መሐመድ በቁርአን
በ M. J. Fisher, M.Div
ትርጉምና ቅንበር በአዘጋጁ
ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ማነፃፀሪያ
መሐመድ የነቢያት መጨረሻ ወይንም መደምደሚያ ነበርን ወይንስ ጌታ ኢየሱስ በማቴዎስ 24.24 ላይ ትንቢት የተናገረለት የሐሰት ነቢይ ነው? ብዙ ሰዎች የመሐመድን አገልግሎት ለመገምገም የሚያስችላቸው ምንም ማገናዘቢያ የላቸውም፡፡ ስለ መሐመድ ሕይወት ምንነት ለመረዳት የሚያስችለን አንዱ ምንጫችን የሚሆነው እራሱ ቁርአን የሚያስተምረው ነው፡፡ እዚህ ጽሑፍ ላይ የምናቀርባቸው የቁርአን ጥቅሶች እራሳቸው በመሐመድ የተነገሩ ወይንም ስለ እራሱ ‹የተቀሩት› ናቸው፡፡ ወይንም ደግሞ ሙስሊሞች እንደሚሉት ስለ እራሱ የመጡለት መገለጦች ናቸው፡፡ ጥቅሶቹም የተነገሩት ልክ አላህ በእርሱ በኩል በቀጥታ እንደሚናገር ሆነው ነው፡፡ ስለዚህም በዚህ ምዕራፍ ውስጥ 87 የሚሆኑት ስለ መሐመድ የተነገሩት ጥቅሶች በአጭሩ ቀርበዋል፡፡
በነዚህ የቁርአን ጥቅሶች ስብስብ ውስጥ በጣም የተለያዩ ሐሳብን የያዙ ጥቅሶችን እናገገኛለን፡፡ ለምሳሌም ያህል አንዳንዶቹ የመሐመድን ተልእኮ ይዘረዝሩና እንደ ነቢይ እሱን ለማይቀበሉት ማስጠንቀቂያን ይሰጣሉ፡፡ ሌሎቹ ጥቅሶች ደግሞ ‹በሰይጣናዊ ጥቅሶች› ትርጉም ላይ ይናገራሉ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ መሐመድን በስነ ምግባር ጉድለት ለሚከሱት ሰዎች ምላሽን ይሰጣሉ፡፡ የማያምኑት ለመሐመድ ያላቸውን የግምገማ አመለካከቶች የሚያሳዩ ጥቅሶችም አሉ፡፡ ሰዎች መሐመድን እንዴት ሊመለከቱት (ስለ እሱ ምን ማድረግ እንዳለባቸው) ዝርዝሮችም በሌሎች ጥቅሶች ቀርበዋል፡፡ አላህ ለመሐመድ ብቻ ስለ ሰጠው ዕድሎች የሚናገሩም ቁጥሮች አሉ፡፡ አንቀፆቹንም ለመረዳት እንዲቻል አንዳንድ ጠቃሚ የሆኑ የሰዋስዋዊ (የቋንቋ) እና ታሪካዊ መረጃዎች በቅንፍ ውስጥ ተጨምረዋል፡፡
ይህ መጽሐፍ የተጻፈው ሙስሊም ላልሆኑና የመሐመድን ስራ ከኢየሱስ ጋር ለማወዳደር ለሚገምቱ ሰዎች ነበር፡፡ አንዳንድ መመሳሰሎች (በኢየሱስና በመሐመድ መካከል) አሉበት፡፡ ሁለቱም በዓለም ላይ ያሉ ትልልቅ ሃይማኖት ጀማሪዎች ናቸው፡፡ ሁለቱም በአይሁድ ቅዱስ መጽሐፍ ላይ ትንቢት ስለ እነሱ እንደተነገረ ተናግረዋል፡፡ ስለዚህም የእነሱ የሃይማኖት ትምህርት ማለት የአብርሃም፣ የሙሴ፣ እና የዳዊት እምነት ቀጣይ እንደሆነ ሁለቱም ተናግረዋል፡፡ ከሁለቱ አንዳቸውም መጽሐፍን ጽፈው አላለፉም ነገር ግን ተከታዮቻቸው መልክቶቻቸውንና ስራዎቻቸውን እንዲያቀናብሩ ትተውላቸዋል፡፡
