መጽሐፍ ቅዱስንና ቁርአንን ማወዳደር
(በትክክል ልናደርግ የምንችለው እንዴት ነው?)
በSamuel Green
ትርጉምና ቅንብር በአዘጋጁ
ክርስትያኖችና ሙስሊሞች በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ በሚነጋገሩበት ጊዜ በአብዛኛው መጽሐፍ ቅዱስና ቁርአን ሲወዳደሩ ይታያል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስና ቁርአንም በሚከተሉት መንገዶች ይወዳደራሉ፡-
- የመጽሐፎቹ ተጠብቆ የመቆየት ጉዳይ
- ቅዱስ መጽሐፍ ሆነው የመወሰዳቸው ጉዳይ
- ስለ ኢየሱስ፣ ስለ ሴቶች እና ስለ ምፅዋት ወ.ዘተ ያሏቸው ትምህርቶች ጉዳይ
- ሳይንሳዊ ትክክለኛነታቸው ጉዳይ
እና በውስጣቸው ያሉ ቅራኔዎች ይገኙባቸዋል::
እንደዚህ ዓይነቶቹን መጽሐፍ ቅዱስን ከቁርአን ጋር ማወዳደሮች እኔም እራሴ ከዚህ በፊት አድርጌዋለሁኝ፡፡ ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስን ከቁርአን ጋር ማወዳደር በእርግጥ አሳሳችና ትክክልም ያልሆነ ጉዳይ ነው፡፡ ለዚህም ሁለት ዋና፣ ዋና ምክንያቶች አሉ፡፡
ምክንያት አንድ፡- የመጽሐፍ ቅዱስ እና የቁርአን ዓውድ
ቁርአን የጀመረውና የሚሽከረከረው በመሐመድ ሕይወት ዙሪያ ላይ ነው፡፡ መሐመድ የቁርአንን ቃላቶች ያስታወሳቸው (የተናገራቸው) በሕይወቱ ውስጥ ካገጠሙት የተለያዩ ሁኔታዎች የተነሳ ነው፣ ነገር ግን እነዚህ ሁኔታዎች ምን እንደነበሩ በቁርአን ውስጥ አልተመዘገቡም፡፡ ያም ቁርአን የራሱን ዓውድ ወይንም ቅደም ተከተል አይሰጥም ማለት ነው፡፡ ቁርአንን በትክክል ለመረዳት ትክክለኛውን ዓውድና ቅደም ተከተል መረዳት በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ነገር ግን ዓውዱን እና ቅደም ተከተሉን ለማወቅ ከቁርአን ውጪ ወደ እስላማዊ ልማዶች ውስጥ መሄድ ይኖርባችኋል - እነዚህም እንደ ሐዲት ወይንም ሲራ ጽሑፎች ማለት ነው፡፡ እነዚህ መጻሕፍት ለቁርአን ዓውድን ይሰጣሉ፡፡ እስላማዊው ሊቅ ሃቢብ ኡር ራህማን አዛሚ በግልፅ የተናገረው ቁርአን በሐዲትና በሲራ ላይ የተመሰረተ ነው በማለት ነው፡፡ ሃቢብ ኡር ራህማን እንዳለው፡-
‹ልማዶች እንደማይጠቅሙና ትክክለኞች አይደሉም ከተባለ እጅግ በጣም ብዙ የሆኑትን የቁርአንን ጥቅሶች ለመረዳትም ሆነ ለማብራራት በፍፁም አይቻልም፡፡› (Habib Ur Rahman Azami, The Sunnah in Islam, pp. 29-31.)
