የአውራ ጣት ሕግ

ትንሳኤና ቁርዓን በሎጂክ አካሄድ

David Wood

ትርጉምና ቅንብር በአዘጋጁ

የኤቨረስት ተራራ ከአውራ ጣት እጅግ በጣም ትልቅ ነው፡፡ ይሁን እንጂ አውራ ጣቴን በአይኔ ፊት ባደርገው ተራራውን ሙሉ በሙሉ ይሸፍነዋል፡፡ ይህም እኔ ከኤቨረስት ተራራ ይልቅ ለእኔ በጣም ቅርብ ስለሆነ እኔ የራሴን ጣት ከተራራው የበለጠ እንደሆነ አድርጌ አየዋለሁኝ ማለት ነው፡፡ በተመሳሳይ መንገድ ፀሐይና ጨረቃ ከምድር ሆነው ሲታዩ ፍፁም እኩል የሆነ መጠን ያላቸው ነው የሚመስሉት ይህ የሆነበትም ምክንያት እኛ እጅግ በጣም ለጨረቃ የቀረብን ስለሆነ ነው፡፡ እኛ ወደ ጨረቃ ጉዞን ብናደርግ በጣም እየቀረብናት ስለምንሄድ ከፀሐይ እጅግ በጣም ትልቅ መስላን ልትታይ ትችላለች፡፡ ነገር ግን ይህ ሁሉ ፀሐይ ከጨረቃ ሚሊየን ጊዜ የመብለጧን እውነታ በፍፁም ሊቀይረው አይችልም እንደዚሁም የኤቨረስት ተራራ ከጣቴም ሚሊዮን ጊዜ የበለጠ ነው፡፡

እጅግ በጣም ብዙ ሚሊዬን የሆኑ ሙስሊሞች እስልምና እጅግ በጣም ብዙ በሆነ ሳይንሳዊና ታሪካዊ ማስረጃ የተደገፈ ነው በማለት ያምናሉ፡፡ ክርስትያኖች ግን የሚያምኑት ማስረጃዎቹ በትክክል ቢመረመሩ የክርስትናን እውነትነት እንደሚያመለክቱ ነው፡፡ ሙስሊሞችና ክርስትያኖች ሁለቱም በአንድ ጊዜ ትክክል ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ስለዚህም ከሁለቱ አንደኛው ያለው በአይን እይታ መምታታት የተፈጠረው ዓይነት ችግር ውስጥ ነው፡፡ ምናልባትም ለክርስትና ያለው ማስረጃ ከአውራ ጣቴ በምንም የማይበልጥ ሊሆን ይችል ይሆናል ይህም የእስልምና ማስረጃ ተራራ እዚያ እሩቅ ትልቅ ሆኖ እያለ እንደማለት ነው፡፡ ምናልባትም እስልምና ልክ እንደ ጨረቃ የክርስትናን ብርሃን መጋረድ ችሎ ይሆናል ይህም ሙስሊሞች ሁሉንም ነገር የሚመለከቱት ከተምታታ አቋም ላይ በመነሳት ስለሆነ ነው፡፡

በምዕራብ ከተነሳው (እያደገ ካለው) አለማመን ጋር እስልምናንና ክርስትናን በመደገፍ በታሪክ ውስጥ እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ ንግግሮች ተደርገዋል፡፡ ይህ እጅግ በጣም ብዙ የሆነው ክርክር አድጓል - ይህም የሆነው ሃይማኖታዊውና ዓለማዊው የእምነት ስርዓት ‹የትኛው የበለጠ አሳማኝ ነው› በሚል የሕልውና ክብር እየተፎካከረ ባለበት ሁኔታ ነው፡፡ እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ ማስረጃዎች ስላሉ ጉጉት ያላቸውና እውነቱን ፈላጊዎች በፍለጋቸው ውስጥ በመካከል የሚይዙትንና የሚጨብጡትን ሲያጡ ይታያሉ፡፡ ስለዚህም በሁለቱ ተፎካካሪ ስርዓቶች መካከል የትኛውን ነው መርጦ መያዝ የሚገባው የሚለው ተስፋ አስቆራጭ የሆነና አስቸጋሪ ነገር ነው፡፡

ይህንን ችግር ቆርጦ ለማለፍ የሚያስችል ምናልባት አሳማኝ የሚሆነው ማስረጃ ቢኖር፤ ለእያንዳንዱ መከራከሪያ ያለውን ስርዓት በጥንቃቄ መመልከትና መመርመር ነው፡፡ ስለዚህም፣ ለእስልምናና ለክርስትና ያለውን ማስረጃ ለማወዳደር፣ የእኛ የመጀመሪያ እርምጃ መሆን ያለበት ለእስልምና ያለውን ከፍተኛና ጠንካራ ነው የሚባለውን መከራከሪያ ወይንም ማስረጃ በጥንቃቄ መመርመር እና ይህንንም ከክርስትና ጠንካራ ማስረጃ ጋር ማወዳደር ነው፡፡ ይህም ዘዴ በዓለም ላይ ያሉትን ሁለት ታላላቅ ሃይማኖቶች ስርዓት ለመመርመር ‹ማስረጃ› ነገር ይሆንልናል (ታላላቅ በተከታዮቻቸው ቁጥር መሠረት)፡፡

