የመሐመድና የቁርአን ታሪክ

M. J. Fisher, M.Div 

ትርጉምና ቅንብር በአዘጋ

አሰቃቂ የልጅነት ጊዜ

በአረቢያን ባህረ ሰላጤ አካባቢ የነበረው የመሐመድ የልጅነት ታሪክ አሰቃቂና የትግል ጊዜ ነበር፡፡ መሐመድ የተወለደው በ570 ዓ.ም አካባቢ ሲሆን፣ አባቱ አብድ-አላህ (አብደላ) የሞተው ከመወለዱ በፊት ነበር፡፡ አላህ የሚለውም ስያሜ የአባቱ ስም አንድ ክፍል ነበር፡፡ ምክንያቱም በእሱ ጎሳ ውስጥ ያ ስም የዋነኛው አምላካቸው ዋና ስም ነበርና፡፡ የመሐመድ እናት አሚና ሕፃንን ልጅ ለሞግዚት የመስጠትን የበድዊን አረቦችን የጥንት ባህል ተከትላ ለሚበቃ ጊዜ ያህል መሐመድ በሞግዚት እጅ ውስጥ እንዲያድግ ተደርጓል፡፡ ስድስት ዓመት ሲሞላውም እናቱ ሞተች፡፡ በስድስተኛው መቶ ዓመት (ማለትም በዚያን ጊዜ) ውስጥ ወላጅ አልባ መሆን አሳዛኝ ሁኔታ ነበር፡፡ በድህነት ውስጥ የነበረው የሐሺም ጎሳ ዋና መሪ የነበረው አሁ-ታሊብ ከቋራይሽ ነገድና የመሐመድም አጎት ነበር፡፡ ስለዚህም ልጁን በአላፊነት እንዲንከባከብ ተደረገ፡፡ መሐመድም በጎሳዎችና በግለሰቦች ውስጥ በየጊዜው ይነሳ በነበረ ዓመፅና ግጭት ውስጥ አደገ፡፡

በሞት የተበላሸ ጋብቻ

መሐመድ ባለበት ደረጃ ላይ ያለ ሰው ሃብትና ኃይልን ሊያገኝ የሚችልበት አንዱ መንገድ ጥሩ ጋብቻን መመስረት ነው፡፡ አርባ ዓመት ዕድሜ ያላት ከድጃ የተባለች ነጋዴ ሴት የሃያ አምስት ዓመት ዕድሜ የሆነውን መሐመድን ለማግባት ወሰነች፡፡ ይህም ወደ ሶርያ በምትልከው የንግድ ጉዞ ላይ እሷን ወክሎ በሃላፊነት ተልእኮውን ከተወጣ ነበር፡፡ እሷም ከዚያ በፊት ሁለት ጊዜ አግብታ ነበር፡፡ መሀመድን ካገባች በኋላ እስክትሞትም ሚስቱ ሆና ቆይታለች፡፡ እነሱም አራት ሴት ልጆችን አሳድገዋል ሁለቱ ወንዶች ልጆቻቸው ግን በሕፃንነታቸው ነው የሞቱት፡፡ የመሐመድ ሚስት ከድጃ በመካ ነጋዴዎች ዘንድ ታዋቂ የነበረች ቢሆንም መሐመድ በመካ ነጋዴዎች ዘንድ ተቀባይነትን ለማግኘት ሞክሮ ሳይካለት ቀርቷል፣ እነሱም እሱን ከመካከላቸው እንደ አንዱ አላደረጉትም ነበር፡፡ መሐመድ መንፈሳዊ እርዳታን ለማግኘት የሄደበት አንዱም ምክንያት ይህ ሳይሆን አይቀርም፡፡

የሃይማኖት ፍለጋ

የአረቦች የሃይማኖት ሕይወት ለሰዎች የሚረዳ ከመሆኑ ይልቅ አስቸጋሪነቱ በጣም የበለጠ እንደሆነ መሐመድ ተገነዘበው፡፡ የባዛንታይን እና የሮማን ክርስትያኖች የዓለምን አብዛኛውን ክፍል ተቆጣጥረው በአረቢያም እንኳን ብዙዎችን ወደ ክርስትና መልሰው ነበር፡፡ የከዲጃም የአጎት ልጅ ዋራካም እንኳን ክርስትያን ሆኖ ነበር፡፡ በአረቢያ ባሕረ ሰላጤም እጅግ በጣም ሃብታም የሆኑ የአይሁድ ጎሳዎችም ነበሩ፣ ነገር ግን የአገሪቱ ዋና እምነት እንዲሁም የመሐመድም ጎሳ እምነት የጣዖት አምልኮ ነበር፡፡