መጽሐፍ ቅዱስ ግን በጣም የተለየ ነው፡፡ እርሱ የራሱን ዓውድና ቅደም ተከተል ይሰጠናል፡፡ የእርሱም መገለጥ የጀመረው ከዘፍጥረት ሲሆን እስከ አዲሱ ፍጥረት ድረስ ያለውን ታሪክ ማለትም እስከ ትንሳኤ ድረስ ያለውን በትክክል (እራሱ መጽሐፍ ቅዱስ ያለሌላ ምንም ተጨማሪ ማገናዘቢያ ይናገራል) ያስረዳናል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የተለያዩ ትዕዛዞችን ወይንም የወንጌል አዋጆችን ሲያደርግ የሚያደርገው እራሱ በገለጠው በዓውዱ ውስጥ በመሆን ነው፡፡ ስለዚህም መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት የሚያስፈልጋችሁ ነገር መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እራሱ - በራሱ ብቁ የሆነ ነው፣ ይህም የእግዚአብሔር ቃል መሆን እንደሚገባው ነው፡፡ ስለዚህም መጽሐፍ ቅዱስን ከቁርአን ጋር ብቻ ማወዳደር አሳሳች ብቻ ሳይሆን ትክክልም አይደለም፡፡
ምክንያት ሁለት፡- ልምዶችና እምነቶች
ብዙዎቹ መሠረታዊ የእስልምና ልምምዶችና እምነቶች በቁርአን ውስጥ ያሉም ወይንም ቁርአን እነሱን አልያዘም፡፡ ስለዚህም፡-
ሱና (የመሐመድ ሕይወት ልምምድ) ለቁርአን አስፈላጊ የሆነ መሙያ ነው፡፡ ስለዚህም በእርግጥ በጣም የተለያዩ ማስረጃዎች (ምሳሌዎች) በሱና ውስጥ አሉ፡፡ እንዲያውም ሱና ከቁርአን የበለጠ የሆነባቸው ነገሮች አሉ፣ ለምሳሌም ቁርአን (በቀን ስለሚደረጉ) ስለ ሦስት የቀን ፀሎቶች ሲጠቅስ (በ24.58) ሱና ግን በቀን አምስት ፀሎቶችን ያስቀምጣል፡፡ በሌላ ጎኑ እስልምና እንደተጀመረ በአጠቃላይ ይደረጉ ከነበሩት ልምምዶች ውስጥ ከሱና ጋር የሚቃረኑ የሚመስሉ ጉዳዮችም አሉ፡፡ እንደዚሁም ደግሞ ቁርአን መሰረታዊም የሆኑትን ትዕዛዛቶቹንም እንኳን ሙሉ በሙሉ ግልፅ አያደርጋቸውም፡፡ ስለዚህም ቁርአን ስለ ፀሎት ያዛል ነገር ግን እንዴት መደረግ እንዳለበት አይናገርም፡፡ የፀሎት መልክ (ወይንም ሁኔታው) ድንጋጌውም (ሶላት) ሙሉ ለሙሉ የተመሠረተው በሱና ላይ ነው፡፡ (Cyril Glassé, "Sunnah", The Concise Encyclopedia of Islam, pp. 381-382)
ሶላህ (መደበኛ የተመለደው አምልኮ) መመስረት ግዴታዊው ትዕዛዝ የተገለጠው በቁርአን ውስጥ ነው አንዳንድ የሶላህ አስፈላጊ ነገሮች (እንደ ቂያም፣ ሩኩ፣ ሱጁድእና ቂራህ) ጭምር፡፡ ነገር ግን ሶላህን የማቅረብ ሁኔታ እራሱና ከእርሱ ጋር የተያያዙት እና መከናወን ያለባቸው የተለያዩት ነገሮች ሁሉ በቁርአን ውስጥ አልተገለጡም ነበር ... እንደዚሁም በተመሳሳይ መንገድ ወደ መካ የሚደረገው ጉዞ ማለትም ሐጂ እንደ ሃይማኖት ስራ ሆኖ በቁርአን ውስጥ ተነግሯል ነገር ግን እንዴት መደረግ እንዳለበት አልተገለጠም፡፡ ነቢዩ እራሱ ሐጂን በማድረግ ትክክለኛውን የማድረጊያውን መንገድ አሳይቷል (Habib Ur Rahman Azami, pp. 10-11)