የእስልምና ማዕከላዊ ማስረጃ በመሆን የሚቀርበው ሁልጊዜ ቁርአን ነው፡፡ ቁርአን ከእግዚአብሔር የመጣ መሆኑን ለማስረዳት በጣም ዘመናዊው መከራከሪያ ሆኖ የሚቀርበው ደግሞ ሳይንሳዊ ትክክለኛነቱ እንደሆነ ነው፡፡ ይህ ዘመናዊው መከራከሪያ ነው፣ ይሁን እንጂ በቀዳዳዎች የተሞላ ነው፡፡ ለምሳሌም ያህል መሐመድ የተናገረው፡-

1. ከዋክብት በዲሞኖችን (በሰይጣናትን) ላይ የሚተኮሱ ሚሳይሎች ናቸው ብሎ ነው፡፡

2. የሰው ፅንስ የሚያልፈው በደም መርጋት ደረጃ ውስጥ ነው፡፡

3. ሰዎች 90 ጫማ የቁመት ርዝመት የነበራቸው ነበሩ፡፡

4. ፀሐይ በረግረጋማ ጭቃ ውስጥ ትጠልቃለች እንዲሁም ደግሞ

5. ጉንዳኖች መናገር ይችላሉ ይላል (ለእነዚህ ለእያንዳንዳቸው ዝርዝር ወደ ፊት ይቀርባል)

በቁርአንና በሃዲት ውስጥ ካሉት ከእነዚህና ከሌሎችም ሳይንሳዊ ስህተቶች የተነሳ የቁርአንን ሳይንሳዊ ፍፁምነት በማንሳት ሙስሊሞች የሚናገሩት ነገር ፍፁም አሳማኝ ሊሆን የማይችል ነው፡፡ በጭራሽ አያሳምንም፡፡

ይሁን እንጂ ቁርአን ከእግዚአብሔር የመጣ ነው ለማለት ሌላም ማስረጃዊ ክርክር አለ፡፡ ሙስሊሞች አንዳንድ ጊዜ የሚናገሩት ቁርአን እጅግ በጣም ልዩ በሆነ መንገድ ተጽፏል በማለት ነው፡፡ ቁርአን እጅግ በጣም ግሩም ነው በእያንዳንዱም ዝርዝር ነገር ላይ አድናቆትን የሚያስገኝ ነው፡፡ ይህም ደግሞ ከእግዚአብሔር ብቻ የሆነ መሆኑን የሚያሳይ ነው ይላሉ፡፡ ይህም ክርክር እራሱ የመጣው ደግሞ ከእራሱ ከቁርአኑ ላይ ነው፡፡

‹በባሪያችንም ላይ ካወረድነው በመጠራጠር ውስጥ ብትኾኑ ከብጤው አንዲትን ምዕራፍ አምጡ ውነተኞችም እንደኾነችሁ ከአላህ ሌላ መስካሪዎቻችሁን ጥሩ› ቁርአን 2.23፡፡

‹አብዛኛዎቻቸውም ጥርጣሬን እንጂ አይከተሉም ጥርጣሬ ከእውነት ምንም አያብቃቃም አላህ የሚሠሩትን ሁሉ ዐዋቂ ነው፡፡ ይህም ቁርአን ከአላህ ሌላ (ከኾነ ፍጡር) የተቀጠፈ ሊኾን አይገባውም ግን ያንን ከርሱ በፊት ያለውን (መጽሐፍ) የሚያረጋግጥና በመጽሐፉ ውስጥ ያለውን የሚዘረዝር በርሱ ጥርጣሬ የሌለበት ሲኾን ከዓለማት ጌታ (የተወረደ) ነው፡፡› ቁርአን 10.36-37፡፡

‹ሰዎችም ጋኔኖችም የዚህን ቁርአን ብጤ በማምጣት ላይ ቢሰበሰቡ ከፊላቸው ለከፊሉ ረዳት ቢኾንም እንኳ ብጤውን አያመጡም በላቸው፡፡› ቁርአን 17.88፡፡

በሌላ አነጋገር እናንተ የቁርአንን አንድ ምዕራፍ ዓይነት መጻፍ ካልቻላችሁ መጠራጠራችሁን በማቆም ቁርአን ከመለኮታዊው እግዚአብሔር የመጣ ነው ብላችሁ መቀበል አለባችሁ ነው፡፡ በእኔ አመለካከት ይህ የእስልምና እጅግ ጠንካራው መከራከሪያ ነጥብ ነው፡፡ ብዙ ሙስሊሞች ይህንን ላይቀበሉት ይችሉ ይሆናል (በዚህ ሐሳብ ላይስማሙ ይችሉ ይሆናል) ነገር ግን መሐመድ እራሱ የተጠቀመበት መከራከሪያ ይህ ስለሆነ፣ ሙስሊሞች ለዚህ ነጥብ ታላቅ ክብርን መስጠት አለባቸው (ማለትም መሐመድ የተጠቀመበትን መከራከሪያ ከራሳቸው ሐሳብ በላይ አድርገው መውሰድ ይኖርባቸዋል)፡፡ በተጨማሪም ከተጠቀሱት ጥቅሶች እንደምናየው ከሆነ እስልምና ከማያምኑት ሰዎች በጥያቄ ውስጥ በሚገባበት ጊዜ ሙስሊሞች እንዲከራከሩበት የተሰጣቸው መከራከሪያ ማለትም የታዘዙበት ይህ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህም መሐመድ የእግዚአብሔር ታላቅ ነቢይ ነው ብለን የምናስብ ከሆነ ሌላው ልንገምተው የሚገባን ነገር እሱ የእስልምና ጠንካራው መከራከሪያ የትኛው ነጥብ እንደሆነም ያውቃል ብለን በማመን መሆን ይኖርበታል፡፡