በሌላ መልኩ ደግሞ ልዩነታቸው እጅግ በጣም የጎላ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስን ከፍ አድርጎ የሚያሳየው ስጋን የለበሰ ብቸኛ አምላክ አድርጎ ሲሆን ቁርዓን ግን መሐመድን የሚያቀርበው ነቢይ እንደሆነ አድርጎ ነው፡፡ ኢየሱስ አላገባም ነበር መሐመድ ግን ብዙ ሚስቶች ነበሩት፡፡ ኢየሱስ ሽብርተኛ አልነበረም ቤተክርስትያኑንም ሽብርተኛ እንድትሆን አላስተማረም፣ መሐመድ ግን የቅዱስ ጦርነትን ትምህርት (ጂሃድን) አስቀምጧል፣ ይህንንም የእስልምና እምነት እጅግ ጠቃሚ ክፍል አድርጎታል፡፡ በሁለቱ መካከል ያለው ልዩነት እጅግ በጣም ግልጥ ነው፡፡
ስለዚህም ቁርዓን ስለ መሐመድ የሚከተሉትን ነገሮች ይናገራል፡፡
ወላጅ የሞቱበት ድሃ፡- መሐመድ ወላጆቹ የሞቱበት ልጅ ነበር ግን ቤት ተሰጥቶት ነበር፡፡ እሱም ድሃ ነበር ነገር ግን ሃብታም ሆነ 93.6-8፡፡
አሊሃህ ወይም አላህ፡- የጣዖት አምላኪዎቹ የመሐመድን ትምህርት ሰዎች እንዲቃወሙት ያበረታቱ ነበር ይህንም ሲያደርጉ አማልክትን (አሊሃህን) ወደ አንድ አምላክ (አላህ) አደረጋቸው እያሉ ነበር፣ ይህ ደግሞ ምንም ሳይሆን ፈጠራ ነው ብለው ነበር 38.4-7፡፡
እንደ ኢየሱስ ያለ ነቢይ፡- አላህ ከመሐመድ ጋር የከበረ ቃል ኪዳንን ወሰደ ይህም ከሌሎች ነቢያት ማለትም ከኖህ፣ ከአብርሃም፣ ከሙሴ እና ከማርያም ልጅ ከኢየሱስ ጋር እንደ ወሰደው ዓይነት ቃል ኪዳን ነው 33.7፡፡
ልጅ የሌለው ግን የነቢያት መደምደሚያ (ማህተም)፡- መሐመድ ወንድ ልጅ የለውም (ይህ ባይሆንለትም እንኳን) እሱ የነቢያት ማህተም ለመሆኑ የአላህ ማረጋገጫ አለው 33.40፡፡
ያልተማረ ነው፡- አላህ ለሙሴ የመለሰው መልስ በፃድቃኑ ላይ ምህረትን እንደሚያደርግ ነው፣ እነሱም በእሱ መገለጥና በነቢዩ የሚያምኑት ናቸው፣ እሱም ማንበብንና መጻፍንም የማያውቀው ነው 7.157ሀ፡፡
የመሐመድ ነገድ፡- የኩራይሽ (መሐመድ አባል የነበረበት የአረብ ጎሳ ነው) ነገድ (ጎሳ) ከሌሎቹ ይልቅ እድልንና ክብርን በማግኘት ይደሰታል (ምክንያቱም በካዓባ ወይንም በመካ በሚገኘው የማምለኪያ ማዕከል ላይ በእነሱ ጎሳ ይመለክ የነበረው አንድ አላህ ብቻ ነበረ)፡፡ እነሱም በዚያ ቤት ላይ ጌታ የሆነውን አላህን ያከብሩታል 106.1-4፡፡