መካም መሐመድ ያለበት (አባል የነበረበት) የዚህ የብዙ ጣዖታት እምነት (ፖሊቲስቲክ) ዋና ማእከል ነበረች፡፡ እነዚህም ጣዖት አምላኪዎች ፊታቸውን ወደ መካ አድርገው ይሰግዱ ነበር፡፡ እነሱም በዓመት አንድ ጊዜ ወደ መካ ይጓዙ ነበር፣ እዚያም የሚገቡበት ሰፊና ክብ የሆነ ቦታ (መስጂድ) አለ፣ እዚያም 45 ጫማ ከፍታ፣ 33 ጫማ ስፋት እና 50 ጫማ ርዝመት ያለውና ዙሪያውን ከብበው የሚቀመጡት ከአባ ተብሎ የሚጠራው ጥንታዊ ግንብ አለ፡፡ የግንቡም ውስጥ የተሞላው በጣዖታት ነው፡፡ በከአባም ጠርዝ ላይ አንድ ጥቁር ድንጋይ ከውጭ በኩል እንደ ማዕዘን ድንጋይ ሆኖ ከላይ ይታያል፡፡ ድንጋዩም ወይንም ከተወርዋሪ ኮከብ የተገኘው ድንጋይ በአምላኪዎቹ ይሳማል፡፡ ከከአባም አንድ ማይል በሚሆንና ዋዲ ሚና በተባለ ቦታ ላይ ተጓዦቹ ሄደው ድንጋይ የሚወረውሩበት ምሰሶ አለ እሱም የሚወክለው ሰይጣንን ነው፡፡ እነሱም በጨረቃ ወር ፆምና ለድሃዎች ስጦታን በመስጠትም ያምናሉ፡፡ መሐመድ መካን በተቆጣጠረ ጊዜ ከተከበረው ጥቁር ድንጋይ በስተቀር በከአባ ውስጥ የነበሩትን ጣዖታት በሙሉ አጠፋቸው፡፡ ይሁን እንጂ እያንዳንዱን የጣዖት ልምምድ እንዳሉ ስለተዋቸው በአሁኑ ጊዜ የእስልምና አንድ አምላክ አምልኮ ውስጥ እጅግ በጣም ጠቃሚ  የሃይማኖቱ ልምምድ ክፍሎች ሆነዋል፡፡ ይህም እውነታ በመሐመድ ጊዜ የነበሩትን ሰዎች በቀላሉ ወደ እስልምና እምነት እንዲለወጡ አድርጎአቸዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ያሉት ብዙዎቹ ሙስሊሞች ከከፍተኛ የቴክኖሎጂ ስልጣኔ ጋር አብረው ለመሄድ እየታገሉ እነዚህን ስርዓቶች የመከተል ችግሮች ቢኖሩባቸውም እንኳን ያደርጓቸዋል፡፡ እጅግ በጣም ብዙ የሚሆኑት ሙስሊሞች የሚኖሩት ከሳውዲ አረቢያ እርቀው ነው፣ ለሃይማኖት ጉዞ መሄድ ካለባቸው አገር ሩቅ የመሆኑ ነገር ለብዙዎቹ ትልቅ የገንዘብ አቅም ሸክም ሆኖባቸዋል፡፡

ቁርአን፡

የመሐመድ የጭንቀት ሁኔታ የተደመደመው መንፈሳዊ ልምምዶች ተቀብሏል በሚል ሪፖርት ነበር፡፡ በራሱ ምክንያት መሐመድ በምድረ በዳ ዋሻ ውስጥ በመሆን ለብቻው በጥሞና ውስጥ መቀመጥን ጀመረ፡፡ እሱም በእነዚህ ቀናት ውስጥ አንድ መንፈሳዊ አካል እንደቀረበውና ጥቂት አረፍተ ነገሮችን እንዲናገር እንደጠየቀው ተናገረ፡፡ ከዚያም ክስተት በኋላ መሐመድ ያመነው እሱ በሰይጣን እንደተያዘ ነበርና እራሱን ለመግደል ሙከራን አደረገ፣ ነገር ግን በሌላ መንፈሳዊ አካል መገለጥ ከዚህ እራስን የመግደል ድርጊት ተከለከለ (ዳነ)፣ ሌላውም መንፈሳዊ አካል እሱ ነቢይ መሆኑን አረጋገጠለት፡፡

በሙስሊም ታሪክ መሰረት፣ መሐመድ መልእክቶች መቀበሉን ቀጥሏል፡፡ እሱም እነዚህን መልእክቶች ለተከታዮቹ እያስታወሰ ይነግራቸው ነበር (ይደጋግምላቸው) ነበር፡፡ እነሱም ባገኙት ነገር ሁሉ ላይ እንደ ድንጋዮችና አጥንቶች ሁሉ ላይ ይጽፏቸው ነበር፡፡ እነዚህም መልእክቶች ወደ መሐመድ ይመጡ የነበሩት መሐመድ በልክፍት የተያዘ መስሎ ከሚታይበት ጊዜ በኋላ ነበር፡፡ በእነዚህ አስማቶች መካከል መሐመድ ልክ አላህ በእሱ ምትክ ይናገር እንደነበረ ተናግሯል፡፡ በኋላ መልአኩ ገብርኤል ነው በማለት የተናገረው መንፈሳዊ መሪው፣ በግጥማዊ መገለጡ መልእክቶችን ያንቆረቁር ነበር ብሏል፡፡ ቁርአን ግልፅ እንዳደረገው በዚያን ጊዜ የነበሩት ብዙዎቹ ክርስትያኖችና አይሁዶች ይህንን ባህርዩን እብድነት ወይንም ሰይጣናዊ ልክፍት እንደሆነ እንዳሰቡት ነው፡፡ በመጀመሪያም ቃላቶቹ አጫጭሮች ነበሩ በኋላ ግን እረጃጅሞች ሆነዋል፡፡

የአስርተ ዓመታት ተቀባይ ማጣት

ቁርአን ግጥም መሰል የሆነ አቀራረብ ስላለው ሙስሊሞች ሁሉ ተዓምራታዊ ውበት አለው ይላሉ፡፡ እጅግ በጣም ብዙ የሚሆኑት የመሐመድ ጊዜ ሰዎች ግን የመሐመድ ጥቅሶች ልዩ ናቸው በማለት አያምኑም ነበር ምክንያቱም የአረቢያ ባሕረ ሰላጤ በምትሃታዊ ጠንቋዮቹና በብዙ ግጥሞቹ በጣም የታወቀ ነበርና፡፡ የዚህም እውነታ እራሱ በቁርአንም በራሱ ውስጥም ምስክርነት ተሰጥቶታል፡፡

