መጽሐፍ ቅዱሳዊ ገፀ ባሕርያት በቁርአን

M. J. Fisher, M.Div.

ትርጉምና ቅንብር በአዘጋጁ

መግቢያ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ንፅፅር

በቁርአን ውስጥ መሐመድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆኑ ሰዎችን ታሪኮች በብዛት ሲጠቅስ ይታያል፡፡ ይህንንም መሐመድ በጣም ብዙ ጊዜ አድርጎታል፡፡ በዚህም ጽሑፍ ውስጥ ያለው ስብስብ አራት መቶ አስራ ሁለት የሆኑትን ይዟል፡፡ አንዳንዶቹ ታሪኮች ከመጽሐፍ ቅዱሳዊው ጉድኝታቸው ጋር የሚስማሙ ሲሆኑ ሌሎቹ ግን በጣም የተለዩ ናቸው፡፡ ይህ ለሙስሊሞች እጅግ አስቸጋሪ ነው ምክንያቱም ቁርአን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር እንደሚስማማ ይናገራልና፡፡ በመሐመድ ዘመን ለነበሩት ክርስትያኖችና አይሁዶች የእነሱ መጽሐፍ በመንፈስ ቅዱስ የተሰጠና የጥንት ነቢያትና የሐዋርያቱ ትክክለኛ መልእክት እንደነበረ፣ እውነተኛም እንደሆነ እርግጠኞች ነበሩ፡፡ ለእነሱም በመጥሐፍ ቅዱስና በቁርአን ታሪክ መካከል ያለው ቅራኔ መሐመድ የሐሰት ነቢይ የመሆኑ ምልክት ነበረ፡፡

ለምሳሌም ሰይጣን ለአዳም ስላልሰገደ መወገዙን መጽሐፍ ቅዱስ አይናገርም፡፡ እንዲሁም ደግሞ ንጉሱ ሰለሞን ከወፎች ጋር መነጋገሩንና እነሱንም ማዘዙን መጽሐፍ ቅዱስ አይናገርም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ አብርሃም ካባን በመካ እንደገነባ እና የአረብ ነቢይ ከመገለጥ ጋር እንዲመጣ እንደፀለየ አይናገርም፡፡ ኢየሱስ ከሸክላ ሕይወት ያላትን ወፍ እንደፈጠረ እንዲሁም ስለ መሐመድ መምጣት ትንቢትን እንደተናገረ መጽሐፍ ቅዱስ አይናገርም፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ መሆኑን የሚያስተምረውን ግልጥ የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት ቁርአን አይቀበለውም፡፡ ኢየሱስ ሕይወቱን በመስቀል ላይ መስጠቱን ቁርአን ይክዳል፡፡ ስለዚህም ኢየሱስን ልክ እንደማንኛውም ነቢይ ያደርገውና ሰው የሆነው አምላክ ከሚለው እውነታ ዝቅ ያደርገዋል፡፡  

ከነዚህም ቅራኔዎች በተጨማሪ ቁርአን ባስቀመጣቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ታሪኮች ላይ የታሪካዊ ችግሮች ያሉበት ይመስላል፡፡ ወደ አንድ አምላክ አምልኮ የተለወጡትን  አስማተኞቹን ፈርዖን እንደሰቀላቸው ቁርአን ይናገራል፡፡ የአገዳደሉም መንገድ ሮማውያን በኋለኛው ዘመን ይጠቀሙበት የነበረው ዓይነት ነው፡፡ በሙሴ ጊዜ የወርቁን ጥጃ የሠሩት ሰማርያውያን እንደሆኑ ይናገራል ነገር ግን በዚያን ጊዜ ሰማርያ የሚባል ስምና ቦታ አልነበረም፡፡ የተባረከችው ሴት የኢየሱስ እናት ማርያም የአሮን እህት ናት በማለት ቁርአን ይናገራል፤ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ግን የሙሴና የአሮን እህት የነበረችው ማርያም ጥንት እንደነበረች ነው (የኢየሱስ እናት ማርያም ደግሞ ሌላ እንደነበረች ነው)፡፡ የቁርአን ተቺዎች በዘመናት ሁሉ የተናገሩት ነገር መሐመድ በሙሴና በአሮን እህት ማርያምና በጌታ በኢየሱስ እናት ማርያም መካከል መምታታትን እንዳደረገ ነው፡፡