መልእክተኛ፡- መሐመድ እንዲያድነው ወደ እሱ የሚመለከተው ምንም አዳኝ የለውም እሱም እራሱ መልእክተኛ ብቻ ነው 72.22፣23፤ 22.49፡፡
መሐመድን አክብሩት፡- መሐመድ የምስራችን ዜናና ማስጠንቀቂያን ያመጣልና አማኞች አሱን ሊረዱትና ሊያከብሩት ይገባቸዋል፡፡ ለመሐመድ የሚደረግ የታማኝነት መሐላ ለአላህ የተደረገ የታማኝነት መሐላ ማለት ነው፡፡ እነሱም እጃቸውን በአንድ ላይ በሚያደርጉበት ጊዜ የአላህም እጅ በእነሱ ላይ ይሆናል 48.8-10፡፡
ፈጣን ምላስ፡- የቁርዓንን ጥቅሶች በሚያነብበት ጊዜ መሐመድ ምላሱን በፍጥነት ማንቀሳቀስ የለበትም፣ 75.16፡፡
ለመጽሐፍ ቅዱስ አመልክቱ፡- ሙስሊሞች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሁለቱም በብሉይ ኪዳን ሕግና በአዲስ ኪዳን ወንጌል (መሐመድን) ተጠቅሶ ያገኙታል 7.157፡፡
የመጀመሪያው ሙስሊም፡- መሐመድ መናገር ያለበት ነገር ፀሎቱ፣ ሕይወቱ እና ሞቱም ሁሉ በሙሉ ለአላህ እንደሆነ ነው፡፡ እሱም (አላህ) ምንም ሚስት ወይንም ሸሪክ የለውም እሱም ለአላህ እራሱን በማስገዛት የመጀመሪያው ነው 6.162፣ 163፡፡
ሰይጣናዊ ጥቅሶች፡- መሐመድ የቁርአን ክፍሎች እንዲሆኑ አንዳንድ ጥቅሶችን ተናግሯል ነገር ግን በእርግጥ እነሱ የመጡት ከሰይጣን ነበር፣ ነገር ግን ይህ በእሱ ብቻ የሆነና ያልተለመደ አይደለም ምክንያቱም ከዚህ በፊት የመቱት እያንዳንዱ ነቢይና ሐዋርያ ተመሳሳይ ችግር ነበራቸው በማለት ቁርአን ይናራልና፡፡ ሰይጣናዊ ጥቅሶች ተወግደዋል፡፡ የሰይጣናዊ ጥቅሶች ዓላማም የማያምኑትን ለመፈተንና እነሱንም በሁለት ቡድን ለመክፈል ነበር ይህም ቁርአን ለሚያምኑት እውነት መሆኑን የሚያመለክት ምስክር መሆኑን ለማሳየት ነው 22.52፣ 53፡፡ ሰይጣናዊ ጥቅሶች ተደምስሰው በተሻሉ ጥቅሾች ወይንም በተመሳሳይ ጥቅሶች ተተክተዋል 2.106፡፡
አጭበርባሪ፡- የቁርአን ክፍል እንዲሆን መሐመድ ከሰጣቸው ጥቅሶች መካከል አንዱ በሌላ ጥቅስ በተተካበት ጊዜ ሙስሊሞች ያልሆኑት የተናገሩት እሱ አጭበርባሪ እንደሆነና ነቢይ ነኝ ብሎ በማጭበርበር የሚጠይቅ እንደነበረ ነው 16.101፡፡