በአል ኢርባድ ኢብን ሳሪያህ አስ-ሲላሚ የተተረከው እንደሚከተለው ነው፡- ... እነሱ ተሰበሰቡና ነቢዩ (ሰላም በእሱ ላይ ይሁን) በፀሎት መራቸው፣ ቆመና እንዲህ አለ፡ ከእናንተ በአልጋው ላይ ጋደም ሲል አላህ የከለከለው በቁርአን ላይ ብቻ የሚገኙትን ነው በማለት ይገምታልን? በአላህ፣ እኔ በቁርአን ውስጥ እንደሚገኙት ብዙ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ሰብኬያለሁ ትዕዛዝንም ሰጥቻለሁ በቁርአን ውስጥ እንደሚገኙት ያህል ወይንም ከዚያም የበለጠ ((Abu-Dawud: bk. 19, no. 3044, Hasan))፡፡
የእስልምና ሻሪያም (እንኳን) ሙሉ የሚሆነው ከቁርአን እና ከሱና ጋር ከተረዳዳ ብቻ ነው (Habib Ur Rahman Azami, p. 5)፡፡
እንዴት መቼና ምን መፀለይ እንዲሁም በሐጂ ጊዜ ምን ማድረግ፣ ግርዛት፣ የጊዜው ምልክቶች፣ በእርግጥ ብዙዎቹ የእስልምና አስፈላጊ ልምምዶች እና እምነቶች የመጡት ከሱና (ልምምድ) የመሐመድ (የሕይወት ልምምድ) ላይ ነው፡፡ ሱና ለእስልምና በጣም ጠቃሚ ነው ይሁን እንጂ ከቁርአን አልመጣም፣ ሱና የመጣው ከሐዲት እና ከሲራ ላይ ነው እንጂ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስንመጣ ግን እንደዚህ አይደለም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ክርስትያን የሚያስፈልገው ነገር ሁሉ አለው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እኛን ለማዳን እግዚአብሔር ያደረገውን ነገር ሁሉ ሙሉ ለሙሉ ይናገራል፣ እናም ለእራሱ ክብርን ለመስጠት እኛም እንዴት መኖር እንዳለብን ይናገራል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የእውቀታችን ሁሉ መሠረት ነው እንዲሁም (በእግዚአብሔር የምናገኘውን) ነፃነታችንን ምን እንደሆነ ይተረጉምልናል፡፡ ስለዚህም መጽሐፍ ቅዱስን ከቁርአን ብቻ ጋር ማወዳደር ስህተትና አሳሳች ነው፡፡
ትክክለኛው ማወዳደር
እዚህ ላይ አሁን ግልፅ መሆን ያለበት ነገር መጽሐፍ ቅዱስን ከቁርአን ጋር ማወዳደር ጥቅመ ቢስ መሆኑ ነው፡፡ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ የክርስትና መሰረት ሲሆን ቁርአን ግን የእስልምና መሰረት አይደለም፡፡ እስልምና የተመሰረተው በቁርአን፣ በሐዲት እና በሲራ ላይ ነው እንጂ፡፡ እናንተም በክርስትናና በእስልምና መጻሕፍት መካከል እውነተኛና ትክክለኛ ማወዳደር ለማድረግ የምትፈልጉ ከሆነ ማድረግ ያለባችሁ ከሁለቱም ሃይማኖቶች ጠቃሚ መጻሕፍት መሆን አለበት፡፡