ከስነ ጽሑፍ ይዘቱ ባሻገር የመልእክቱ ይዘት ለመካ የጣዖት አምላኪዎች ስድብ ነበር፡፡ መሐመድ አላህ አንድና ብቸኛ አምላክ እንደሆነ ጥቅሶችን ይደጋግም ነበር፡፡ መልእክቱም የመካ ኢኮኖሚ የተመሰረተበትን የጣዖት አምልኮ ይኮንን ነበር፡፡

በዚህም ምክንያት በመጀመሪያዎቹ አስር ዓመታት የራስ ነቢይነቱ እወጃ ጊዜ ውስጥ መሐመድ ጥቂት ተከታዮችን ብቻ ነበር ያገኘው፡፡ የራሱም ጎሳ ሳይቀር በእርሱ ላይ ተቃውመውት ነበር (አልተቀበሉትም ነበር)፡፡ የጎሳ ታማኝነት የጎሳዎች ባህል መሠረት በነበረበት ዘመን ውስጥ ይሄ ፈፅሞ ተሰምቶ የማይታወቅ ነገር ነበር፡፡

መሐመድ እንቅስቃሴውን አት-ታይፍ ወደ ተባለች ከተማ ለማዛወር በፈለገበት ጊዜ፣ የከተማው መሪዎች ስምምነቱን ያጠናቀቁት በሚከተሉት ጠንካራ ተቃውሞዎች ነበር፡፡ በመሆኑም መሐመድ ሲመለስ ድንጋይን በእሱ ላይ እንዲወረውሩበት የከተማዎቹን ነዋሪዎች ማህበረ ሰብ በማደፋፈር ነበር፡፡

ቅዱስ ጦርነት

የመካ ነዋሪዎች መሐመድን ለመግደል ያሴሩ ነበር ስለዚህም ወደሌላ ቦታ መሰደድ አስፈላጊ ነበር፡፡ ስለዚህም ከ አት-ታይፍ ከተማ ይልቅ ከመዲና ከተማ ነዋሪዎች ጋር ስምምነት ማድረግ በጣም የተሻለ ነበር፡፡ መዲናም በግብርና ምርት ማዕከልነቷ በጣም ሐብታም ብትሆንም በጎሳዎች ግጭት በጣም ትቸገር ነበር፡፡ በመዲና ካሉት ነዋሪዎች አንዳንዶቹ፣ የሙስሊሞች በዚያ መኖር የሰላም መንፈሳዊ ስሜትን ያመጣል ብለው በማሰብ መሐመድን በግጭቶች መካከል እንደ ሸምጋይ አድርገው ጋበዙት፡፡ የመካ ሰዎች መሐመድን ለመግደል የነበራቸውን ዕቅድ ተግባራዊ ከማድረጋቸው በፊት መሐመድ ከተከታዮቹ ጋር ወደ መዲና ሄደ፣ እዚያም ተከታዮቹ በታዋቂነትና በኃይልም እየጠነከሩ ሄዱ፡፡ ወደ መዲና የተደረገው ጉዞም ዕለት ሐምሌ 1 ቀን 622 ዓ.ም (እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር) ነበር፡፡ ሙስሊሞችም ይህንን ቀን የእስላሞች ቀን መቁጠሪያ የመጀመሪያ ቀን አድርገው ወስደውታል፡፡

ከዚህ ጉዞ ጥቂት ቆየት ብሎም እስልምና እምነት ከተቃዋሚዎቹ ጋር በሚያደርገው ሁኔታ ሁሉ ወደ ዓመፀኝነት ተቀየረ፡፡ መሐመድም ሙስሊሞች ለእስልምና እንዲዋጉ የሚያስችላቸውን ጥቅሶችን አወጀ፡፡ ይህንንም የመካ ሰዎችን ዒላማ በማድረግ ጀመሩት፡፡ ሙስሊሞች በአላህ ስም የንግድ ሸቀጦችን ዘረፉ፣ ይህም በእነሱ እና በታጣቂ የመካ ጦር ኃይል ጋር መደበኛ ወደ ሆነ ጦርነት መራቸው፡፡ ጦርነቱም መካን ወደሚደግፉት ከተማዎች ሁሉ ተስፋፋ፡፡ ሙስሊሞችም በጦርነት ዘረፋ ምክንያት በጣም ሃብታሞች እየሆኑ መጡ፡፡

ሙስሊሞች ስኬትን (ድልን) ያገኙ ነበር፡፡ አሁን የጦር ኃይል መሆናቸው እውነታ ደረጃቸውን አንድ አድርጎ አባልነታቸውን የበለጠ እንዲጠናከር አደረገው፡፡ ጠላቶቻቸው እነሱን መፍራት ሲጀምሩም በመዲና ጎሳዎችም ላይ ያላቸው ተፅዕኖ እያደገ መጣ፡፡