ጥርጥርን ያመጣ ለውጥ፡- የመሐመድ የቀደሙት ትዕዛዞች ከመጀመሪያው በተለዩ በሌሎች ትዕዛዞች በመተካታቸው ሞኝ የሆነው ሰው ይደነቅ ይሆናል (ይህም መሐመድ ሙስሊሞች የሚፀልዩበትን አቅጣጫ ከኢየሩሳሌም ወደ መካ መቀየራቸውን በተመለከተ ነው)፡፡ ለእነዚህ ሞኝ የሆኑ ተጠራጣሪዎች መልስ የሚሆነው የመጀመሪያው መገለጥ ተሰጥቶ የነበረው የከባዱ ፈተና የመጀመሪያ ክፍል እንዲሆን ነበር፡፡ ይህ ለውጥ (በቁርአን ውስጥ) የተደረገውም የትኞቹ ተከታዮች ሙስሊም ሆነው እንደሚቀጥሉ እና የትኞቹ ደግሞ እንደሚመለሱ ለመፈተን ነበር፡፡ እሱም ታላቅ ፈተና ነበር እውነተኛ ሙስሊሞች የሚፀኑበት ነበር 2.142፣143፡፡
የተገመሰች ጨረቃ ተዓምር፡- ፍርድ ቅርብ ነው ጨረቃም በሁለት ትከፈላለች፡፡ ነገር ግን የማያምኑት ምልክትንም ቢያዩ የሚናገሩት ይህ የዘወትር ድግምት ነው በማለት ነው 54.1-2፡፡
ተዋጊዎች፡- መሐመድ ከማያምኑትና ከመናፍቃን ጋር ተዋጋ በጣምም ክፋባቸው የእነሱም መጨረሻ ገሃነም ናት 66.9፡፡
ምርኮ፡- መሐመድና ተከታዮቹ የአንድ ከተማ ሰዎችን ድል ባደረጉበት ጊዜ የተሸነፉት ሰዎች ንብረት መከፋፈል የነበረበት በመሐመድ ነበር ይህም በሚደረግበት ጊዜ ማንም ሰው እንዴት እንደተደረገ አስተያየትን መስጠት አይኖርበትም 59.7፡፡
ከትችት በላይ ነው፡- መሐመድን በተመለከተ ሊተች የሚገባውን ማንኛውንም ነገር በግል መነጋገር አይፈቀድም፡፡ የምስጢር ምክክሮች ሁሉ ክፉ ናቸው 58.9፣10፡፡
የቀስታ ድምፅ፡- ሙስሊሞች ከመሐመድ በላይ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው መነጋገር የለባቸውም፡፡ እነሱም በመሐመድ ፊት መነጋገር ያለባቸው በዝቅተኛ ድምፅ ነው፡፡ መሐመድ በሌላ ክፍል ውስጥ እያለ ጮክ ብለው ከእሱ ጋር መነጋገር የለባቸውም ነገር ግን መሐመድ ወደ እነሱ እስኪመጣ ድረስ መጠበቅ ይኖርባቸዋል 49.2-4፡፡
የግል ውይይት፡- አንድ ሰው በግል ከመሐመድ ጋር ውይይት ከማድረጉ በፊት እራሱን ለማዘጋጀት በቅድሚያ ለድሆች ምፅዋትን ማድረግ አለበት 58.12፡፡
አሳፋሪ ነገር፡- መሐመድ ለጉዲፈቻ ልጁ ለዘይድ ሚስቱን እንዳይፈታና አላህን እንዲፈራ ነግሮታል ይህም መሐመድ በልቡ ሌላ ነገርን ቢያውቅም ነው (ያም እሱ እራሱ እንደ ወደዳትና እሷ የእሱ ሙሽራው እንደሆነች ቢያውቅም ነው)፡፡ መሐመድ ለዘይድ ሚስት የነበረውን ስሜት ለመደበቅ ሙከራን አድርጓል ይህም ሰዎች ምን ይላሉ በማለት ነበር፡፡ (የመሐመድ የጉዲፈቻ ልጁም የአባቱን ዝንባሌ በመረዳት) ሚስቱን ፈታትና ለመሐመድ ሚስት እንድትሆን ተሰጠች፡፡ ይህ ደግሞ አባቶች የጉዲፈቻ ልጆቻቸውን ሚስቶች ከተፈቱ በኋላ ማግባት ይችላሉ የሚል ሕግ ተደረገ፡፡ መሐመድም ይህንን ድርጊት በማድረጉ ሊከሰስ እንደማይገባው ተደረገ 33.37፣38፡፡