መከራከሪያ ነጥቦችን ለመገምገም ከተፈለገ ብዙ ጊዜ ሊረዳን የሚችለው ነገር ነጥቦቹን በቅደም ተከተላዊ መንገድ የማስቀመጥ አስፈላጊነት ነው፡፡ በእስልምና በኩል (ልክ በክርስትና እንደሚሆነው ሁሉ) ዋናው መከራከሪያ ነጥብ የሚሆነው ነገር የሚቀመጠው ከአጠቃላይ ወደ ዝርዝር በሚወረድ ትንተና (በሲሎጊስቲክ) መንገድ ሲሆን የሚታወቀውም ‹ሞደስ ፖነንስ› በመባል ነው፡፡ በዚህ መርሆ መሠረት ሲቀመጥ የእስልምና ጠንካራ መከራከሪያ የሚሆነው እንደሚከተለው ነው፡-

1. መሠረተ ሐሳብ አንድ፡- የማያምኑት በቁርዓን ውስጥ ያለውን አንድ ምዕራፍ ዓይነት የማያመጡ ከሆነ (ማምጣት የማይችሉ ከሆነ) ቁርአን ከእግዚአብሔር ነው ማለት ነው፡፡

2. መሠረተ ሐሳብ ሁለት፡- የማያምኑት በቁርአን ላይ ያለውን አንድ ምዕራፍ ዓይነት ማምጣት አይችሉም (መፍጠር አይችሉም)፡፡

3. መደምደሚያ፡- ስለዚህም ቁርአን ከእግዚአብሔር መሆን አለበት፡፡

‹ሲሎጊስቲክ› ዓይነት ክርክር ብዙውን ጊዜ ጠቃሚ ነው ምክንያቱም እያንዳንዱን መሠረተ ሐሳብ በነጠላ እንድንመረምር እድል ይሰጠንና የተሰጠው መደምደሚያ ትክክል ነው አይደለም የሚለውን እንድናጠና (እንድናውቅ) ይረዳናል፡፡ ለሙስሊሞች መከራከሪያ ይህንን ዘዴ ስንጠቀም የምናገኘው የእስልምና ነገር እና ክርክር በእውነት እንዴት በጣም ደካማ እንደሆነ ማስተዋል ችለን ነው፡፡ ለምሳሌ የመጀመሪያውን መሠረተ ሐሳብ ተመልከቱ፡ ‹የማያምኑት በቁርአን ውስጥ ያለውን አንድ ምዕራፍ ዓይነት መስጠት የማይችሉ ከሆነ ቁርአን ከእግዚአብሔር መሆን አለበት›፡፡ በመሠረቱ ቁርአን ከመለኮት የመጣ ነው ብለው ለመናገር የሙስሊሞች አንዱ መለያ መስፈርት የስነ ጽሑፍ ይዘቱ ውብ ነው በማለት ነው፡፡ አስተውሉ ይህም ማለት ‹እናንተ እንደ ተ.ኤስ ኤሊዮት ዓይነትን ግጥም መግጠም ካልቻላችሁ ወይንም እንደ ሸክስፒር ዓይነት ድራማ ወይንም የቻርልስ ዲከንስን ዓይነት ልብ ወለድ ካልደረሳችሁ፣ ስለዚህም ማመንና መቀበል ያለባችሁ የእነሱ ስራ ከእግዚአብሔር የመጣ መሆኑን ነው› ማለት ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ክርክር ዋጋ ቢስ ነው የሚመስለው ነገር ግን ቁርአን ጋ ስንመጣ ሙስሊሞች የሚሉት በትክክል እንዲህ ዓይነት አካሄድን ነው፡፡

ስለዚህም የሙስሊሞች መከራከሪያ የሆነው የመጀመሪያው መሠረተ ሐሳብ ስህተት ነው (ይህንን የምንቀበል ከሆነ በዓለም ላይ ያሉት ታላላቅ ጸሐፊዎችና ባለቅኔዎች ስራ ሁሉ ከእግዚአብሔር ነው ወደሚል አመለካከት ውስጥ እንገባለን ወይንም ለዚህ ዓይነት ሐሳብ ክፍት እንሆናለን ማለት ነው)፡፡ በመሆኑም በስነ ጽሑፍ ውበት ሁኔታና በመለኮት ምንጭነት መካከል ምንም ዓይነት ግንኙነት ያለ አይመስልም፡፡ ስለዚህም የሙስሊሞች መከራከሪያ ዋናውና አንዱ መሠረተ ሐሳብ ስህተት ስለሆነ (ወይንም ይህንን ለማረጋገጥ በጣምም በዝቅተኛው ደረጃ የማይቻል ስለሆነ) አጠቃላይ የመከራከሪያው ሐሳብ ውድቅ ነው ወይንም በጭራሽ ተቀባይነት የለውም፡፡ ሁለተኛው መከራከሪያም እንደዚሁ እጅግ በጣም ችግር ያለበት ነው፡፡ ሁለተኛው ሐሳብ የሚለው ‹የማያምኑቱ የቁርአንን አንድ ምዕራፍ የሚመስልን ማምጣት አይችሉም ነው›፡፡ ብዙ ሰዎች ቁርአንን ለማንበብ ከፍተውት በጭራሽ አያውቁም ስለዚህም እዚህ ጋ አራት ተከታታይ ምዕራፎችን እንድታነብቡ አደርጋለሁ (ነገር ግን እነዚህ ምዕራፎች እጅግ አጫጭር ናቸው)፡፡