አንዳንድ እውነታዎች በሐዲት ላይ
ሐዲት የሚለው ቃል ስለ አንድ ነገር ዘገባ ወይንም ዜና ማለት ነው፡፡ አንድ ሐዲት ከአንድ ዓረፍተ ነገር እስከ አንድ ሙሉ ገፅ በይዘቱ ሊለያይ ይችላል፡፡ በእስልምና እምነት የሐዲት ዋናው ጉዳይ ያለው መሐመድ በተናገረውና ባደረገው ነገር ላይ ነው፡፡ ማለትም ሐዲት የያዘው ሱናን ነው ማለት ነው፡፡ እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ የሐዲት ስብስቦች አሉ፣ እንደ ፕሮፌሰር ማሱድ አል-ሐሰን ገለጣ ዋናዎቹ ስብስቦች፡-
የታወቁት (እውቅና) የተሰጣቸው የሐዲት ስብስቦች በ ‹ሙስናፍ› (1) ምሳሌ የሚከተሉት ስብስቦች ናቸው፡-
1. አል ቡካሪ (870 ሒጂራ) (የ7658 ሐዲቶች ስብስብ)
2. ሙስሊም (875 ሒጂራ) የ7748 ሐዲቶች ስብስብ)
3. አቡ ዳውድ (875 ሒጂራ) (የ5276 ሐዲቶች ስብስብ)
4. አል ቲርሚዚ (892 ሒጂራ) (የ4415 ሐዲቶች ስብስብ)
5. አል-ናሳይ (915 ሒጂራ) (የ5776 ሐዲቶች ስብስብ)
6. ኢብን ማጃ (886 ሒጂራ) (የ4485 ሐዲቶች ስብስብ)
የአል-ቡካሪና የአል-ሙስሊም ስብስቦች ከሌሎቹ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ነው ያሉት የሚታወቁትም ‹አል-ሳሂሃይን› ተብለው ነው፣ ማለትም እውነተኞች እና ስልጣን ያላቸው ተብለው ነው፡፡
በጣም የታወቀው ስብስብ በ‹ሙስናድ› (2) ላይ ያለው ንድፈ ይዘት፣ የአሕመድ ኢብን ሐኒባል ስብስብ ነው (855 ሒጂራ)፡፡
በሐዲት ላይ ያለው የሺያ ስራዎች ነቢዩ የሰራውንና ያደረገውን ብቻ ዝም ብሎ አይጠቅስም፣ የሺያ ኢማሞች ያሉትንና ያደረጉትንም ይጠቅሳሉ እንጂ፡፡ የሺያ ስራዎች በሐዲት ላይ በሚከተሉት ስብስቦች ውስጥ ናቸው፡-
1. መሐመድ ኢብን ያቆብ አል-ኩሉኒ (939 ሒጂራ)
2. መሐመድ አል-ሁሚ (991 ሒጂራ)
3. ጣሒር ሰል-ሻሪፍ አል ሙርታዛ (1004 ሒጂራ)
4. ሙሐመድ አል-ቱሲ (1067 ሒጂራ) (Prof. Masud-ul-Hasan, History of Islam, vol. 1, p. 613)፡፡
እንደዚሁም ደግሞ የማሊክ ሙዋታ ጠቃሚ ስብስቦችም በተጨማሪ ይገኛሉ፡፡
የሲራ አንዳንድ እውነታዎች
ሲራዎች የመሐመድ የሕይወት ታሪኮች (ባዮግራፊዎች) ናቸው፡፡ እነዚህም የእሱን የሕይወት ቅደም ተከተል ዓውድ ይሰጣሉ፣ በዚህም ምክንያት የቁርአንን ዓውድና ቅደም ተከተልም ይሰጣሉ ማለት ነው፡፡ ሁለቱ ጥንታዊ ሲራዎች፡-
1. መሐመድ ኢብ ኢሻቅ (773) በኢብን ሂሻም በኩል (840 ሒጂራ) የክለሳ ስራ፣ Sirat Rasul Allah. (English translation 798 pages[3].)
2. መሐመድ ኢብን ሳዓድ (852 ሒጂራ) Kitab al-Tabaqat al-Kabir, (English translation, 1097 pages[4].)