ለምሳሌም ያህል በመዲና ውስጥ ሦስት የአይሁድ ጎሳዎች ነበሩ፡፡ ሦስቱም ጎሳዎች በመጽሐፍ ቅዱሳዊው የነቢይነት መስፈርት መሰረት የመሐመድን ነቢይነት እውነተኛነት አልተቀበሉትም፡፡ ቁርአን የመጽሐፍ ቅዱስ ተከታይ መጽሐፍ ነው የሚል ጥያቄን መሐመድ ያቀርብ ስለነበር፣ የእነሱ አለመቀበል ትልቅ ቅሬታን ማምጣት ነበረበት፡፡ ሆኖም አይሁዶቹ በሙስሊሞች ላይ ጦርነትን የማስነሳታቸው ነገር ምንም ማስረጃ የለም ነገር ግን መሐመድ እነሱን አጠቃቸው፡፡ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ነገዶች ባኑ ቃያኑካህ እና ናዲር እንዲሰደዱ ተገደዱ፡፡ የእስልምናው ጦርም ንብረቶቻቸውን ቤታቸውን መሬታቸውን እና ለም የነበረውን የአትክልት ቦታቸውን ሁሉ ወረሰው፡፡ የመጨረሻው የአይሁድ ቀሪ ጎሳ በመዲና ውስጥ ባኑ ቁራይዛህ የተባለው ነበር፡፡ የመሐመድ ጦር የባኑ ቁራይዛህን ጎሳ ከበቧቸው፡፡ ከበባው የተሳካ ነበር፡፡ ጦር መሳሪያቸውን እንዲያስረክቡ ከተደረጉ በኋላ በዚያን ዘመን እንኳን ተደርጎ የማይታወቅን ጭካኔያዊ ፍርድ ተፈረደባቸው፡፡ ሙስሊሞች ወንዶቹን አይሁዶች በሙሉ ገደሏቸው እነሱም ከ600 እስከ 900 የሚሆኑ ሲሆኑ ሴቶቹና ልጆቹ በሙሉ ለሙስሊም ተዋጊዎቹ ባሪያዎች እንዲሆኑ ወይንም እንዲሸጡ ተደረገ፡፡ የእነሱንም ንብረት በማከፋፈል በኩል ሃላፊነቱን ወስዶ ያከፋፈለው እራሱ መሐመድ ነበር፡፡ እንዲሁም መሐመድ ባሏ የተገደለባትንና ራይሃና የተባለችውን መበለት የራሱ ቅምጥ እንድትሆን ለእራሱ ወሰዳት፡፡

የመካ ወታደሮች ባድርና ኡሁድ በተባሉት ቦታዎች ላይ ከሙስሊሞች ጋር ተዋግተዋል፡፡ በኡሁድ ጦርነት ላይ በ625 ዓ.ም መሐመድ እራሱ በጭንቅላቱ ላይ በጣም ቆስሎ ነበር ከዚህም የተነሳ እሱ ሞቷል የሚል የስህተት ጩኸትም እንኳን ተሰምቶ ነበር፡፡ ጦርነቱ የተጠቃለለው የትኛውም ወገን ሳያሸንፍ ነበር፣ ለሙስሞች ግን ከመካዎች ጋር ተዋግቶ ድል ሳይደረጉ መትረፍ ማለት እንደ አንድ ዓይነት ድል ነበር የተቆጠረው፡፡

በመጨረሻም የሙስሊም ኃይል ጠንካራ በመሆኑ መካዎች ከመሐመድ ጋር የሰላም ስምምነት ለማድረግ ተስማሙ ያም ስምምነት ‹አል-ሁዳይቢያህ› በመባል የሚታወቀው ስምምነት ሲሆን የተደረገውም በ628 ዓ.ም ነበር፡፡ እሱ የተደረገው ለሚቀጥሉት አስር ዓመታት ሰላምን ለማስከበር ነበር፡፡ በዚህ ስምምነት ወቅት መካዎች ያደረጉት ስህተት መሐመድ ጎረቤት ጎሳዎችን፣ ማለትም በሰላም ስምምነታቸው ላይ ጥበቃ ያልተደረገላቸውን እንዲወጋ መፍቀዳቸው ነበር፡፡ መሐመድ በመካ ነጋዴዎች የጭነት ጉዞ ላይ የዘረፋ ጥቃት እንዲደረግም ፈቅዶ ነበር ይህም የእሱ ጦር ሰራዊት አባላት እንዳልሆኑ በሚናገሩ ቡድኖች አማካኝነት ነበር፡፡ እነሱም ከመሐመድ ቁጥጥር ውጪ እንደሚዘርፉ በማስመሰል ይናገሩ ነበር፡፡

የሰላም ስምምነቱ ከተደረገ ከሁለት ዓመታት ብቻ በኋላ ፈረሰ፡፡ ስምምነቱ እንዴት እንደፈረሰ የሚናገሩ የተለያዩ ምክንያቶች አሉ ነገር ግን ውጤቱ ታሪክ ሆኗል፡፡ መሐመድ እንደተናገረው የሰላም ስምምነቱ የፈረሰው በመካዎች እንደሆነ ነው፡፡ የእሱ እስላማዊ ጦር መካን ወረረና ወጋት ይህም በ630 ዓ.ም ነበር፡፡

መሐመድ ከሞተ በኋላ የእስላም ጦር ኃይል በሰሜን አፍሪካ፣ በዩሮፕ እና በመካከለኛው ምስራቅ ድሎችን በማግኘቱ ለሃይማኖቱ መሰራጨትና በኤስያ አገሮች ውስጥ ለንግድ መስፋፋት ተጨማሪ ዕድገትን ሰጥቷል፡፡ ሙስሊሞች እንደ አንድ የሃይማኖታቸው ተግባር በጠላቶቻቸው ላይ (ወይንም በተቃዋሚዎቻቸው) ላይ የሚያስነሱት ዓመፅ ‹ጂሃድ› ወይንም ቅዱስ ጦርነት በመባል ይታወቃል፡፡ ይህም አሁንም በዓለም ዙሪያ ሁሉ በዚህ በያዝነው አዲስ ምዕተ ዓመትም እንኳን እራስን ለመከላከልና የእስልምናን ኃይልና ተፅዕኖን ለማስፋፋት የሚደረግ ነው፡፡ ሙስሊሞች ሊያስቡበት የሚገባው ጥያቄ ግን መቼና እንዴት ጂሃድ መደረግ አለበት የሚለውን ጥያቄ ነው፡፡