‹በአላህ ስም እጅግ በጣም ርኅሩኅ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡ እኛ በጣም ብዙ በጎ ነገሮችን ሰጠንህ፡፡ ስለዚህ ለጌታህ ስገድ (በስሙ) ሠዋም፡፡ ጠይህ (የሚጠላህ) እርሱ በእርግጥ (ዘሩ) የተቆረጠው ነው፡፡› ምዕራፍ 108፡፡

‹በአላህ ስም እጅግ በጣም ርኅሩኅ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡ በላቸው፡- እላንተ ከሐዲዎች ሆይ ያንን የምትገዙትን (ጣዖት አሁን) አልገዛም፡፡ እናንተም እኔ የምገዛውን (አምላክ አሁን) ተገዢዎች አይደላችሁም፡፡ እኔም ያንን የተገዛችሁትን (ወደፊት) ተገዢ አይደለሁም፡፡ እናንተም እኔ የምገዛውን (ወደፊት) ተገዢዎች አይደላችሁም፡፡ ለናንተ ሃይማኖታችሁ አላችሁ ለኔም ሃይማኖቴ አለኝ፡፡› ምዕራፍ 109፡፡

‹በአላህ ስም እጅግ በጣም ርኅሩኅ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡ የአላህ እርዳታና (መካን) መክፈት በመጣ ጊዜ፤ ሰዎችንም ጭፍሮች እየኾኑ በአላህ ሃይማኖት ውስጥ ሲገቡ ባየህ ጊዜ፤ ጌታህን ከማመስገን ጋር አጥራው ምሕረትንም ለምነው እርሱ ጸጸትን በጣም ተቀባይ ነውና፡፡› ምዕራፍ 110፡፡

‹በአላህ ስም እጅግ በጣም ርኅሩኅ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡ የአቡ ለሀብ ሁለት እጆች ከሰሩ (ጠፉ እርሱ) ከሰረም፡፡ ከርሱ ገንዘብና ያም ያፈራው ሁሉ ምንም አልጠቀመውም፡፡ የመንቀልቀል ባለቤት የኾነችን እሳት በእርግጥ ይገባል፡፡ ሚስቱም (ትገባለች) እንጨት ተሸካሚ ስትኾን፤ በአንገትዋ ላይ ከጭረት የኾነ ገመድ ያለባት ስትኾን፡፡› ምዕራፍ 111፡፡

እዚህ አራቱ የመሐመድ ሱራዎች (ምዕራፎች) አሉን፡፡ እነዚህም በቁርአን መሠረት መሆን ያለባቸው ከተጻፉ ማናቸውም ነገሮች (ጽሑፎች) ሁሉ በደረጃቸው እጅግ በጣም የላቁ ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ላይ አንድ ተዓምራታዊ የሆነ ነገር ይኖራልን? በእነዚህ አንቀፆች ውስጥ አንድ ሊታመን የማይቻል ወይንም አንድ አስደናቂ ነገር በመኖሩ የሰው ልጆች መለኮታዊ ምንጭነታቸውን ለመቀበል የግድ ሊባሉባቸው ይችላሉን? በፍፁም ምንም ነገር የለባቸውም፡፡ እነዚህ ቃላት በማንም ሰው ሊጻፉ የሚችሉ ቃላት ብቻ ናቸው፡፡ በእርግጥ በእነዚህ ቃላት ውስጥ ያለው አንድ አስደናቂ ወይንም ልዩ ነገር ቢኖር እጅግ በጣም ምንም የማይስቡ መሆናቸው ነው (ይህም ስለ እነሱ ከተጠየቀው ጥያቄ አኳያ ስናያቸው ነው)፡፡

ሙስሊሞች እነዚህ አንቀፆች የአረብኛው የእንግሊዝኛ ትርጉም ስለሆነ ነው በማለት ሊከራከሩ ይችሉ ይሆናል ማለትም የቁርአን ተዓምራታዊ ተፈጥሮ ሊታይ የሚችለው በአረብኛው የመጀመሪያው ቋንቋ ብቻ ነው ይላሉ፡፡ ይሁን እንጂ ይህም ነገር እንድናተኩር የሚገፋፋን ቁርአን ተዓምራታዊ የሚሆነው በስነ ጽሑፍ ሁኔታው ብቻ ነው እንጂ በይዘቱ አይደለም ወደሚል ነው፡፡ የቁርአን ይዘትና ትርጉም ወደ ሌሎች ቋንቋዎች ሊተረጎም ይችላል ነገር ግን የስነ ጽሑፍ ስነ ዘዴ (ስታይል) ግን በትርጉም ለማስቀመጥ አስቸጋሪ ነው፡፡ ስለዚህም ቁርአን ልዩ የሆነው በስነ ጽሑፍ ስነ ዘዴው ብቻ ከሆነ እና በይዘተ-ትርጉሙ ካልሆነ የምንመለሰው ወደ ሼክስፒርና ዲክንስ ዓይነት ጽሑፍ ነው፡፡ ስለዚህም እጅግ ግሩም የሆኑት የጸሐፊዎች የጽሑፍ ስራዎች በሙስሊሞች መለኮታዊ ምንጭ አላቸው ተብለው የማይቆጠሩት ለምንድነው?