እጅግ በጣም ብዙ ሚስቶች፡- ሙስሊሞች አራት ሚስቶች ብቻ ከሴት ባሮቻቸው ጭምር እንዲኖራቸው ነው የተፈቀደላቸው 4.3፡፡ ነገር ግን መሐመድ (ከአራት በላይ ነው ያገባው) ይቅር ተብሏል፡፡ እሱ ያገባቸው ሚስቶቹ ስለፈቀዱለት እሱ ሊወነጀል አይገባውም፡፡ ይህም ከመካ ከእሱ ጋር የተሰደዱትን የአጎቱን ልጆች ይጨምራል፡፡ ይህም ለመሐመድ ብቻ እንጂ ለሌላ ለማንም ያልተሰጠ ዕድል ነበር፡፡ ልክ እንደሌሎቹ ሙስሊሞችም በጦር ከማረካቸው (የጦርነት ምርኮ ካደረጋቸው) ከባሪያ ሴቶቹ ጋርም የግብረ ስጋ ግንኙነት ማድረጉንም መቀጠል ይችላል 33.50፡፡
የሚስቶች ባሕሪ፡- ከመሐመድ ሚስቶች አንዷ ኃጢአትን ብታደርግ የምትቀጣው እጥፍ ነው፡፡ እሱንና አላህን የሚታዘዙት ሚስቶቹ ግን እጥፍ ሽልማትን ያገኛሉ፡፡ እነሱም እንደሌሎቹ ሴቶች አይደሉም፡፡ እነሱንም ለሚመኝና ለሌላ ሰው በቀስታ ድምፅ መመለስ የላባቸውም፡፡ የእሱ ሚስቶች ውበታቸውን ማሳየት የለባቸውም፡፡ እነሱም በቤት መቆየትና የሃይማኖት ተግባራቸውን ማሳየት አለባቸው 33.30-34፡፡
ትክክለኛ ያልሆነ ቅጣት አይፈቀድም፡- ከሌሎቹ ሙስሊም ወንዶች በተለየ መልኩ መሐመድ ለሚስቶቹ ሐቀኛ ወይንም እኩል ዕድልን ለመስጠት ከእነሱ ጋር በሚተኛበት ጊዜ በዙር ወይንም በተራ ማድረግ የለበትም፡፡ እንደዚሁም ደግሞ ለጊዜው ከዘጋቸው ሚስቶቹ ጋር ግንኙነትን ያደርጋል፣ ይህም እነሱ በስቃይ ውስጥ እንዳይሆኑ እና እሱም በሰጣቸው ደስተኞች እንዲሆኑ ነው 33. 51፡፡
የሚስቶች ከፍተኛ ጣሪያ ላይ መደረስ፡- ለመሐመድ ተጨማሪ ሚስቶችን ማድረግ ወይንም አሁን ያሉትን ሚስቶቹን በአዲስ ሚስቶች መለወጥ አይፈቀድም፣ ይህም በሌላ ሴት ውበት ቢሳብም ጭምር እንኳን ነው፡፡ መሐመድ ከአዲስ ሴት ጋር የግብረ ስጋ እንዲያደርግ የሚፈቀድለት ከአዲስ የሴት ባሪያ ልጃገረዶች ጋር ብቻ ከሆነ ነው 33.52፡፡
ታማኝ ላለመሆን የተሰጠ ይቅርታ፡- (መሐመድ ከኮፕቲክ ክርስትያን ባሪያ ሴት ጋር ግብረ ስጋ ላለማድረግ ቃል ኪዳን ገባ፡፡ ይህንንም ቃል የገባው ሐፍሳ የተባለችውን ሚስቱን ለማስደሰት ነበር፡፡ ቃል ኪዳኑን አፍርሶ በተያዘ ጊዜ በቁርአን አማኞች የሆኑት እነዚያ አላህ መሐላውን በጥያቄ እንደሰወረው አመኑ)፡፡ ‹አንተ ነቢዩ ሆይ አላህ ለአንተ የፈቀደልህን ነገር ሚስቶችህን ማስወደድን የምትፈልግ ስትኾን (ባንተ ላይ) ለምን