የመሐመድ ስኬቶች

መሐመድ ስድሳ ዓመት ሲሆነው እጀግ በጣም ብዙ የሆነ ሐብትና ኃይል ነበረው፡፡ በመዲና ውስጥ በታዋቂነት ከፍ ማለቱ እንዲሁም ሙስሊሞች በመካ ላይ ያገኙት የመጨረሻ ድል መሐመድን በሚያስፋፋው ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ ላይ ሙሉ ለሙሉ የመቆጣጠርን ኃይል እንዲያገኝ አድርጎት ነበር፡፡ እሱም እንደ አላህ ቃል ተደርጎ ይፈራ እና ይከበር ነበር፡፡ እስልምናን የተቃወሙትን ሰዎች የወደፊት ዕጣም ሆነ ንብረት ይቆጣጠር ነበር፡፡ ብዙ አይሁዶችና ክርስትያን ማህበረሰቦች መጠነኛ ነፃነት ተሰጥቷቸው ነበር ይህም ለመሐመድ ቀረጥን እስከከፈሉ ድረስ፣ ለእስልምና አገዛዝ እራሳቸውን እስካስገዙ እና እምነታቸውን ለሌሎች ለማካፈል ወንጌልን እስካልሰበኩ ድረስ ነበር፡፡

ለእሱም ይሰጥ የነበረው ክብር እጅግ በጣም ትልቅ ነበር አሁንም እንኳን ቢሆን እሱ የተናገራቸው የባህርያት መርሆዎች፣ አለባበሶች፣ የየዕለቱ ልምምዶች፣ የፂም አቆራረጥም እንኳን ሳይቀር በዓለም ዙሪያ እስልምናን በሚከተሉት ዘንድ እንደ ምሳሌ የሚወሰዱ ናቸው፡፡ የመሐመድ ሐሳቦች እና እሱ እንዴት በኃይል እያደገ እንደሄደ የሚናገሩ መረጃዎች ሃዲት በተባለ መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግበው ይገኛሉ፡፡ ሃዲት አንድ መጽሐፍ ሳይሆን ከመሐመድ በኋላ ተጠናቅሮ የተጻፈ እጅግ በጣም ብዙ ጥራዝ የሆነ የመጽሐፍ ስብስብ ነው፡፡ ከእነዚህም ውስጥ በጣም የተከበረው ስብስብ ‹የሳሂህ አል ቡካሪ› በመባል የሚታወቀው ሃዲት ነው፡፡ እሱም መሐመድ ለየዕለቱ ሕይወት መመሪያነት የተናገረውን ወይንም የሰጠውን ነገር በዝርዝር ይናገራል እንዲሁም ስለመሐመድ ጀግንነት በማውሳት እና ለታማኝ ሙስሊሞች የዕለት ተዕለት ሕይወት መመሪያን ይሰጣል፡፡

አንድ ባሏን የፈታች ሐብታምን ሴት ለማግባት እራሱን ብቁ እና ጥሩ አድርጎ ማቅረብ ለነበረበት ሰው፣ አሁን እጅግ በጣም ብዙ ሴቶች ኖረውታል፡፡ ከዲጃ ከሞተች በኋላ መሐመድ በግምት አስራ ስድስት ሚስቶች እና በጦርነት ላይ የተማረኩ ባርያ ሴቶች ነበሩት፡፡ መሐመድ ሲሞት አብረውት ይኖሩ የነበሩ ዘጠኝ ሚስቶች እና ሁለት ባሪያ ሴቶች ነበሩት፡፡ እሱም ከመሰረታቸው አወዛጋቢ ጋብቻዎች መካከል ሁለቱ የአይሻና የዘይነባ ጉዳይ ይገኙበታል፡፡ አይሻም ከመሐመድ ጋር ተጋብታ የነበረው ገና የስድስት ዓመት ሕፃን ልጅ ሆና ነበር፡፡ ጋብቻውም የተጠናቀቀው እሷ ገና በአሻንጉሊቶች የምትጫወት የዘጠኝ ዓመት ልጅ እያለች ነበር፡፡ በዚያን ጊዜም መሐመድ የሃምሳ ሦስት ዓመት ሰው ነበር፡፡ ዘይነባ ደግሞ የጉዲፈቻ ልጁ ሚስት የነበረች ናት፡፡ የሙስሊም ታሪክ ግልጥ እንደሚመስለው ዘይነባ ባሏን የፈታችው መሐመድ የልጁን ሚስት ስለፈለጋት ብቻ እንደነበረ ነው፡፡

የመሐመድን ባህርይ መተቸት በተመለከተ በቁርአን ውስጥ በጣም ብዙ ጊዜ መሐመድ እራሱ ሲገልጣቸው ይነበባል፡፡ ይደረጉም የነበረው አላህ የእሱን ባህርይ እንደሚደግፈው ተደርገው በመቀመጥ ነበር፡፡ መሐመድም ለሚስቶቹ ትዕዛዝን ሲሰጥ እንዳለ ተደርገው የተቀመጡም ጥቅሶች በቁርአን ውስጥ ይገኛሉ ይህም ለአጠቃላይ ሕዝብ ጭምር ሲሆን የሚያሳየውም እሱን እንዴት መታዘዝ እንደሚገባቸው ተደርጎ ነው፡፡ ሙስሊሞች እነዚህን ትዕዛዞች ያምኗቸዋል፣ እነዚህም በመሐመድ የተነገሩት ጥቅሶች በሙሉ በቁርአን ውስጥ ተጠናቅረው ይገኛሉ፡፡

