ነፃ ፈቃድና - የአስቀድሞ ውሳኔ
M. J. Fisher, M.Div.
ትርጉምና ቅንብር በአዘጋጁ
መግቢያና ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ንፅፅር
ቁርአንና መጽሐፍ ቅዱስ በጋራ ያላቸው አንድ ነገር ቢኖር በነፃ ፍቃድና በአስቀድሞ የምርጫ ውሳኔ ላይ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በግልፅ የሚያቀርበው አንድ ሰው በእግዚአብሔር ካልተነሳሳና በእግዚአብሔርም ብርሃንን ካላገኘ እንደማያምን ሲሆን በእግዚአብሔር ኃይል የተቀሰቀሱት ሰዎች ደግሞ የማመን ሃላፊነት እንዳለባቸው ነው፡፡ እነዚህን ሁለቱንም እውነቶች መጽሐፍ ቅዱስ በትክክል ያስቀምጣል፣ ዮሐንስ 6.35-51፡፡ ክርስትያን ቲዎሎጂያኖች እነዚህን ተቃራኒ የሚመስሉ ሐሳቦች ለመረዳት ለዘመናት ታግለዋል (በትክክል ሲታይ ግን ተቃራኒ አይደለም)፡፡ አንዳንድ አዋቂዎች በዚህ ጉዳይ ላይ ነፃ ፈቃድ ብዙ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃ አለው በማለት ሲናገሩ፣ ሌሎች ደግሞ የእግዚአብሔር ሉዓላዊ ፈቃድ በሁሉ ነገር ላይ ወሳኝ ነው ይህም ደኅንነትንም ይጨምራል በማለት ይናገራሉ፡፡ አሁንም ሌሎች የሚያምኑት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉት እነዚህ ሁለቱም እውነቶች በእግዚአብሔር ብቻ ግልፅ የሆኑና አብረው የሚሄዱ ወይንም የሚገኙ እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡
ቁርአን ከመጽሐፍ ቅዱስ ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ ስለተጻፈ የመጽሐፍ ቅዱስን ብዙዎቹን ዋና ዋና ሐሳቦች እንደሚያስተጋባቸው እርግጠኛ የሆነ ነገር ነው፡፡ ስለዚህም ተቃራኒ የሚመስሉት ‹መምረጥ› እና ‹መመረጥ› በውስጡ ይገኛሉ፡፡ ለማነፃፀርም ያህል በቁርአን ውስጥ ያሉት ጥቅሶች መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ካሉት ጥቅሶች በበለጠ መልኩ እጅግ ጠንካራ ሐሳብ ይዘዋል፡፡ ሰዎች የመወሰን ሃላፊነት ያለባቸው መሆኑን የሚናገሩት የቁርአን ጥቅሶች እጅግ በጣም ጠንካራዎች ናቸው፣ እንደዚሁም አላህ በሚያምኑትና በማያምኑትም ላይ የበላይ ተቆጣጣሪነት እንዳለው የሚናገሩትም ጥቅሶች እንደዚሁ በጠንካራ ሁኔታ ነው የተቀመጡት፡፡
ክርስትያኖች እንደዚህ ዓይነት በጣም ግልፅ ያልሆኑላቸውን ነገሮች የሚወስዱት ልክ የቅዱስ ስላሴን አስተምህሮ በሚወስዱበት መንፈስ ነው፡፡ አንዳንድ እውነቶች ከሰው መረዳት ውጪ እንደሆኑ ክርስትያኖች ያምናሉ ምክንያቱም የእግዚአብሔር መንገዶች ከእኛ ውሱን የመረዳት ችሎታ በጣም ከፍ ያሉ ናቸውና፡፡ ይሁን እንጂ ብዙ ሙስሊሞች ከዚህ የነፃ ፈቃድና የምርጫ ውሳኔ ሐሳብ ግልፅ አለመሆን ጋር ይታገላሉ፡፡ ከዚህ በታች የሰፈሩትን ሃያ ስድስት የጥቅሶች ስብስብ የሚያነብ ሙስሊም ሁሉ እውነተኛ የሆነ የእምነት ግጭት ሊፈጠርበት ይችላል፡፡ የዚህም ምክንያቱ በቁርአን ውስጥ ያሉ ትምህርቶች የተቀመጡት ሎጂካዊ ሆነው ነው ወይንም በሆነ መልኩ ነው በማለት ያምናልና፡፡ እንደዚሁም ደግሞ በሰዎች ሁሉ ውስጥ ተመሳሳይ የሎጂክ አካሄድ ደረጃ እንዳለም ሙስሊሞች ያምናሉ ይህም የስላሴን ትምህርት ለመካድ ተጨማሪ ምክንያት እንደሆነ ያስባሉ፡፡ ነገር ግን እነሱ በእምነታቸው የተተውት ሎጂካዊ ባልሆነውና ግራ በሚያጋባው ነፃ ፈቃድና የቅድሚያ ውሳኔ ሐሳብ ውስጥ ነው፡፡