በሙስሊሞች ምላሽ ሌላው ችግር የሚሆነው እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ ስራዎች ትርጉም ያላቸው እና ውብ የሆኑ ከሌሎች ቋንቋዎች ወደ እንግሊዝኛ ተተርጉመዋል ነገር ግን እነዚህን ውብ እና ግሩም ገፅታዎቻቸውን ይዘው ተቀምጠዋል፡፡ ለምሳሌ የሚከተለውን ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተወሰደውን አንቀፅ አስተውሉ፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ አለ፡-

‹በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮኽ ናስ ወይም እንደሚንሽዋሽዋ ጸናጽል ሆኜአለሁ። ትንቢትም ቢኖረኝ ምሥጢርንም ሁሉና እውቀትን ሁሉ ባውቅ፥ ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ እምነት ሁሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ። ድሆችንም ልመግብ ያለኝን ሁሉ ባካፍል፥ ሥጋዬንም ለእሳት መቃጠል አሳልፌ ብሰጥ ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም። ፍቅር ይታገሣል፥ ቸርነትንም ያደርጋል፤ ፍቅር አይቀናም፤ ፍቅር አይመካም፥ አይታበይም፤ የማይገባውን አያደርግም፥ የራሱንም አይፈልግም፥ አይበሳጭም፥ በደልን አይቆጥርም፤ ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል እንጂ ስለ ዓመፃ ደስ አይለውም፤ ሁሉን ይታገሣል፥ ሁሉን ያምናል፥ ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፥ በሁሉ ይጸናል። ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም፤ ትንቢት ቢሆን ግን ይሻራል፤ ልሳኖች ቢሆኑ ይቀራሉ፤ እውቀትም ቢሆን ይሻራል። ከእውቀት ከፍለን እናውቃለንና፥ ከትንቢትም ከፍለን እንናገራለንና፤ ፍጹም የሆነ ሲመጣ ግን ተከፍሎ የነበረው ይሻራል። ልጅ ሳለሁ እንደ ልጅ እናገር ነበር፥ እንደ ልጅም አስብ ነበር፥ እንደ ልጅም እቈጥር ነበር፤ ጎልማሳ ሆኜ ግን የልጅነትን ጠባይ ሽሬአለሁ። ዛሬስ በመስተዋት በድንግዝግዝ እንደምናይ ነን በዚያን ጊዜ ግን ፊት ለፊት እናያለን፤ ዛሬስ ከእውቀት ከፍዬ አውቃለሁ በዚያን ጊዜ ግን እኔ ደግሞ እንደ ታወቅሁ አውቃለሁ። እንዲህም ከሆነ፥ እምነት ተስፋ ፍቅር እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ፤ ከእነዚህም የሚበልጠው ፍቅር ነው።› 1ቆሮንቶስ 13.1-13፡፡

እዚህ ጋ ያሉት የጳውሎስ ቃላት ውበትም ትርጉምም ያላቸው፣ ሁለቱንም ናቸው ይህ ደግሞ ከግሪኩም ከተተረጎሙም እንኳን በኋላ ነው፡፡ በእርግጥ አንድ ሰው ይህ አንቀፅ ከቁራን ከጠቀስኩት እጅግ በጣም የበለጠ ነው በማለት ሊከራከር ይችላል ምክንያቱም እጅግ በጣም ትርጉም ያለው ነውና ከተተረጎመም እንኳን በኋላ እጅግ በጣም ውብ ነውና፡፡ ይህንን መከራከሪያ ማንኛውም የክርስትያን ተከራካሪ አይጠቀምበትም ምክንያቱም የስነ ጽሑፍ ስነ ዘዴ መከራከሪያነት ከዚህ በላይ እንዳየነው በውስጣቸው ደካማ መከራከሪያዎች ናቸውና፡፡

ስለዚህም የእስልምና ፍትሐዊነት በመጀመሪያ የተቀመጠው በሲሎጂዝም ላይ ሲሆን መሠረቱም ሁለት ስህተት የሆኑ መከራከሪያ ነጥቦች ናቸው፡፡ ሰዎች በእንደዚህ ዓይነት ማስረጃ ባለው ክርክር ምን ያህል እንደሚያምኑ መገመት እጅግ አስቸጋሪ ነው የሚሆነው፤ ነገር ግን እስልምና አስደናቂ በሆነ መንገድ ባለፉት አስራ ሦስት ምዕተ ዓመታት አድጓል በመሆኑም አሁን በዓለም ላይ ሁለተኛው ትልቅ ሃይማኖት ሆኗል፡፡ ይሁን እንጂ በጣም ትልቁ ሃይማኖት ክርስትና ነው የተመሠረተውም በተለየ አስተምህሮ ላይ ነው፡፡

በጣም በተለያዩ አጋጣሚዎች፣ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የተነበያቸው እሱ ከሞት እንደሚነሳ ነው፡- ‹ከዚያን ቀን ጀምሮ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ይሄድ ዘንድ ከሽማግሎችና ከካህናት አለቆች ከጻፎችም ብዙ መከራ ይቀበልና ይገደል ዘንድ በሦስተኛውም ቀን ይነሣ ዘንድ እንዲገባው ለደቀ መዛሙርቱ ይገልጥላቸው ጀመር።› ማቴዎስ 16.21 22

‹በገሊላም ሲመላለሱ ኢየሱስ። የሰው ልጅ በሰዎች እጅ አልፎ ይሰጥ ዘንድ አለው፥ ይገድሉትማል፥ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል አላቸው። እጅግም አዘኑ።› ማቴዎስ 17.22-23፡፡