እነዚህ ሁሉ ችግሮችና ልዩነቶች ለእስልምና እጅግ በጣም አስቸጋሪዎች ናቸው፡፡ እነሱ ችግሮች ናቸው ምክንያቱም ቁርአን ሙስሊሞች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ጠንካራ እምነት እንዲኖራቸው ሲያዝ በተመሳሳይ ጊዜ ቁርአን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ይቃረናልና ነው፡፡ ከዚህም አስቸጋሪ መምታታት ውስጥ ለመውጣት ያለው ብቸኛ የሙስሊሞች መንገድ ክርስትያኖችንና አይሁዶችን መጽሐፍ ቅዱስን ለውጠውታል በማለት መክሰስ ብቻ ነው፡፡

ለእነዚህ ሁሉ ክሶች ክርስትያኖች እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ አስደናቂ ማስረጃዎችን ያቀርባሉ፡፡ Dead Sea Scrolls በመባል የሚታወቁት የብዙ ሺ ጥንታዊ የአዲስ ኪዳን ጽሑፎች መገኘት ከማስረጃዎቹ ውስጥ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ እነዚህ እጅግ በጣም ብዙ የሆኑት በእጅ የተገለበጡ ጽሑፎች አሁን ካሉት ጋር ሲወዳደሩ የሚያሳዩት እውነታ አይሁዶችና ክርስትያኖች ቅዱሳን መጽሐፍቶቻቸውን እጅግ በጣም በከበረ እና ክብር በሰጠ መንገድ ይገለብጧቸው እንደነበረ ነው፡፡ እነሱም የራዕይን መጽሐፍ የመጨረሻ ጥቅስ እጅግ በጣም የምር አድርገው ወስደውት እንደነበረ ነው ምክንያቱም የእግዚአብሔርን ቃል አንዲት ቃል መቀየር እንኳን የሚያስከትለውን አሰቃቂ ውጤት ተገንዝበው ነበርና ራዕይ 22.18-21፡፡

ስለዚህም ቁርአን የሚከተለውን ይናገራል፡-

ሰይጣን አዳምና ሔዋን፡- መላእክቱ በአዳም ፊት እንዲሰግዱ በተናገራቸው ጊዜ ከጂኒ በስተቀር ሁሉም በአዳም ፊት ሰገዱ 18.50፡፡ ሰይጣን በአዳም ፊት መስገድ ነበረበት ይህም አላህ አዳምን ከሰራው በኋላ እና የአላህን የሕይወት እስትንፋስ እፍ ካለበት በኋላ ነበር፡፡ ሰይጣን በጣም ኩሩ ነበር እንዲሁም በአላህ መልእክት አላመነም ነበር ምክንያቱም ሊጂካዊ አልነበረምና፡፡ ሰይጣን ከእሳት ተፈጥሮ እያለ 38.71-76 ከአፈር ለተፈጠረው እንዲሰግዱ አላህ የሚፈቅደው ለምንድነው? ሰይጣንም ከገነት ውስጥ ተባረረ ምክንያቱም ለአዳም አልሰገደም ነበርና፡፡ አላህም ለእሱ እስከ ፍርድ ቀን ድረስ የሚሆንን ተግሳፅ ሰጠው፡፡ ሰይጣንም በአላህ ላይ በቀልን ለማድረግ መሐላን አደረገ ይህም የሰዎችን ልጆች በማጥቃት ነው፣ ሰውንም ኃጢአት እንዲያደርግ መራው:: ሰይጣንም የሰዎችን ልብስ ከላያቸው ላይ ገፈፋቸው ይህም አፍረታቸውን ለመግለጥ ነበር፡፡ እሱም አዳምንና ሄዋንን አላህ እንዳይበሉ የከለከላቸውን አትክልት እንዲበሉ አሳሳታቸው፡፡ አዳምና ሄዋንም ምህረትን ለመኑ ስለዚህም በሕይወት እንዲኖሩ ተፈቀደላቸው 7.11-27፣ 20.115-122፣ 38.71-85፣ 2.30-37፡፡