እንደምታዩትና እንደምታነቡት በእስልምና እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ ጠቃሚ መጻሕፍት ይገኛሉ እነሱም ሁሉም ከቁርአን የበለጡ በጣም ትላልቆች ናቸው፡፡ ሁለቱ የቡካሪና የሙስሊም ሐዲቶች ከቁርአን 6236 ቁጥሮች የበለጠ ሐዲቶችን ይዘዋል፡፡ ከእስልምና ወደ ክርስትና በተመለሰው እስላማዊ ሊቅ የተነገረኝ ነገር እስልምና አስር በመቶ ቁርአንና ዘጠኛ በመቶ ልማድ ነው (ሐዲትና ሲራ)፡፡ ቁርአን እንደ ስዕል ፍሬም ነው፡፡ እርሱም አንዳንድ ዳራዎችን ይሰጣል፣ ነገር ግን የስዕሉ ዝርዝር ነገሮች የሚመጡት ከልማድ ውስጥ ነው፡፡
አንዳንድ ማገናዘቢያዎች፡-
አንደኛ፡- መጽሐፍ ቅዱስና ቁርአን ተመሳሳይ ናቸው ብላችሁ አታስቡ፡፡ ቁርአን ለሚናገረው ነገር ዓውድን አይሰጥም ወይንም የእስልምናን አስፈላጊ የሆኑትን ተግባራዊ ድርጊቶችን አይሰጥም፡፡ እነዚህ ነገሮች ሁሉ የመጡት ከሌሎች መጻሕፍት ውስጥ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ግን ለክርስትያን ልምምድና እምነት የሚያስፈልጉት ሁሉ ነገሮች አሉት፡፡ (ከውጪ የሚዋሰነው ምንም ነገር አያስፈልገውም)፡፡
ሁለተኛ፡- ክርስትያኖችና ሙስሊሞች፣ የመጽሐፍ ክፍሎች ተጠብቀው መቆየትን ጉዳይ፣ የካኖንን አመሰራረትን፣ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የሚሰጡ ትምህርቶችን፣ ሳይንሳዊ ትክክለኛነት እና ቅራኔዎችን በተመለከተ መጻሕፍትን ለማወዳደር ከፈለጉ፣ ሐዲትና ሲራም በማወዳደሩ ውስጥ መካተት ይኖርባቸዋል፡፡ ይህ ከተደረገ ውድድሩን ትክክለኛና ትርጉም ያለው ያደርገዋል፡፡ አንድ እስላማዊ መሪ መጽሐፍ ቅዱስን ብቻ ከቁርአን ጋር ሲያወዳድር ብትመለከቱ ይህ ብቁ ያልሆነ አካሄድና ደግሞም አሳሳች መሆኑን ለመናገር ድፍረት ይኑራችሁ፡፡
ሦስተኛ፡- በዜና ማሰራጫዎች ውስጥ እስላማዊ መሪዎች እና ሌሎችም ስለ አንዳንድ ልምምዶች ብዙ ጊዜ ይናገራሉ፡፡ ለምሳሌም ያህል የሴቶች መገረዝ ትክክል አይደለም ምክንያቱም በቁርአን ውስጥ የለምና ይላሉ፡፡ ይሁን እንጂ እንደዚህ ዓይነት አባባሎች በትክክለኛ መረጃ ላይ ያልተመሰረቱ ወይንም አሳሳቾች ናቸው፡፡ (ሆነ ተብለው ለማሳሳት የተደረጉ ናቸው)፡፡ ምክንያቱም እውነተኛው እስልምና በቁርአን ላይ አልተመሰረተምና፣ እስልምና የተመሰረተው በቁርአንና በሱና ላይ ነው እንጂ፡፡ በእርግጥ ቁርአን የሴቶችንም የወንዶችንም ግርዛት በተመለከተ ምንም የሚናገረው ነገር የለም፡፡ ስለ ግርዛት ቁርአን ምንም የሚናገረው ነገር የሌለው የመሆኑ ጉዳይ ግርዛትን የእስልምና ልምምድ ከመሆን አላገደውም ምክንያቱም የመጣው ከሱና ነውና፡፡