‹ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ሊወጣ ሳለ፥ በመንገድ አሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርት ብቻቸውን ወደ እርሱ አቅርቦ። እነሆ፥ ወደ ኢየሩሳሌም እንወጣለን፥ የሰው ልጅም ለካህናት አለቆችና ለጻፎች ይሰጣል፤ የሞት ፍርድም ይፈርዱበታል፥ ሊዘባበቱበትም ሊገርፉትም ሊሰቅሉትም ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታል፥ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል አላቸው።› ማቴዎስ 20.17-19፡፡

ጠላቶቹ ምልክትን እንዲያሳያቸው በጠየቁት ጊዜ ጌታ ኢየሱስ እንደገና ስለመነሳቱ ትንቢትን ተናግሯቸው ነበር፡-

‹ስለዚህ አይሁድ መልሰው። ይህን ስለምታደርግ ምን ምልክት ታሳየናለህ? አሉት ኢየሱስም መልሶ። ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፥ በሦስት ቀንም አነሣዋለሁ አላቸው።› ዮሐንስ 2.18-19፡፡

የኢየሱስ አድማጮች ቆይተው የተረዱት ነገር ጌታ ኢየሱስ ቤተመቅደስ በማለት የተናገለት የእራሱን ሰውነት እንደሆነ ነው ዮሐንስ 2.21-22፡፡

በተጨማሪም ሐዋርያው ጳውሎስ የጌታ የኢየሱስን ትንሳኤ የክርስትና እምነት ማስረጃ አድርጎ ተናግሮበታል፡፡ በሐዋርያት ሥራ 17፤ ጳውሎስ የተናገረው፡ ‹ቀን ቀጥሮአልና፥ በዚያም ቀን ባዘጋጀው ሰው እጅ በዓለሙ ላይ በጽድቅ ሊፈርድ አለው፤ ስለዚህም እርሱን ከሙታን በማስነሣቱ ሁሉን አረጋግጦአል።› ሐዋርያት 17.31፡፡ እነዚህን የመከራከሪያ ነጥቦች በሎጂካዊ መልክ በማስቀመጥ ወደሚከተለው ነገር ላይ እንመጣለን፡-

1. መሠረታዊ ነጥብ አንድ፡- ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት ከተነሳ የእሱ መልእክት ከእግዚአብሔር ነበር፡፡

2. መሠረታዊ ነጥብ ሁለት፡- ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት ተነስቷል

3. መሠረታዊ ነጥብ ሦስት፡- ስለዚህም የእሱ መልክት ከእግዚአብሔር ነበር፡፡

መሐመድ አስደናቂ የሆነ የስነ ጽሑፍ ዓይነት መጽሐፉ ከመለኮት የመጣ ለመሆኑ ማስረጃ ነው በማለት ሲከራከር፣ ኢየሱስና ጳውሎስ የተናገሩት ቅዱስ መጽሐፍ ከመለኮት የመሆኑ ማስረጃ ትንሳኤ ነው በማለት ነው፡፡ የመጀመሪያው የክርስትና መከራከሪያ ዋና ሐሳብ እውነታ እራሱ በራሱ ማረጋገጫን የሚሰጥ ነው፡፡ አንድ ሰው ጌታ ኢየሱስ ሰዎችን ከሞት በማስነሳቱ ዙሪያ ላይ ተቃውሞን ሊያስነሳ ይችላል (ላይቀበለው ይችላል) እናም እነዚህ ሰዎች (ከሞት የተነሱት) ከእግዚአብሔር መልእክት አላቸው በማለት መደምደሚያን ልንሰጥ አንችልም፡፡ ነገር ግን ይህ ዋናውን ነጥብ ይጥለዋል፡፡ የጌታ ኢየሱስ ከሞት መነሳት ከሌሎቹ ሰዎች የተለየ ነው ምክንያቱም እሱ ስለ እራሱ አንዳንድ እጅግ በጣም ልዩ የሆኑ ነገሮችን ተናግሯል፤ አንዳንዶቹም በሙስሊሞችም እንኳን ተቀባይነትን አግኝተዋል፡፡ ሙስሊሞች እራሳቸው ኢየሱስ ከድንግል መወለዱን፤ ያለምንም ኃጢአት የኖረ መሆኑን፤ ተዓምራትን ማድረጉን እና መሢህ መሆኑን ያምናሉ፡፡ ኢየሱስም እራሱ ለተናገረው ነገር ማስረጃ ለመሆኑ እሱ እራሱ ከሞት እንደሚነሳ ትንቢትን ተናግሯል እሱ የተናገረውም ትንቢት ደግሞ እውነት ሆኗል፡፡ ስለዚህም አሁን እኛ የምንጠይቀው ጥያቄ፡ ‹እግዚአብሔር ሐሰት አስተማሪን ከሞት ያነሳዋልን?› በማለት ነው፡፡ እኔ እንደሚመስለኝ ክርስትያኖችም ሙስሊሞችም የሚስማሙበት ሐሳብ እግዚአብሔር ሐሰት አስተማሪን ከሞት እንደማያስነሳ ነው፡፡ ስለሆነም የክርስቶስ ጥያቄ የሐሰት አስተምህሮ ካልሆነ ምን ሊሆን ይችል ነበር? እነሱ እውነቶች መሆን አለባቸው፡፡ ስለዚህም የመጀመሪያው ዋና ሐሳብ ስለ እግዚአብሔር በምናውቀው ነገር መሠረት ትክክለኛ ስሜትን የሚሰጥ ነው፡፡

