ሲዖል በቁርአን
M. J. Fisher, M.Div.
ትርጉምና ቅንብር በአዘጋጁ
በቁርአንና በመጽሐፍ ቅዱስ መካከል ካለው አንዱ ትልቅ ልዩነት በሲዖል ላይ የተሰጠው ትኩረት ወይንም አፅንዖት ነው፡፡ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ሲዖል አስራ አራት ጊዜ ብቻ ነው የተጠቀሰው፡፡ በነዚህም ጥቅሶች ውስጥ ጥቃቅን የሆኑ ዝርዝሮች አልተገለጡም፡፡ ቁርአን ምንም እንኳን ከአዲስ ኪዳን ይልቅ እጅግ ትንሽ ቢሆንም ሲዖልን ዘጠና አምስት ጊዜ ያህል ጠቅሶታል፡፡ (በዚህ ጽሑፍ በተዘረዘሩት አርባ ሰባት ጥቅሶች ውስጥ የተደጋገሙ ጥቅሶች አልቀረቡም)፡፡ መሐመድ ብዙውን ጊዜ ሲዖልን የጠቀሰው ቁርአንን ለማይቀበሉ እንደ ማስፈራሪያ እንዲሆን አድርጎ ነው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ ሲዖልን ከገሃነም ጋር ያያይዘዋል ይህም ያለማቋረጥ በእሳት ከሚቀጣጠለውና ከኢየሩሳሌም ውጪ ካለው የቆሻሻ መጣያ ጋር በማመሳሰል ነው፡፡ ይህም ሲዖልን የሚያስመስለው የውጪ፣ የጨለማ፣ የልቅሶና የእሳት ቃጠሎ ስፍራ እንደሆነ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በግልፅ የሚያውጀው እግዚአብሔር ሰዎችን ከሲዖል ካላዳናቸው በስተቀር ለሰዎች ሁሉ የማይቀር የስቃይ ስፍራ አድርጎ ነው፡፡ እግዚአብሔር ዓለሙን እንደዚህ ስለወደደ በክርስቶስ ኢየሱስ በኩል ወደ ምድር መጥቶ የእሱን ይቅርታና ዘላለማዊ ሕይወትን ለሚቀበሉቱ ተሰቃይቶ በመሞት ስቃያቸውንና ሲዖላቸውን ተክቶላቸዋል፡፡ እንደዚህ በቅፅበት የዳነው ሰው በመስቀል ላይ ከኢየሱስ ጎን የተሰቀለው ሰው ነበር፡፡ እሱም አብሮት የተሰቀለው ወንጀለኛ ያሳየው ከነበረው ማሾፍ ስለጌታ ሲከራከርና ቀጥሎም ጌታ ኢየሱስ በመንግስቱ በመጣ ጊዜ እንዲያስታውሰው ሲጠይቅ ነበር፡፡ ጌታ ኢየሱስም ቃል የገባለት በገነት ከእሱ ጋር አብረው እንደሚሆኑ ነበር ሉቃስ 23.39-43፡፡
ቁርአን የመጽሐፍ ቅዱስን የሲዖል እሳት ስቃይ ሐሳብ ይደግመዋል፣ ነገር ግን ከዚህ በመቀጠል የሚገልጠው ስጋዊ የሆነን ቶርቸርን (ስቃይን) ነው፡፡ ዝርዝር ነገሮች ከሆኑትም ውስጥ በመላእክት መገረፍንና በሰንሰለት ታስሮ መጓዝን ሁሉ ይጨምራል፡፡ እጅግ በጣም ዝርዝር ሁኔታ ውስጥ በመግባት አንዳንዴም እርስ በእርስ በሚጋጭ ሁኔታ ያቀርበዋል፡፡ ለምሳሌም ያህል በሲዖል ውስጥ የሚኖረው ምግብ ‹ዳሪዕ› ነው የሚሆነው ወይንም መራራ አትክልት ነው ይላል፡፡ ከዚያም ቁርአን የሚጨምረው ብቸኛ ምግብ የሚሆነው ቆሻሻ ነው በማለት ሲሆን ቀጥሎም በሲዖል ያሉ ሰዎች ምግብ የሚሆነው ዛኩም ከተባለ ዛፍ ያለ ፍሬ ነው ይላል፡፡
ሌላው የሚቃረን አባባል ደግሞ በሰንሰለት የመታሰር ጉዳይ ነው፡፡ የጠፉት ከባድ ሸክምን ተሸክመው እንዲጓዙ ወይንም ደግሞ በፈላ ውሃ ውስጥና በእሳት ውስጥ ይጎተታሉ ወይንም ከሌሎች ጋር አብረው በጥልቅ ጉድጓድ ውስጥ አብረው ይታሰራሉ ይላል፡፡