ቁርአን መጽሐፍ ሆነ

መሐመድ ከሞተ በኋላ የእሱ ጥቅሶች በድንጋዮች በአጥንቶች፣ በቆዳዎች እና በተከታዮቹ የማስታዎስ ችሎታ ውስጥ ተቀምጠው ቆይተዋል፡፡ ዓመታትም ካለፉ በኋላ ሙሉውን ቁርአንን በቃላቸው እንደሚያስታውሱ ከሚናገሩትም ብዙዎቹ በቶርነት ላይ ተገደሉ፡፡ የቁርአን ቃላት ተጽፎባቸው ከነበሩትም አንዳንዶቹ ነገሮች ተበላሹ ወይንም ጠፉ፡፡ ስለዚህም በጣም በከፍተኛ ፍጥነት አዋቂዎቹ የሚያስታውሱትን መናገር እና በሌሎች ተጽፈው የተቀመጡትን ጥቅሶች በማሰባሰብ የመጀመሪያውን ቁርአን ለመፍጠር ተንቀሳቀሱ፡፡ እነዚህም የመጀመሪያው የቁርአን ጥራዞች እየተባዙ በእስላሞች ማህብረሰቦች መካከል ይሰራጩ ነበር፡፡

በአሁኑ ጊዜ ያሉ ሙስሊሞች ከመጀመሪያ ጀምሮ አንድ ብቸኛ የሆነ ያለምንም ስህተት ግድፈት ወይንም ጭማሬ የተቀናበረ ቁርአን አለ በሚለው ሐሳብ ላይ በጣም ትኩረትን ይሰጣሉ፡፡ የእስላም ታሪክ እንደሚያሳየው ከሆነ ግን ከአራት እስከ ሰባት የተለያ የቁርአን ትርጉሞች እንደነበሩ ነው፡፡ ከመሐመድ ቀጥሎ ስልጣን ከያዙት መካከል አንዱ የሆነው ካሊፍ ኡትማን ከዚህ እውነታ የተነሳ በጣም ደንግጦ ነበር፡፡ እሱም ሦስት አባላት ያሉትን ኮሚቴ መሠረተና አንድ የቁርአን ወጥ ትርጉም እንዲፈጥሩ አደረገ፡፡ ከዚያም የሙስሊም መሪዎች ሌሎቹን የቁርአን ትርጉሞችን በሙሉ እንዲቃጠሉ ለማድረግ ሙከራን አደረጉ ((Sahih Bukhari, Vol. 6, p. 479).

በጣም የተከበረው ሐዲት የመዘገበው የኡትማንም ወጥ ኮፒ የተባለው ቁርአንም መታረም እንደነበረበት ነው፡፡ ከኮሚቴው አባሎች ውስጥ አንዱ ዛይድ የተናገረው እነሱ እንዴት የተዘለለ (ወይንም የጠፋ) ጥቅስን በመጨረሻ እንዳስተዋሉ ነበር፡፡ ይህንን ጥቅስም ፈልገው ኩዛይማ-ቢን-ታቢት አል አነሳሪ በሚባል ሰው ዘንድ አግኝተውታል፡፡ የሙስሊሞች ትውፊትም እንደሚናገረው ለዚህ ወጥ እንዲሆን በተዘጋጀው ቁርአን ውስጥ በኋላ የተጨመረው አንቀፅ የሚገኘው በምዕራፍ 33 ቁጥር 23 ውስጥ ነው (Sahih Bukhari, Vol. 6, p. 479)፡፡ ይህም አንቀፅ ከተጨመረም በኋላ እንኳን ከኡስማን ወጥ የቁርአን ቅንብር ውስጥ ያልተጨመሩ አንቀፆች እንዳሉ የታመኑ የእስልምና ትውፊቶች ይናገራሉ፡፡ አመንዝራዎች በድንጋይ እንዲወገሩ የሚያዙትን ጥቅሶች መሐመድ እንደተቀበለ ሪፖርት ተደርጓል (Ibn Ishaq, Sirat Rasulullah, p. 684). ነገር ግን ይህ የቁርአን ትምህርት በአሁኑ ጊዜ ባሉ ቁርአኖች ውስጥ አይገኝም፡፡

አመንዝራዎችን በድንጋይ የመውገርን ዓይነት ጥቅሶችን ማጣት በእስልምና ልምምድ ውስጥ እንዲደገፍ ትደርጓል፡፡ እስልምና ከተመሠረተበት መሰረት አመንዝራዎች ሁልጊዜ በድንጋይ ሲወገሩ ነበር ነገር ግን ኡትማን ወጥ ባደረገው ቁርአን ውስጥ አመንዝራዎች አንድ መቶ ጊዜ እንዲገረፉ ነው የሚጠይቀው 24.2፡፡

እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ ሙስሊሞች ቁርአን የጽሑፍ ማስተካከል ተደርጎበታል፣ ተቀይሯል ወይንም በሆነ አንድ መንገድ መሐመድ በመጀመሪያ ከተናገረው ጋር አንድ አይደለም የሚለውን ሲሰሙ በጣም ይናደዳሉ፡፡ እነሱም የሚያምኑት በኡትማን የተቃጠሉት የቁራን ኮፒዎች እሱ ወጥ ካደረጋቸው (እና ከባረከው ኮፒ) ጋር በጣም ጥቂት ልዩነት እንዳላቸውና መሐመድ የተናገራቸውን ጥቅሶች ያለምንም ስህተት ካስታወሱ ከመሐመድ ጥብቅ ተከታዮች ያልምንም ስህተት እንደመጡ አድርገው ነው፡፡ ስለዚህም በቁርአን ውስጥ ስህተት እንዳለ የሚጠቁሙትን ትውፊቶች በሙሉ ታማኝ ያልሆኑ የእስልምና ታሪኮች በማድረግ ይቆጥሯቸዋል፡፡ እነሱም ቁርአንን እንደ አላህ ፍፁም ቃል አድርገው ያከብሩታል ስለዚህም በአንቀ ፆቹ ላይ ምሁራዊ የሆነን ማንኛውንም ትችት እና ጥያቄ ወይንም ምርመራ ለማድረግ  አይፈልጉም፡፡

