁት የሰይጣን ጥቅሶች ለዚህ አስደናቂ ምሳሌን ይሰጡናል፡፡ የእስላም ነቢይ የተቀበለው መገለጥ ከአላህ ሌላ አማልክት ለሆኑት መፀለይ ምንም ችግር እንደሌለበት ነው፡፡ ቆይቶ ግን እነዚህን ቃላት በከንፈሮቹ ላይ ያስቀመጣቸው ሰይጣን እንደሆነ ተናገረ፡፡ (አስማት የተደረገበት ነቢይ የሚለውን ተመልከቱ)፡፡ ስለዚህም ልክ ጳውሎስ እንደተነበየው መሐመድ በሰይጣን ትምህርት ተታልሎ ነበር ማለት ነው፡፡
አምስተኛ፡- ጳውሎስ የተነበየው ሰዎች ጤናማውን ትምህርት የማይሰሙበት ጊዜ እንደሚመጣ ነው፡፡ እውነትን ከመስማት ይልቅ ተረትን ወደ መስማት ጆሮቻቸውን እንሚያዘነብሉ ነው፡፡ የዚህ ትንቢት ትክክለኛ ፍፃሜ በተግባር የሚታየው በአሁኑ ጊዜ ባሉት ሙስሊሞች ዘንድ ነው፡፡ እጅግ በጣም ብዙ የሆኑና እውነትን የሚፈልጉ ሙስሊሞች ቢኖሩም እንኳን ማስረጃዎች የሚያመለክቱት ወዴት ነው የሚለውን ለማየት ፈቃደኛ ያልሆኑና ግድ የሌላቸው እጅግ በጣም ብዙ ሙስሊሞች አሉ፡፡ እስልምና ሊታመን የማይቻል ሃይማኖት መሆኑን ከመቀበል ይልቅ መስማት የሚፈልጉቱን እንዲነግሯቸው ወደ ጃማል አል ባዳዊና ወደ ሻቢር አላይ ይሄዳሉ፡፡
እነዚህ የጌታ ኢየሱስ ትንቢቶች ለእስልምናና ለመሐመድ በትክክል ሊያገለግሉ ይችላሉ፡፡ በመሆኑም መሐመድ ሌሎች የእግዚአብሔር መልእክተኞች ስለ እርሱ እንደተናገሩ ሲናገር እርሱ ትክክል ነበር ማለት ነው፡፡ ችግር የሚሆነው እነዚህ መልእከተኞች የተናገሩት ስለ ሐሰት ነቢያት መነሳት ነበር፣ እንጂ ከክርስትና በኋላ ስለሚመጣ አዲስ ሃይማኖት መነሳት አልነበረም፡፡ በአሰቃቂ ሁኔታ ብዙ ሰዎች የሐሰት ነቢይን መነሳት ማስጠንቀቂያ አላስተዋሉትም፡፡ እስከ አሁንም ዘመን ድረስ ብዙዎች የክርስቶስን ቃላት አይቀበሉም፡፡ ነገር ግን አንድ ከሞት የተነሳ ሰው እና መነሳቱም በእግዚአብሔር የተመሰከረለትና ሰው ሁሉ የሚናገረውን ሊሰማለት የሚገባው ሰው ቢኖርና - ይህ ከሞት የተነሳ ሰው የሐሰት ነቢያት ይመጣሉ በማለት ቢነግረን - እኛ ምናልባት ነቢይ ነኝ በማለት የሚነሳን ማንኛውንም ሰው የምንመለከተው በጥርጣሬ ዓይን መሆን ይኖርበታል፡፡ በተለይም -- ልክ እንደ መሐመድ በባህርዩ ብልሹ የሆነውን ሰው ነቢይነት በጥርጣሬ መመልከት ይኖርብናል፡፡ በእርግጥም ከሌሎች የባህርይ ጉድለቶቹ ባሻገር መሐመድ በዓለም ላይ ያለውንና በጣም ግልጥ የሆነውን ትንቢት ባለመቀበሉ በደለኛ ነው፡፡ ይህም ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሞት እና ትንሳኤ የተነገረውን ትንቢት ነው፡፡ ይህም ትንቢት፡-