ሙስሊሞች ስለመጽሐፍ ቅዱስ ከሚቃወሙት ነገር ውስጥ አንዱ የይቅርታ የነፃ ስጦታ መኖርን ነው ኤፌሶን 2.8-10፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የሚገልጠው የክርስቶስ መስቀልና የትንሳኤው ድል ለሚያምኑቱ የሲዖልን ኃይል እንዳሸነፈው ነው ይህም ደግሞ ለእግዚአብሔር የሚኖሩበትን መነሳሳትና ችሎታን እንዲያገኙ አድርጓቸዋል፡፡ ሙስሊሞች ሁልጊዜ እንደሚያምኑት የሲዖል ማስፈራራት በማንኛውም ሰው ፊት ሁልጊዜ መቀመጥ እንዳለበት ነው ይህም ለሙስሊሞችም እንኳን ነው፡፡ ምክንያቱም ጥሩ ሕይወትን ለመኖር ይችላሉና፡፡
ስለዚህም ቁርአና ስለ ሲዖል የሚከተሉትን ጥቅሶች ይናገራል፡-
ሲዖልን መሙላት፡- አላህ ቢፈቅድ ኖሮ ለእያንዳንዱ ሰው እውነተኛ ምሪትን በሰጠ ነበር፣ ነገር ግን የአላህ ቃል የሚለው እሱ ሲዖልን በሰዎችና በጅኒዎች እንደሚሞላው ነው (32.13፣ 11.119፣ 7.18)፡፡
እሳት፡- ኃጢአተኛው በሲዖል ውስጥ ይቃጠላል 82.14፡፡ እሳቱም የሚለኮሰው በአላህ ነው እሱም እስከ ደረት ድረስ ከፍታ ያለው ነው በበላያቸው ተለኩሶ በዙሪያቸው ይከባቸዋል 104.6-9፡፡ በፍርድ ቀን ሰዎች በሲዖል እሳት ውስጥ ይላጫሉ ይህም እነሱ የካዱት እሳት ይህ ነው እየተባሉ እየተነገራቸው ነው እናም በስራቸው ውጤት የተነሳ እዚያ ውስጥ ይቃጠላሉ 52.11-16፡፡
መጠጥ፡- የማያምኑት በፍርድ ቀን የፈላን ውሃ እንዲጠጡ ይሰጣቸዋል 88.5፡፡
ምግብ፡- ሲዖል ውስጥ የሚኖረው ምግብ ዳሪዕ ብቻ ነው (እሾኸማ መራራ አትክልት ሲሆን ሽታውም መልኩም መጥፎ ነው)፡፡ እሱም ረሃባቸውን በፍፁም አያረካላቸውም 88.6፡፡ እዚያም የሚኖረው ብቸኛ ምግብ ከቁስል እጣቢ የሚመጣ ቆሻሻ ብቻ ነው 69.36፡፡ የነሱም ምግብ የሚሆነው ከዘቁም ዛፍ ነው ይህም የሚበለቅለው በሲዖል ጫፍ ላይ ነው ፍሬውም የሰይጣን እራስ የመሰለ ሲሆን እንዲጠግቡም ይበሉታል ከዚያም የፈላ ውሃን ጠጥተው ተመልሰው ወደሲዖል ውስጥ ይጣላሉ 37.62-68፡፡
ሰንሰለቶች፡- ሰዎች በሰንሰለት ታስረው ሰባ ክንድ እንዲጓዙ ይደረጋል 69.32፡፡ ከማንኛውም ለሐዋርያት በተሰጡት ቅዱስ መጽሐፍ (መጽሐፍ ቅዱስ ወይንም ቁርአን) ጋር የማይስማሙት እነዚያ በአንገቶቻቸው ላይ ሰንሰለት ታስሮባቸው በፈላ ውሃ ውስጥ ይጎተታሉ ከዚያም በፍርድ ቀን ወደ እሳት ውስጥ ይጣላሉ 40.69-72፡፡ እነሱም አብረው ታስረው በጠባብ ስፍራ ተጥለው ሞትን ይለምናሉ 25.13፡፡
የሹፈት ጥያቄዎች፡- ኃጢአተኞች በገነት ውስጥ በሚኖሩት ሰዎች የሚከተሉትን ጥያቄዎች ይጠየቃሉ፡- ‹ወደ ሲዖል እንድትጣሉ የተደረጋችሁት ምን ስለሰራችሁ ነው?› መልሳቸውም የሚሆነው እንዳልፀለዩና ረሃብተኞችን እንዳልመገቡ ነው፣ እንዲሁም ሰዎችን እንዳሙና የፍርድ ቀንን እንደካዱ ነው 74.40-46፡፡ የገነትም ነዋሪዎች በሲዖል ውስጥ ባሉት ላይ ያሾፉባቸዋል 7.44-50፡፡