የቁርአን ባህርያት

የቁርአን ጽሑፋዊ አቀነባበር አስደናቂ ነው፡፡ ቁርአን ከክርስትያኖች አዲስ ኪዳን በጣም አጭር የሆነ መጽሐፍ ነው፡፡ ምዕራፎቹም በተነገሩበት ጊዜ በቅደም ተከተል አልተቀመጡም፣ ነገር ግን ረጅም የሆነው ምዕራፍ በመጀመሪያ በመጨረሻም አጭር የሆነው ምዕራፍ ሆነው ነው የተደራጁት፡፡ ከዚህም የአደረጃጀት አካሄድ የተነሳ የክስተቶች ወይንም የሐሳብ ቅደም ተከተል የለውም፡፡ የቁርአን ምዕራፎች በመሐመድ መቼ እንደተነገሩ በመመርመር እና በዚህም መሠረት ቅደም ተከተል በማስያዝ ቁርአን የተባለ እትም በፔንጁን አታሚዎች ታትሟል፡፡

በአንድ ምዕራፍ ውስጥ ያለውን ሐሳብ መከተልና መረዳት እጅግ በጣም ከባድ ነው፡፡ በአንድ ምዕራፍ ውስጥም ሆነ በአንድ ጥቅስ ውስጥ ያለው ዋና ሐሳብ ወደ ሌላ ሐሳብና ርዕስ ያለምንም መሸጋገሪያ ሊቀየር ይችላል፡፡ ለዚህ ነው ልክ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ እንዳለው ርዕሳዊ ጥናት በጣም አስፈላጊ የሆነው፡፡

መሐመድ ጥቅሶቹን ይናገር በነበረበት ጊዜ በአንደኛ መደብ ነጠላ አነጋገር አልተናገረም ማለትም ‹እኔ ማመን አለባችሁ በማለት እናገራለሁ› በሚል መሠረት አልተናገረም፡፡ እሱ የተናገረው ልክ በመላእክት በኩል ከአላህ የመጣ መልእክትን እንደሚያስተላልፍ አስመስሎ ነው፣ ስለዚህም እሱ እንዲናገር ይጠበቅ የነበረው በአንደኛ መደብ ብዙ ቁጥር መልክ ነው ‹እኛ ዓለማትን ፈጥረናል እና እኛ ሰዎችን በአንተ (በመሐመድ) እንደ ነቢይ እንዲያምኑ አዘናል› በሚል መንገድ ነው፡፡ ሙስሊሞች የአንደኛ መደብ ብዙ ቁጥር በቁርአን ውስጥ ያለው ከአላህ አንድነት ጋር ይቃረናል በማለት አያምኑም፡፡

መሐመድ አረብኛን ይናገራል ይህም የቁርአን ቋንቋ ነው፡፡ አረብኛን የማያውቁም ሙስሊሞችም አንኳን ቁርአንን በአረብኛው እንዲያስታውሱት ይጠየቃሉ፡፡ ይህንንም የሚያደርጉት ቁርአን በሌላ ቋንቋ ከተተረጎመ ቁርአንነቱን ያጣል በሚል ሰበብ ነው፡፡ ምክንያቱም በትርጉም ውስጥ ቁርአን መልእክቱን ሊያጣ ይችላል በማለት ያምናሉ፡፡

የቁርአን ትምህርቶች

በቁርአን ውስጥ ጥቂት ዋና ሐሳቦች ብዙ ጊዜ ይደጋገማሉ፡፡ በጣም ግንባር ቀዳሚውን የያዙት ጣዖታትን በተቃረነ መልኩ የተነገሩት፣ በአላህ አንድነት የማመን ትዕዛዝ እና ከመጽሐፍ ቅዱስ ነቢያቶች እኩል የመሐመድ ነቢይነት ዋጋ ማመንን መቀበል ናቸው፡፡ እነዚህን እምነቶች በመደገፍም ቁርአን የፍጥረትን ድንቅነት ይደጋግማል የጣዖት አምልኮን ሞኝነት የሚመጣውን የፍርድ ቀንን አሰቃቂነት እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስን የሚያረጋግጥ መስሎ መቅረቡንም ይናገራል፡፡

መጽሐፍ ቅዱስን የሚያረጋግጥ ነው ‹የሚባል› ቁርአን መጽሐፍ ቅዱስን በተመለከተ የተናገራቸውን መልካም ነገሮች ለመጥቀስ ነው፡፡ በጊዜው የነበሩት አይሁዶችና ክርስትያኖች ቁርአን መጽሐፍ ቅዱስን ሲጠቅስ ሲሰሙ ሁለት ችግሮችን ተገንዝበው ነበር፡፡ እጅግ ብዙ የሆኑ ያልተለመዱ መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሚመስሉ ተረቶችን አግኝተው ነበር፡፡ አንዱም ምሳሌ ንጉሱ ሰለሞን ከጉንዳኖችና ከአዕዋፍ ጋር የመነጋገሩ ጉዳይ ነበር፡፡ መሐመድ በአንድ አምላክ  ከሚያም ከሌሎች አማኞች ዘንድ ይጠብቅ የነበረውን ድጋፍን ያላገኘበት ዋናው ምክንያት ይህ ነበር፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የቁርአን ትምህርት የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት የሚቃረን መሆኑ ነበር፡፡ ቁርአን የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል እንደሚደግፍ እየተናገረ የሥላሴን ትምህርት ይክዳል፣ እንዲሁም ክርስቶስን አምላክነት ይክዳል፣ እንዲሁም ደኅንነት በመስቀሉ ላይ በተሰራው ስራ መሆኑን ይክዳል እንዲሁም የክርስቶስ ኢየሱስን ከሞት መነሳት ማለትም ትንሳኤን ይክዳል፡፡