‹የሰማነውን ነገር ማን አምኖአል? የእግዚአብሔርስ ክንድ ለማን ተገልጦአል? በፊቱ እንደ ቡቃያ ከደረቅም መሬት እንደ ሥር አድጎአል። መልክና ውበት የለውም፥ ባየነውም ጊዜ እንወድደው ዘንድ ደም ግባት የለውም። የተናቀ ከሰውም የተጠላ፥ የሕማም ሰው ደዌንም የሚያውቅ ነው፤ ሰውም ፊቱን እንደሚሰውርበት የተናቀ ነው፥ እኛም አላከበርነውም። በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ ሕመማችንንም ተሸክሞአል፤ እኛ ግን እንደ ተመታ በእግዚአብሔርም እንደ ተቀሠፈ እንደ ተቸገረም ቈጠርነው። እርሱ ግን ስለ መተላለፋችን ቈሰለ፥ ስለ በደላችንም ደቀቀ፤ የደኅንነታችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ፥ በእርሱም ቍስል እኛ ተፈወስን። እኛ ሁላችን እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ጠፋን፤ ከእኛ እያንዳንዱ ወደ ገዛ መንገዱ አዘነበለ፤ እግዚአብሔርም የሁላችንን በደል በእርሱ ላይ አኖረ። ተጨነቀ ተሣቀየም አፉንም አልከፈተም፤ ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት፥ በሸላቶቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ፥ እንዲሁ አፉን አልከፈተም። በማስጨነቅና በፍርድ ተወሰደ፤ ስለ ሕዝቤ ኃጢአት ተመትቶ ከሕያዋን ምድር እንደ ተወገደ ከትውልዱ ማን አስተዋለ? ከክፉዎችም ጋር መቃብሩን አደረጉ፥ ከባለጠጎችም ጋር በሞቱ ሆኖም ግፍን አላደረገም ነበር፥ በአፉም ተንኮል አልተገንበትም ነበር። እግዚአብሔርም በደዌ ያደቅቀው ዘንድ ፈከደ፤ ነፍሱን ስለ ኃጢአት መሥዋዕት ካደረገ በኋላ ዘሩን ያያል፥ ዕድሜውም ይረዝማል፥ የእግዚአብሔርም ፈቃድ በእጁ ይከናወናል። ከነፍሱ ድካም ብርሃን ያያል ደስም ይለዋል፤ ጻድቅ ባሪያዬም በእውቀቱ ብዙ ሰዎችን ያጸድቃል፥ ኃጢአታቸውን ይሰከማል። ስለዚህም እርሱ ብዙዎችን ይወርሳል፥ ከኃያላንም ጋር ምርኮን ይከፋፈላል፤ ነፍሱን ለሞት አሳልፎ ሰጥቶአልና፥ ከዓመፀኞችም ጋር ተቈጥሮአልና፤ እርሱ ግን የብዙ ሰዎችን ኃጢአት ተሸከመ፥ ስለ ዓመፀኞችም ማለደ።› ኢሳያስ 53፡፡1-12፡፡
የአዘጋጁ ማሳሰቢያ፡-
መሐመድ ነቢይ ሆኖ ይመጣል የሚልን ትንቢት መጽሐፍ ቅዱስ ይዟል በማለት ሙስሊሞች ከሚያቀርቧቸው ውስጥ የአምስቱን ትክክለኛ ትንተና ከዚህ በላይ አይተናል፡፡ እንደተመለከትነውም ይህ የሙስሊሞች ክርክር ዞሮ ዞሮ በራሳቸው ላይ ችግርን እንደፈጠረ ነው፣ ምክንያቱም ጥቅሶቹ ስለ መሐመድ የሚናገሩት ምንም ነገር የለምና፡፡ በትክክል ክርክሮቹን ሎጂካዊ በሆነ መንገድ ያጠና እንዲሁም እውነትን ፈላጊ የሆነ ሁሉ ቁርአንም ሆነ የእስልምና ሃይማኖት መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት የሌላቸው መሆናቸውን ማስተዋል ይችላል፡፡