ማለቂያ የሌለው ነው፡- በሲዖል ያለው ስቃይ በፍፁም አያቆምም እንዲሁም ደግሞ በሲዖል ያሉት እነዚያ ምንም ምህረት አይደረግላቸውም 16.85፡፡
በመላእክት ይመታሉ፡- የማያምን ሰው በሚሞትበት ጊዜ ነፍሱን መላእክት ይሸከሙና ይወስዱታል ከዚያም ፊቱን እና ጀርባውን እየመቱት ‹የሲዖልን እሳት ስቃይ ቅመስ› ይሉታል 8.50፡፡
የብረት በትር፡- የማያምኑት በብረት በትር ይገረፋሉ (ይቀጣሉ) 22.21፡፡
የአዘጋጁ ማሳሰቢያ፡
የሲዖል ስቃይ እጅግ አስፈሪ ነው፡፡ ዘላለማዊም ነው፡፡ እግዚአብሔር እራሱ ሰዎችን ከሲዖል ስቃይ ካላዳናቸው በስተቀር ማንም ሊያድናቸው አይችልም፡፡ ሰዎች ከሲዖል ስቃይ እንደሚድኑ እንዴት ሊያውቁ ይችላሉ? እግዚአብሔርስ እንዴት ነው ሊያድናቸው የሚችለው? እነዚህ ጥያቄዎች በጣም አስፈላጊ ናቸው፡፡ እዚህ ምድር ላይ ሆነን ከሲዖል ስቃይ የምናመልጥ ለመሆኑ የምንከተለው እምነታችን ዋስትና የማይሰጠን ከሆነ ከንቱ እና ምንም የማይጠቅም ነው፡፡ ስለ ሲዖል አስፈሪነት አስረድቶንና አሳይቶን መፍትሄውን የማያሳየን ከሆነ ከንቱ ማስፈራራት ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሔር ግን ሰዎች ከሲዖል ፍርድ እንዲድኑ እና መዳናቸውንም በትክክል እንዲያውቁ ይፈልጋል፡፡ ይህንንም ያደረገው ሲዖል ለሚገባቸው ኃጢአተኞች ንፁህ መስዋዕትን እራሱ በመክፈል የሲዖል ፍርዳቸውን በመውሰድ ነው፡፡ ይህንንም ያደረገው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ብቻ ነው፡፡
ስለዚህም ሰዎች ኃጢአታቸውን በመናዘዝ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በተከፈለው ዋጋ የሚያምኑ ከሆነ፡፡ ከኃጢአታቸው ይቅርታን በመቀበል በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ከሲዖል ፍርድ ለመዳናቸውና የዘላለምን ሕይወት እርግጠኝነት እንዳገኙ ይረጋገጥላቸዋል፡፡ ይህንን በሕይወታቸው በእውነት ይለማመዳሉ በትክክልም ያውቁታል፡፡ አንባቢ ሆይ ወደዚህ እውነተኛ ተስፋ በመምጣት የደኅንነትን እውነት እንድትቀምስ እንዲሁም እንድትድን ወደ ክርስቶስ እውነተኛ መንግስት እንድትመጣ እንጋብዝሃለን፡፡ ለዚህም የሚረዳህን መጽሐፍ ቅዱስን አግኝተህ ብታነብ ስለዚህ እውነት የበለጠ ልትገነዘብ ትችላለህ እንዲሁም ደግሞ በአቅራቢያህ ወደሚገኝ የወንጌላውያን ቤተክርስትያን በመሄድ የጌታን ቃል ስማ፡፡ ለምን ለዘላለም መውጫ ወደሌለው ወደሲዖል ትሄዳለህ? ጌታ ይርዳህ፡፡
የትርጉም ምንጭ: Hell, Chapter 10 of "A Topical Study of the Qur'an From a Christian Perspective" by M.J Fisher, M.Div
ሙሉ መጽሐፉ በአማርኛ: ርእሳዊ የቁርአን ጥናት በክርስትና አይን ሲመረመር
ለእስልምና መልስ አማርኛ ዋናው ገጽ