አንባቢዎች ቁርአንን እንዲያነቡ እና ትምህርቱንም እንዲያምኑ ለማሳመን ብዙ የሆኑ ማበረታቻዎች በውስጡ ተደጋግመዋል፡፡ ለጦር ድል አድራጊነት እንዲሁም ከድል የሚገኙት ምርኮዎች ስለ እስልምና ለሚዋጉት ምድራዊ ሽልማቶች ሆነው እንደሚሰጡ፡፡ ከሞትም በኋላ ደግሞ በገነት ውስጥ የስጋዊ ስሜት በረከቶች የተስፋ ቃል ሆነው ተሰጥተዋል እነዚህም ከሲዖል አሰቃቂ ሁኔታዎች ጋር በተቃረነ መልኩ ነው፡፡

ሙስሊሞች የሚያተኩሩባቸው አምስት የእስልምና መሰረቶች ይገኛሉ እነዚህንም በቁርአንና በሃዲቶች ውስጥ ትምህርት ተሰጥቶባቸዋል ተብሎ የሚታሰቡ ናቸው፡፡ እነሱም የሚጨምሩት አላህ አንድ መሆኑን ማወጅ፣ መሐመድ ደግሞ ነቢይ መሆኑን፣ ወደ መካ ፊትን አዙሮ በቀን አምስት ጊዜ መፀለይ፣ ምፅዋትን መስጠት፣ በየዓመቱ በረመዳን ወር የአንድ ወር ፆም ሙሉ ቀን ማድረግ፣ እንዲሁም ቢያንስ በሕይወት ዘመን አንድ ጊዜ ወደ መካ ጉዞ ወይንም ሃጂ ማድረግ ናቸው፡፡

የአዘጋጁ ማሳሰቢያ

ከዚህ በላይ ያየናቸው የመሐመድና የእስልምና ሃይማኖት ታሪኮች ግሩም የሆኑ እውነቶችን ይፈነጥቃሉ፡፡ ስለምንከተለው እምነት ትክክለኛውን እውነት መረዳት ይገባናል ጠቃሚነቱም አጠያያቂ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ዘላለማዊ የሆነ ውጤትና ፍፃሜ አለውና፡፡ መጽሐፍትን የሚያነብብ ሰው ሁሉ ከሚያነበው መጽሐፍ አንድ ቁም ነገርንና ትምህርትን እንዲቀስም ይጠበቅበታል፡፡ ታዲያ የቁርአንና የመሐመድ ታሪክ አሰሳ ከሚያሳየው ነገር ምን እንማራለን እምነታችንን ልንጥልባቸው ይገባናል ወይ? ሌላስ የተሻለ እና አሳማኝ የሆነ እምነት የለም ወይ? ከዚህም ሌላ ከዚህ ዓለም በሞት ስለይ ከሃይማኖቴ የማገኘውና በግልጥ የተቀመጠ ዋስትና አለኝን? የሚሉ ጥያቄዎችን ሁሉ መጠየቅ አግባብና ማስተዋል ነው፡፡  

እዚህ ነጥብ ላይ አንባቢዎችን የምናሳስበው ስለ መንፈሳዊ ሕይወታቸው እና ከሕያውና እውነተኛው ፈጣሪ አምላክ ጋር ስላላቸው ግንኙነት እንዲያስቡ ነው፡፡ እንዲህ በማለት ልንጠይቅ ይገባናል፤ የዘላለምን ሕይወት ስለማግኘት ማወቅ የሚገባኝን እውቀት ሁሉ ከየት ነው የማገኘው? ጊዜው በከንቱ ሳያልፍብኝ ምን ማድረግ ነው ያለብኝ? ማለት አለብን፡፡ ለእነዚህ ሁሉ መሠረታዊ ጥያቄዎቻችን እኛ መልስን ያገኘነው ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ነው፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ በትምህርትነት በሚሰጥበት ቦታ በመሄድ ትምህርቱን እንድትከታተሉ እና መልእክቱን እንድትረዱ በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስን በግል በማግኘት በጥንቃቄና በማስተዋል እንድታነቡ እንጋብዛችኋለን፡፡ ለእነዚህ መሠረታዊና ወሳኝ ጥያቄዎች መልስን እስካላገኛችሁ ድረስ እንዳታርፉም በእግዚአብሔር ፍቅር እንመክራችኋለን፣ ጌታ እግዚአብሔር ይርዳችሁ አሜን፡፡

 

የትርጉም ምንጭ: History of Mohammed and the Qur'an, Chapter 1 of "A Topical Study of the Qur'an From a Christian Perspective" by M.J Fisher, M.Div

ሙሉ መጽሐፉ በአማርኛ: ርእሳዊ የቁርአን ጥናት በክርስትና አይን ሲመረመር

 

ለእስልምና መልስ አማርኛ  ዋናው ገጽ