እርም ታደርጋለህ አላህም እጅግ መሐሪ አዛኝ ነው፡፡ አላህ ለእናንተ መሐሎቻችሁን መፍቻ ደነገገላችሁ አላህም ረዳታችሁ ነው እርሱም ዓዋቂው ጥበበኛው ነው፡፡ ነቢዩ ከሚስቶቹ ወደ አንዷ (ምናልባትም ሐፍሳ) ወሬን በመሠጠረ ጊዜ (አስታውስ) እርሱንም በነገረችና (ምናልባትም አይሻ መሐመድ በዘጠኝ ዓመቷ እርሱ ከሃምሳ ዓመት በላይ ሆኖ ያገባትን) አላህ እርሱን (ማውራትዋን) ባሳወቀው ጊዜ ከፊሉን አስታወቀ ከፊሉን ተወ በርሱም ባወራት (ሐፍሳ) ጊዜ ይህን ማን ነገረህ? አለች ዐዋቂው ውስጠ ዐዋቂው ነገረኝ አላት፡፡ ወደ አላህ ብትመለሱ ልቦቻችሁ (ሁለቱ ሴቶች መሐመድን ከተቹበት ወይንም በስተኋላ ካሙበት)፡፡ በእርግጥ ተዘንብለዋልና (ትስሰማማላችሁ) በርሱም ላይ ብትረዳዱ አላህ እርሱ ረዳቱ ነው፡፡ ጂብሪልም ከምዕምናንም መልካሙ ከዚህም በኋላ መላእክቱ ረዳቶቹ ናቸው፡፡ (መላችሁንም) ቢፈታችሁ ከናንተ የበለጡ ሚስቶችን እስላሞች አማኞች ታዛዦች ተፀፃቾች (ለአላህ) ተገዢዎች ፆመኛዎች ፈቶች ደናግልም የኾኑትን ጌታው ሊለውጠው ይከጅላል› 66.1-5፡፡ ‹አላህ ለእነዚያ ለካዱት ሰዎች የኑሕን ሴትና የሎጥን ሴት ምሳሌ አደረገ ከባሮቻችን ከኾኑ ሁለት መልካም ባሪያዎች ስር ነበሩ ከዱዋቸውም ከአላህም (ቅጣት ኑሕና ሎጥ) ከሚስቶቻቸው ምንም አልገፈተሩላቸውም ከገቢዎቹም ጋር እሳትን ግቡ ተባሉ፡፡ ለነዚያ ለአመኑትም የፈርዖንን ሴት አላህ ምሳሌ አደረገ ጌታዬ ሆይ አንተ ዘንድ በገነት ውስጥ ለኔ ቤትን ገንባልኝ ከፈርዖንና ከሥራውም አድነኝ ከበደለኞቹ ሕዝቦችም አድነኝ ባለች ጊዜ፡፡ የዒምራንን ልጅ መርየምንም ያችን ብልቷን የጠበቀችውን (ምሳሌ አደረገ) በርሱም ውስጥ ከመንፈሳችን ነፍፋን በጌታዋ ቃላትና በመጻሕፍቱም አረጋገጠች ከታዛዦቹም ነበረች› 66.10-12፡፡
በመሐመድ ቤት ውስጥ ያለ ስርዓት፡- አንድ ሰው ከመሐመድ ቤቶች በአንዱ ውስጥ የእራት ግብዣ ከተጋበዘ ቀደም ብሎ መምጣት የለበትም እንዲሁም ደግሞ እራት ካለቀ በኋላ ለትንሽ ውይይትም ቢሆን መቆየት የለበትም፡፡ ይህ መሐመድን ይረብሸዋል ደግሞም ሰውየውን እንዲሄድ ለመጠየቅም ያሳፍረዋል፡፡ እንግዳው የሚፈልገው ምንም ነገር ቢኖረው የመሐመድን ሚስቶች በመጋረጃ ማነጋገር አለበት ይህም ለመሐመድ ሚስቶችና ለእንግዳው እጅግ ጥሩ ነገር ነው የሚሆነው 33.53፡፡
መሐመድን ማስቸገር፡- መሐመድን በማናቸውም መንገድ ማስቸገር፣ መተቸት፣ ታላቅ በደል ነው የሚሆነው 33.53፡፡