ይህ ደግሞ ወደ ሁለተኛው ዋና ሐሳብ ያመጣናል፡ ‹ኢየሱስ ከሞት ተነስቷል› ከመጀመሪያው ዋና ሐሳብ በተለየ መልኩ ይህኛው እራሱን በራሱ የሚያረጋግጥ አይደለም፡፡ ይህ የታሪክን ምርመራ የሚጠይቅ ነገር ነው፡፡ የሚገርመው ነገር የክርስቶስን ትንሳኤ አስመልክቶ ያለው ታሪካዊ ማስረጃ እጅግ በጣም ጥሩ ነው፡፡ ወደ ክርስቶስ ሞትና ትንሳኤ ስንመጣ እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ ታሪካዊ ማስረጃዎች አሉ፡፡ እነሱም አንድ ላይ ሲገናኙ ሊያስረዱ የሚችሉት ነገር ኢየሱስ በአካል ከሞት የተነሳ መሆኑን ብቻ ነው፡፡ ለምሳሌም በዶክተር ጋሪ ሃበርማስ የተቀናበረውን የሚከተለውን ታሪካዊ እውነታ ዝርዝር ተመልከቱ፡

1. ኢየሱስ የሞተው በስቅላት ስቃይ የተነሳ ነው፡፡

2. ኢየሱስ ከሞተ በኋላ ተቀበረ፡፡

3. የእሱም ሞት ደቀመዛምርቱን ተስፋ እንዲቆርጡና ከሁኔታውም የተነሳ እንዲታወኩ አድርጓቸዋል፡፡

4. ምንም እንኳን ከሌሎቹ ግኝቶች ጋር በአንድ መልክ ባይታይም፤ ብዙዎቹ ሊቃውንት የሚያምኑት ክርስቶስ ተቀብሮበት የነበረው መቃብር ከጥቂት ቀናት በኋላ ባዶ ሆኖ መገኝቱን ነው፡፡ ይህም ደግሞ የትንሳኤን እውነትነት የሚያጣጥሉ ተቺዎች ሊቃውንትም እንኳን የተቀበሉት ነገር ነው፡፡

5. ያም ደቀመዛምርቱ የኢየሱስን በአካል ከሞት መነሳት አምነው በሕይወታቸው በእውነት እንደተረዱት ነው፡፡

6. ይህ እውነታን የመረዳት ልምድ ደቀመዛምርቱን በሃፍረት ከተሞሉ ተከታዮች እና ከፍርሃት አውጥቷቸው ከኢየሱስ ጋር አንድ በመሆን የሞቱንና የትንሳኤውን ደፋር ተናጋሪዎች (ሰባኪዎች) አድርጎ ቀይሯቸዋል፡፡ ይህም ለዚህ እውነት ለሆነ እምነትም ለመሞትም እንኳን ፈቃደኛ በመሆን ነው፡፡

7. ይህ የትንሳኤ ስብከት የጥንት ክርስትና እምነት ዋና ማዕከላዊ መልእክት ነበር፡፡ እንደዚሁም ደግሞ ይህ ትንሳኤ፤

8. ኢየሱስ ከጥቂት ቀናት በፊት በሞተበት ከተማ፤ በተለይም በኢየሰሩሳሌም ተሰብኮ ነበር

ስለዚህም

9. የክርስትያን ቤተክርስትያን ተመስርታ አደገች፡፡

10. እሁድንም የትንሳኤውን ቀን የአምልኮዋ ዋና ቀን አደረገች፡፡

11. ከሞት የተነሳውን ኢየሱስን ካየ በኋላ ተጠራጣሪው የነበረው የጌታ ወንድም ያዕቆብም አምኖ ተለወጠ

12. የቤተክርስትያን ዋና አሳዳጅ የነበረው የጠርሴሱ ሳውል ከጥቂት ዓመታት በኋላ ክርስትያን ሆነ ይህም የሆነው ከሞት የተነሳውን ኢየሱስ ክርስቶስን ካየ በኋላ ነበር፡፡

እነዚህ ከላይ ያየናቸው እውነቶች በሙሉ በሁሉም ሊቃውንት ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው ናቸው ይህም ከሚከተሉት የተለያየ የስነ መለኮት አመለካከት ልዩነት ውጪ ነው፡፡ አስተውሉ የሙስሊም አቋም በታሪክ ማስረጃ ተሰጥቶት ለመረጋገጥ እና ለማስታረቅ የማይቻል ሲሆን፤ ክርስትና ግን እውነቶቹን ሁሉ በትክክል የሚገጣጥም ነው፡፡ ይህንን ጉዳይ እጅግ በጣም ጠለቅ ባለ ሁኔታ ልንመረምረው እንችላለን፣ ነገር ግን ይህንን ማድረግ ከዚህ አንቀፅ ክልል ውጭ ነው፡፡