በዚህ የዴቪድ ውድ ጽሑፍ መደምደሚያም ላይ ያየነው ሌላው አስገራሚ ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መሐመድ በግልፅ የሚናገረው ነገር እንዳለው ነው፡፡ ይህም ከተሰጡት ጥቅሶች አኳያ መሐመድ የሐሰት ነቢይ መሆኑ እጅግ በጣም ግልጥ ነው፡፡
ታዲያ አንባቢዎች ምን ማድረግ ይገባቸዋል? የሚከተሉት ሃይማኖት ትክክል አለመሆኑን በማስረጃ ካዩት የሚቀጥለው እርምጃቸው ምንድነው መሆን የሚገባው? እነዚህን ጥያቄዎች አንባቢዎች በቅንነት ሊያስቡባቸው ይገባል፡፡ ምክንያቱም የምንከተለው ሃይማኖት ከዘላለም ሕይወት ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነውና፡፡ የምንከተለው ሃይማኖትና እምነት ውሸት ከሆነ ያለምንም ጥርጥር ለዘላለም ሲዖል ውስጥ መግባታችን ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከፍተኛ ኪሳራ ነው፣ የዘላለም ኪሳራ ነው፣ በቀላሉም ልንመለከተው አንችልም፣ በቀላሉ ልንመለከተውም አይገባንም፡፡
አንባቢዎች ሆይ! በአዲስ ኪዳን በዮሐንስ ወንጌል 8.31-32 ላይ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገረውን ቃል እናሳስባችኋለን፡፡ እርሱ የተናገረው ቃል እውነት በመሆኑ ሰዎች በቃሉ ቢኖሩ እውነትን እንደሚያውቁ፣ ያወቁት እውነት ደግሞ አርነት ወይንም በሌላ ቃል ነፃነት እንደሚያወጣቸው የተናገረው ነው፡፡ እውነትን ማወቅና መከተል ለሰዎች መንፈሳዊ ሕይወት እጅግ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ የዚህ ገፅ አዘጋጆችም ዋና ዓላማ ሙስሊሞች እውነትን እንዲያውቁና ወደ እውነትም በመምጣት የሚገኘውን ነፃነት፣ የዘላለምንም ሕይወት እንዲወርሱ ነው፡፡
በመሆኑም የእውነት ምንጭ ወደሆነውና ለሚያምኑትም ሁሉ እርግጠኛ የሆነ የዘላለምን ሕይወት ተስፋ ወደሚሰጠው ወደ ጌታ ኢየሱስ እንድትመጡ እንጋብዛችኋለን፡፡ በእርሱ በኩል ወደ እግዚአብሔር ቀርበው ኃጢአታቸውን በመናዘዝ ይቅርታን ለመቀበል በእርሱ የታመኑት ሁሉ እውነተኛ የሕይወት ለውጥን አግኝተዋል፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር በመታረቅ የእርሱ ልጆችና የመንግስቱ ወራሾችም ሆነዋል፡፡ ይህንን ትልቅ ምህረትና ትልቅ ይቅርታ ደግሞም ተዓምር እንድታገኙ እንጋብዛችኋለን፡፡ ጌታም በምህረቱ እንዲሁም በፀጋው ይርዳችሁ አሜን፡፡
የትርጉም ምንጭ: Muhammad in the Bible? An Analysis of the Muslim Appeal to Biblical Prophecy, David Wood
ለእስልምና መልስ አማርኛ ዋናው ገጽ