ልጅ አልባ ይሆናል፡- መሐመድ እጅግ በጣም ሀብታም በመሆኑ መፀለይና መስዋዕትን ማቅረብ አለበት፡፡ መሐመድንም የሚጠላ ሰው እሱ ዘር (ልጅ) አልባ ነው የሚሆነው 108.1-3፡፡
በኢየሱስ የተተነበየ ነው፡- የማርያም ልጅ ኢየሱስ ለእስራኤሎች የነገራቸው እሱ የመጣው ከእሱ በፊት የተገለጠውን የአይሁድን ቅዱስ መጽሐፍ ለማረጋገጥና እንዲሁም ከእሱ በኋላ የሚመጣውን ሌላ ሐዋርያ ስሙ አህመድ የተባለውን ለማብሰር ነው 61.6፡፡
የመሐመድ መበለቶች፡- መሐመድ ከሞተ በኋላ ሚስቶቹን ማግባት ለማንም ሰው ትክክል አይደለም፡፡ ይህም ታላቅ ኃጢአት ነው የሚሆነው 33.53፡፡
ምንም ተዓምር የለም፡- ሙስሊሞች ያልሆኑት ያስተዋሉት ነገር ሙሴ ተዓምራትን ሲያደርግ መሐመድ ግን ምንም ተዓምራትን አላደረገም፡፡ መሐመድም እራሱ በእሱ በኩል ምንም ተዓምራቶች እንዳልተደረጉ አምኗል 28.48፤ 10.20፤ 13.7፤ 6.37፡፡
የሰማይ መውደቅ፡- የሰማይ ከፊሉ ቢወድቅም እንኳን የማያምኑት የተደራረበ ደመና ነው በማለት ስለሚክዱ መሐመድ በዚህ ነገር መፅናናት አለበት 52.44፡፡
በሰይጣን የተያዘ ነው፡- ሙስሊም ያልሆኑት መሐመድን ትኩር ብለው በመመልከት እንደሚከተለው ይላሉ፡ ‹እሱ በሰይጣን የተያዘ ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም› 68.51፤ 25.8፡፡
የሐሰት ነቢይ፡- ሙስሊም ያልሆኑት የሚሉት መሐመድ የራሱን ቁጥሮች (ጥቅሶች) እራሱ ነው የፈጠራቸው 46.8፤ 52.33፤ 25.4፡፡
ዕብድ ነው፡- ሙስሊም ያልሆኑቱ መሐመድን እብድ ነው ሊሉ ይችላሉ 68.2፡፡ ጣዖትን የሚያመልኩቱ መሐመድ ምንም ተዓምራቶችን ስላላደረገ ስለ መሐመድ ቃላቶች ብቻ አማልክቶቻቸውን ሊክዱ አይችሉም፡፡ እነሱም የወሰኑት አማልክቶቻቸው እሱን በእድነት እንደረገሙት ነው 11.53-54፡፡
የልብ ወለድ ተረቶች፡- ሙስሊም ያልሆኑቱ የቁርአንን ይዘት ይቃወማሉ ምክንያቱም የተለመዱ የጥንት ተረቶች በቁርአን ውስጥ እንደ እውነተኛ ታሪክ ሆነው ቀርበዋልና፡፡ በቁርአን ውስጥም ያሉትን ተረቶች አንድ የሆነ ሰው ጊዜውን ሰጥቶ እነዚህን ነገሮች ለመሐመድን አስተምሮት ነው 16.24፤ 25.5፤ 68.15፤ 83.13፡፡
ከብዙ ግጥሞ መካከል ያለ ግጥም፡- የማያምኑት የሚሉት መሐመድ ገጣሚ ብቻ እንደሆነ ነው 52.30፡፡ በዚያን ጊዜም ገጣሚዎች በእያንዳንዱ ሸለቆ ውስጥ ይዘዋወሩ ነበር፡፡ እነሱም ስህተትን የሚያምኑ ተከታዮችን ይሰበስቡ ነበር፡፡ ገጣሚዎቹም እነሱ እራሳቸው የማያደርጉትን ነገር ለሌሎች ያስተምሩ ነበር 26.224-226፡፡