እዚህ ጋ መነሳት ያለበት ነጥብ የእስልምና ዋና መከራከሪያ ነጥብ የተመሠረተው በሁለት የሐሰት ዋና ሐሳቦች ላይ ሆኖ እያለ የክርስትና ዋና መሠታዊ ነጥብ ግን የተመሠረተው አንድ እራሱን በሚያረጋግጥ ማስረጃ እና ሌላው ደግሞ በታሪክ ምርመራ በሚረጋገጥ ዋና ሐሳብ (ማስረጃ) ላይ መሆኑ ነው፡፡ ይህም የሚያስረዳን ጥንቃቄ በተሞላበት የማስረጃዎች ምርመራ አማካኝነት ክርስትና እውነት መሆን እና አለመሆኑን ማወቅ እንችላለን ማለት ነው፡፡ ነገር ግን እስልምና ይህንን የመሰለ ማስረጃ በማቅረብ በፍፁም ሊከራከር የሚችለበት ምንም ነገር የለውም፡፡ ስለዚህም በእውነተኛ ማስረጃ ላይ የተደገፈ እምነት እንዲኖረው የሚፈልግ ማንም ሰው ቢኖር መምጣት ያለበት ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ክርስትና ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም የክርስትና እምነት፤ እራሱን የሚገልጠው በታሪካዊ ክስተቶች ላይ እንደተመሰረተ እና እራሱንም ለእንደዚህ ዓይነት ምርመራዎች ክፍት እንዳደረገ ነው፡፡ በተጨማሪም ደግሞ አሳማኝ ምክንያት ላይ የተመሠረተን እምነት የሚፈልጉ ምንም ዓይነት ሰዎች ቢኖሩ ዓይናቸውን ከእስልምና ላይ በማንሳት መመልከት ያለባቸው ወደ ሌላ ቦታ መሆን እንዳለበት ነው፡፡ ወደዳችሁም ጠላችሁም እስልምና በየትኛውም ደረጃው ጠንካራ መከራከሪያ ነጥቦች የሉትም፣ እናም እራሱን ሁልጊዜ የሚጥለው ከክርስትና ጋር በመጋጨት ላይ ነው፡፡

ወደ ማስረጃ በሚመጣበት ጊዜ የጌታ ኢየሱስ ትንሳኤ የማስረጃ ሰጪ ተከራካሪዎች የኤቨርሰት ተራራ ነው፡፡ ሙስሊሞች ብዙውን ጊዜ ይህንን ማስረጃ ይዘጉታል (ይክዱታል) ይህም እነሱ ከእስልምና ጋር በጣም ቅርብ በመሆናቸው ከክርስትና ጋር ሲያወዳድሩት ትንሽ መስሎ ስለሚታያቸው ብቻ ነው፡፡ ሙስሊሞች የሚኖሩት በግማሽ ጨረቃ ነው ስለዚህም ትልቅ መስሎ ይታያቸዋል ይህም በዓይን ማየት ከማይታየውና ዓለምን ሁሉ የሚሞላ ብርሃን ፀዳል ካለው ከእግዚአብሔር ልጅ የበለጠ እጅግ በጣም ትልቅ እንደሆነ ቆጥረው ነው፡፡ ይሁን እንጂ በእስላሞች የተጀመረው የዚህ የአመለካከት መምታታት እውነታውን ሊለውጠው አይችልም፡፡ የናዝሬቱ ኢየሱስ በመስቀል ላይ ለኃጢአታችን ሞቶ ተነስቷል ይህም የክርስትና እምነትን መልእክት እውነት መሆኑን አረጋግጧል፡፡ በሚያሳዝን ሁኔታ የክርስትና እምነት ማስረጃዎች ወደ ፊት እየገፉ (እውነትነታቸው እያበራ) ብዙ ሙስሊሞች ከዚህ እውነት በተቻለ መጠን ሲሸሹ (ሲርቁ) ይታያሉ፡፡ በጉዞ ላይ በተቀመጡበት መቀመጫና ከቁርአን ጋር በመሆን ወደ ኋላ በሚያሳይ መስተዋት ወደ ኢየሱስ ይመለከቱና ‹ደህና እሱ በጣም ትልቅ አይደለም› በማለት ያስባሉ፡፡ ነገር ግን እጅግ በጣም መጠንቀቅ አለባቸው፡፡ በመስተዋት ውስጥ የሚታዩ ነገሮች (ምስሎች) በእውነት ከሆኑት ይልቅ በጣም ቅርብ መስለው ይታያሉና፡፡

የአዘጋጁ ማሳሰቢያ፡-

ከዚህ በላይ ባየነው ሎጂካዊ አካሄድ መሠረት የክርስትና የትንሳኤ መሠረት የሚያሳምን ነው፡፡ ሰዎች ወደ ፊት የሚመጣ የትንሳኤ ሕይወት ተስፋ መሠረታቸው የክርስቶስ ትንሳኤ ነው፡፡ የክርስቶስ ትንሳኤ ደግሞ በትክክል የሆነና በታሪክም የተረጋገጠለት ነው፡፡ አንባቢ ይህንን በሚገባና በትክክል ካስተዋለ የሚከተሉትን ጥያቄዎች እንዲያስብባቸው ይጠየቃል፡፡ የትንሳኤ ሕይወት እንዳለ ታምናላችሁን? የምታምኑ ከሆነ በትንሳኤ የምትገቡበት ቦታ የት ነው? ይህስ ተስፋችሁ የተመሠረተው በምን ላይ ነው? የክርስትያኖች የትንሳኤ ተስፋ የተመሠረተው በክርስቶስ ኢየሱስ የትንሳኤ እውነታ ላይ ነው፡፡ እነዚህ ጥያቄዎች መሠረታዊ ናቸው። ትክክለኛ መልሳቸውንም ለማግኘት መጽሐፍ ቅዱስን በማግኘት ዛሬውኑ ማንበብን ይጀምሩ፡፡

 

የትርጉም ምንጭ: Islam’s Rule of Thumb: The Resurrection Versus the Qur’an In the Light of Logic by David Wood

ለእስልምና መልስ አማርኛ  ዋናው ገጽ