አራተኛ፡- እስልምና የተመሰረተው በብዙ መጻሕፍት ላይ ስለሆነ በጣም የተወሳሰበ ሃይማኖት ነው፡፡ መጻሕፍቱም እያንዳንዳቸው የየራሳቸው የሆነ የአጠናንና የሚነቀፉበት ጉዳዮች አሏቸው፡፡ ስለዚህም ከእነዚህ አስፈላጊ መጻሕፍት ጋር ሙስሊሞችን ማስተዋወቅ - የማይቻል ባይሆንም በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ በመሆኑም ውስብስቡን ነገር ቀላል ለማድረግ ብዙዎቹ ሙስሊሞች መታመን ያለባቸው በሊቃውንቶቻቸው ላይ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ግን (እንደዚያ አይደለም) ክርስትያኖች እንዲያነቡትና መልእክቱንም በቀላሉ መረዳት እንዲችሉ ተደርጎ ነው የተጻፈው፡፡ ስለዚህም እኛ ክርስትያኖች እንድትሆኑ ስንጋብዛችሁ የምንጠይቃችሁ መጽሐፍ ቅዱስን ብቻ እንድትቀበሉትና እንድታነቡት ነው፡፡
የአዘጋጁ ማሳሰቢያ
ከዚህ በላይ ያየነው ጽሑፍ ግልፅ እንዳደረገው መጽሐፍ ቅዱስን ከቁርአን ጋር ብቻ ማወዳደር ትክክል እንዳልሆነ ነው፡፡ ምክንያቱም ቁርአን እንደመጽሐፍ ቅዱስ እራሱን ችሎ ወጥ የሆነ መልእክትን ማስተላለፍ አይችልምና፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ ግን ወጥ መልእክት አለው ለሚያነቡትም ሁሉ ግልፅ ነው፡፡ በማንኛውም ዕድሜ፣ ፆታ፣ ትምህርት ደረጃ፣ ዘርና ጎሳ ለሚገኝ ሰው ሁሉ ግልፅ መልእክት አለው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው ሰዎች ለሕይወታቸው ጠቃሚ የሆነውን የእግዚአብሔርን ምህረት መልእክት እንዲያውቁ ነው፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት በጣም ግልፅ ነው፡፡ የሰዎች ልጆች ከኃጢአተኝነታቸው የተነሳ ከእግዚአብሔር እንደራቁ፣ በኃጢአታቸው ምክንያት አንድ ጊዜ እንደሚሞቱና ከዚያም ፍርድ እንዳለባቸው በግልፅ ይናገራል፡፡ ከዚያም ቀጥሎ ሰዎች እራሳቸውን በራሳቸው ጥረት፣ በጎ ስራ፣ ጥሩነት እንዲሁም ሃይማኖትም ማዳን እንደማይችሉ ይናገርና የትክክለኛውንና እግዚአብሔር እራሱ ያዘጋጀውን ምህረት ማግኛ መንገድ ያሳያል፡፡
የመጽሐፍ ቅዱስ ግልፅ መልእክት ኃጢአተኞች ንስሐ እንዲገቡና በአዳኙ በክርስቶስ በማመን በእርሱ በኩል የኃጢአትን ይቅርታ እንዲቀበሉ ይጋብዛል፡፡ በዚህ ግልፅና ትክክለኛ እንዲሁም ከእግዚአብሔር ጋር ብቸኛ የመታረቂያ መንገድ በኩል ወደ እግዚአብሔር የመጡ ሁሉ የኃጢአታቸውን ይቅርታ ተቀብለው የተለወጠ ተግባራዊ ሕይወትን አግኝተዋል፡፡ ይህንንም ሕይወት መጽሐፍ ቅዱስ አዲስ ሕይወት በማለት ይጠራዋል፡፡
አንባቢ ሆይ ግልፅ በሆነውና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ወጥነት ባለው መልክ የተገለጠውን አዲስ ሕይወት ለማግኘት እንድትችል መጽሐፍ ቅዱስን በማግኘት እንድታነብ ይህም የእግዚአብሔር ቃል መልእክት ወደሚሰበክበት ቦታ በመሄድ መልእክቱን እንድትሰማም እንጋብዝሃለን፡፡ እግዚአብሔር ይርዳህ አሜን፡፡
የትርጉም ምንጭ: COMPARING THE BIBLE AND THE QUR'AN (How to do it accurately.)
ለእስልምና መልስ አማርኛ ዋናው ገጽ