አስተማሪ፡- የማያምኑት መሐመድን የሚከሱት አንድ አረብ ያልሆነ ሰው ቁርአንን እንዲቀራ መሐመድን እንደረዳው (እንዳስተማረው) ነው 16.103፡፡
ምስጢራዊ ጉዞ፡- ባሪያውን ከመካ ወደ ኢየሩሳሌም የወሰደው አላህ ሊከበር ይገባዋል 17.1፡፡
ጠላቶች፡- መሐመድን እና አላህን የሚቃወሙትን ሰዎች ማንኛውም ሙስሊም ጓደኛ ሊያደርግ አይገባውም 58.22፡፡
ተጠራጣሪዎች እራሳቸውን መስቀል አለባቸው፡- አላህ መሐመድን ድል እንዲያደርግ አያስችለውም የሚልና የሚጠራጠር ማንም ቢኖር ገመድን ለራሱ ወስዶ በቤቱ ጣሪያ ላይ በማሰር እራሱን በዚያ ላይ መስቀል ይኖርበታል 22.15፡፡
የአዘጋጁ ማሳሰቢያ፡-
በቁርአን ውስጥ ስለመሐመድ የሰፈሩት 87 ጥቅሶች መሐመድ ምን ዓይነት ሰው እንደነበረ በግልጥ ይመሰክራሉ፡፡ እነዚህን ጥቅሶች በጥሞና መመልከት ስለምንከተለው እምነት ግንዘቤ ስለሚሰቱት በጣም ጠቃሚ ናቸው፡፡ ቀጥሎም አንድ ነቢይ ነው ብለን የምንቀበለው ሰው እንደዚህ ዓይነት ብዙ የተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ ማለፉን አስመልክቶ፣ ለምን? ከምን የተነሳ? የሚሉ ጥያቄዎችን መጠየቅ ይገባናል፡፡ ከዚህም ባሻገር ስለ ሕይወታችን የዘላለም ፍፃሜም በትክክል ልንጨነቅና ልናስብ ይገባናል፡፡ ከእግዚአብሔር ተልኬያሁ ብሎ የሚናገር ሰው ከእግዚአብሔር ላለመላኩ ግልጥ የሆነ ማስረጃ በራሱ ከተነገረ ቆም ብለን ልናስብ አይገባንምን? ይገባናል እንጂ!
ስለዚህም ሙስሊሞች ስለሚከተሉት እምነት ቆም ብለው እንዲያስቡና እውነትን የተጠሙ የዚህ ድረ-ገፅ ተከታታዮችን የምንመክረው መጽሐፍ ቅዱስን አግኝተው እንዲያነቡና በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ የወንጌል አማኞች ቤተክርስትያን በመሄድ የጌታን ቃል ትምህርት እንዲከታተሉ ነው፡፡ የእውነት ሁሉ ምንጭና መሠረት የሆነው ጌታ ኢየሱስ እንዲረዳችሁም ፀሎታችን ነው፡፡
የትርጉም ምንጭ: Mohammed, Chapter 10 of "A Topical Study of the Qur'an From a Christian Perspective" by M.J Fisher, M.Div
ሙሉ መጽሐፉ በአማርኛ: ርእሳዊ የቁርአን ጥናት በክርስትና አይን ሲመረመር
ለእስልምና መልስ አማርኛ ዋናው ገጽ