ስለዚህም ቁርአን የሚከተሉትን ይናገራል፡-
ውሳኔዎች፡- ‹ቁርአን እሱ የዓለማት መገሠጫ እንጂ ሌላ አይደለም፡ ከእናንተም ቀጥተኛ መኾንን ለሻ ሰው (መገሠጫ ነው)፡፡ የዓለማት ጌታ አላህ ካልሻም አትሹም› 81.27-29፡፡ 76.29-30፡፡ (የዓለማት ጌታ ካልፈለገ እናንተ አትፈልጉም የሚል ሐሳብ ነው)፡፡
ፈተናው፡- ሰው ከወንድ ዘር ጠብታ ነው የተፈጠረው የዚህም ዓላማው ለመፈተን ነው፡፡ እሱም የማየትና የመስማት ትዕዛዛትን ተሰጠው ይህም ወደ ገነት ለመግባት ምስጋና ያለው መሆኑን ለማየት ነው፡፡ በገነትም ውስጥ የሚኖረው ከማያቋርጥ ወንዝ ውስጥ የሚመነጨውን ወይን ጠጅ ለመጠጣት ነው በሲዖል ውስጥ ግን ያለው በሰንሰለት መታሰር መጨነቅ እና የሚያቃጥል እሳት ነው 76.2-6፡፡
ምሪት፡- አላህ ደስ የሚያሰኘውን ሁሉ በቀናው መንገድ ይመራል 10.25፡፡ አላህ ነው የሚመራውንና የሚጣለውን የሚወስነው 35.8፡፡ አላህ ለእስላም ልብን ይከፍታል ወይንም ያጠነክራል 39.18-22፡፡ እሱ ለአንዳንዶች ጥቂት ለሌሎች ደግሞ ብዙን ይሰጣል 39.52፡፡
እምነት፡- አላህ ፈቃድ ካልሰጠው በስተቀር ማንም እምነት ሊኖረው አይችልም፡፡ የእምነት ስሜት የሌላቸውን እነዚያን አላህ በጣም አጥብቆ ይቀጣቸዋል 10.100፡፡
የተወሰነ ዕድለ ቢስነት፡- በግለ ሰቦች ላይና በምድር ውስጥ የሚሆነውን ነገር አላህ አስቀድሞ ወስኖታል 57.22፡፡
በፍጥረታት ሁሉ ላይ ቁጥጥር፡- በአላህ እጅ ቁጥጥር ስር ያልሆነ ምንም ፍጡር በምድር ላይ አይኖርም 11.56፡፡
ለገሃነም ተፈጠሩ፡- አላህ የሚመራው ሁሉ በቀና መንገድ ይሄዳል አላህ እንዲጠፋ ያደረገው ደግሞ ከጠፊዎቹ ይሆናል፡፡ ብዙ ሰዎችና ጅኒዎች የተፈጠሩት ለሲዖል ነው 7.178-179፡፡
አላህ ስህተትን ያስከትላል፡- አላህ እንዲሳሳቱ ያደረጋቸውን አንድ ሰው ሊያስተካክላቸው በፍፁም አይችልም 4.88፡፡
የግል ሃላፊነት፡- የአላህን ንግግር የማይቀበሉት እነዚያ ድዳና ደንቆሮዎች ናቸው፡፡ እነሱም በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ነው ያሉት፡፡ አላህ አንዳንዶችን ያሳስታል አንዳንዶችን ደግሞ በቀጥታው መንገድ ያስቀምጣል 6.39፡፡ ሐዋርያት ለሰዎች ልጆች ሁሉ የምስራችን እና የማስጠንቀቂያ ዜና ይሰጣሉ፡፡ የሚሰሙና መንገዳቸውን የሚያተካክሉት እነዚያ የሚፈሩትና የሚፀፀቱበት ምንም ነገር አይኖራቸውም፡፡ የአላህን መገለጥ የሚክዱት እነዚያ ግን ለኃጢአታቸው ይቀጣሉ 6.48-49፡፡
ክፉ መሪዎች ተሰጥተዋል ደግሞም ይቀጣሉ፡- በእያንዳንዱ ከተማ ውስጥ ክፉ ነገርን የሚያቅዱትን ክፉ መሪዎችን አላህ አስቀምጧል፡፡ እነሱም ለዚህ ክፉ እቅዳቸው ይቀጣሉ 6.123፣124፡፡
ሲዖልን መሙላት፡- አላህ ቢፈቅድ ለሁሉም ሰው እውነተኛን ምሪት ያደርግ ነበር፣ ነገር ግን የአላህ ቃል የሚለው እሱ ሲዖልን በጅኒዎችና በሰዎች እንደሚሞላ ነው 32.13፣ 11.119፣ 7.18፡፡
የአዘጋጁ ማሳሰቢያ፡-
በአላህ በመመረጥ የእስልምናን እምነት መከተልና ደግሞም በአላህ ስላልተመረጡ አለማመን ወይንም ለመከተል አለመቻል ወይንም በስተመጨረሻ ሲዖል መግባት ከዚህ በላይ ያየነው የቁርአን ትምህርት ነው፡፡ ይህንን ትምህርት ከዚህ በላይ በተጠቀሱት ጥቅሶች መሰረት ቁርአን የማስተማሩ ነገር፣ ትምህርቶችን በትክከለኛ አዕምሮ ለሚመረምሩና እውነተኛ ለሆኑት ሙስሊሞች እጅግ በጣም ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ ከዚህም የተነሳ ማንኛውም ሙስሊም በየትኛውም የእምነቱ ደረጃ ላይ ያለ ቢሆን በአላህ ስለመመረጡና ብሎም መንግስተ ሰማይ ወይንም ገነትን ለመውረስ ስለመቻሉ እርግጠኞች ሊሆን አይችልም፡፡
በመሆኑም ሙስሊሞች ሁሉ የሚኖሩት በጥርጥርና በፍርድ ቀን ፍርሃት ደግሞም ያለምንም የዘላለም ሕይወት ተስፋ ነው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ በሌላ ጎኑ የሚያቀርበው ትምህርት ግን ቅዱስ እግዚአብሔርን በማመን እርሱ እራሱ ባዘጋጀው የደኅንነት መንገድ ወደ እራሱ የሚመጡት ሰዎች፣ ታላቅ መንፈሳዊ እውነተኛ ለውጥን እንደሚያገኙ ነው፡፡ የደኅንነቱም መንገድ በግልፅ እና በሚገባቸው ሁኔታ በወንጌል ስብከት በኩል ስለሚገጥላቸውና እግዚአብሔር ባዘጋጀው የደኅንነት መንገድ በአዳኙ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ወደ እርሱ ሲመጡ የኃጢአት ሙሉ ይቅርታና የዘላለም ሕይወትን እርግጠኛ ተስፋ ያገኛሉ፡፡
ይህ ደግሞ ባዶ ተስፋ ሳይሆን በሕይወታቸው ውስጥ እግዚአብሔር በመንፈሱ ከሚሰራው ለውጥ የተነሳ በትክክል የሚያውቁት ነገር ይሆንላቸዋል፡፡ ስለዚህም ለእውነተኛ ክርስትያኖች መንግስተ ሰማይ የመግባት ጉዳይ ጥርጥር የሌለው ነገር ነው፡፡ እንደዚህ ካልሆነ ደግሞ ሃይማኖት አለኝ፣ የዚህና የዚያ እምነት ተከታይ ነኝ የሚለው ነገር ባዶና ምንም ጥቅም የሌለው ሆኖ ብቻ የሚቀር ነው፡፡
ስለዚህም የዚህ ድረ-ገፅ አዘጋጆች ለሙስሊሞች ሁሉ የሚያስተላልፉት የፍቅር መልእክት ወደዚህ እርግጠኛ እውነትና እምነት ዛሬ ነገ ሳይሉ እና ሳይዘገዩ ንስሐ በመግባት እንዲመጡ ነው፡፡ ሙስሊሞች ሁሉ እንደሚያውቁት የፍርድ ቀን ይመጣል ነገር ግን ያለ እውነተኛና እርግጠኛ ተስፋ ደግሞም ያለ አዳኙ ያለ ጌታ ኢየሱስ ማንም ሰው ከሚመጣው ፍርድ ሊያመልጥ አይችልም፡፡ ስለዚህም ወደ ጌታ ኢየሱስ መምጣት እንድትችሉ መጽሐፍ ቅዱስን በጥሞና እንድነታነቡና በቃሉ መሠረት ወደሚወዳችሁና በእነዚህ መልእክቶች አማካኝነት ወደራሱ ወደሚጠራችሁ እግዚአብሔር እንድትመጡ በክርስቶስ ፍቅር እንጋብዛችኋለን፡፡ እግዚአብሔር በታላቅ ምህረቱ ይርዳችሁ አሜን፡፡
የትርጉም ምንጭ: Free Will - Predestination, Chapter 12 of "A Topical Study of the Qur'an From a Christian Perspective" by M.J Fisher, M.Div
ሙሉ መጽሐፉ በአማርኛ: ርእሳዊ የቁርአን ጥናት በክርስትና አይን ሲመረመር
ለእስልምና መልስ አማርኛ ዋናው ገጽ