ኖህ፡- በዘመኑ የነበሩትን የጣዖት አምላኪዎች ከጥፋቱ ውሃ እራሳቸውን እንዲያድኑ ኖህ ገፋፍቷቸዋል፡፡ የጥፋቱም ወሃ ሲመጣ ኖህ ፀለየ ኃጢአቱ እና የወላጆቹ እንዲሁም በቤቱ ውስጥ የተጠጉት የአማኞች ሁሉ ኃጢአት ይቅር እንዲባልለት ፀለየ፡፡ እንዲሁም ከማያምኑቱ አንዳቸውም እንዳይድኑ ፀለየ፡፡ እሱም ኃጢአተኞች የበለጠ እንዲጠፉ ፀለየ 71.1-28፣ 10.71-73፡፡ ኖህም ከእያንዳንዱ እንሰሳት ወንድና ሴት አድርጎ ወደ መርከቡ ውስጥ ወሰደ ነገር ግን ወንድ ልጁ በተራራዎች መጠጊያን ለማግኘት በስተኋላ ቀረ፡፡ የኖህ ልጆች ከኃጢአተኞች ጋር ሞቱ 11.25-48፡፡ ኖህም የጥፋቱ ውሃ ከመምጣቱ በፊት በሕዝቡ መካከል ለዘጠኝ መቶ ሃምሳ ዓመታት ያህል ኖረ 29.14፡፡

መልካምና መጥፎ ሚስቶች፡- የኖህንና የሎጥን ሚስቶች ምሳሌነት አስታውሱ፡፡ እነሱም ከፃድቃን ባሪያዎች ጋር ተጋብተው ነበር ነገር ግን አታለሏቸው፡፡ ሁለቱም በሲዖል እሳት ውስጥ ገብተዋል፡፡ በሌላ በኩል ግን የፈርዖን ሚስት ክፋትን ከሚያደርጉት ተጠብቃለች ተለውጣለችም፡፡ የኢምራን ልጅም ማርያም ንፅህናዋን የጠበቀች ነበረች፡፡ አላህም በማርያም ውስጥ እስትንፋሱን ነፋባት እሷም እውነቱን መስክራለች 66.10-12፡፡

ሎጥ፡- ሎጥ ግብረ ሰዶማዊነትን እንደ ብልግናና ድንቁርና አውግዞት ነበር፡፡ አላህም የሎጥን ሚስት ከኋላ እንድትቆይ አደረጋት ነገር ግን ሎጥና ጎሳዎቹ በከተማዋ ላይ አላህ ፍርድን ከማዝነቡ በፊት አመለጡ 27.54-57፣ 26፣160-175፡፡ ሰዶምንም የሸክላ ድንጋዮች ዝናብ አጠፋት 51.33፡፡

ዮናስ፡- ዮናስ የአላህ መልክተኛ ነበር፡፡ እሱም በጣም ከባድ ጭነት ባላት መርከብ ኮበለለ፡፡ እሱም ከወታደሮቹ ጋር ዕጣን ተጣጣለ እናም ከጠፉት መካከል አንዱ ሆነ፡፡ ከዚያም አሳ እሱን ዋጠው ምክንያቱም አንድ ስህተትን ስለሰራ ነበር፡፡ እሱም አላህን ከማያመልኩት መካከል አንዱ ቢሆን ኖሮ በዓሳው ሆድ ውስጥ እስከ ፍርድ ቀን ድረስ በቆየ ነበር፡፡ አላህም በባህር ዳር ላይ እሱን ጣለው፡፡ እሱም ታምሞ ነበር፡፡ አላህም የቅልን ዛፍ በእሱ ላይ እንድታድግ አደረገ፡፡ ዮናስም ወደ አንድ መቶ ሃያ ሺ ሰዎች ወይንም ከዚያ ለሚበልጡ ሰዎች ዘንድ ተላከ እነሱም ስላመኑ አላህ ለተወሰነ ጊዜ ደስታን ሰጣቸው 37.139-148፡፡

ኢዮብ ሚስቱን ደበደባት፡- ሰይጣን ኢዮብን ካጠቃው በኋላ ምድሩን በእግሩ እንዲመታ አላህ ነገረውና ሕመሙን የሚያስታግስ የውሃ ምንጭ ወጣለት፡፡ የእሱም ህብረት እንደገና ታደሰለት፡፡ አላህም የዛፍ ቅርንጫፍን ተጠቅሞ መሐላውን እንደሚያሟላለት ነገረው፡፡ (የሙስሊም ባህል እንደሚናገረው ይህ መሐላ የተደረገው ሚስቱን እንዲደበድብ ነው፣ ነገር ግን ኢዮብ ሚስቱን ለመደብደብ ስለተጠቀመበት ነገር የተለያየ ነገርን ይናገራሉ አንዳንዶች ‹ጭፍግ ቀንበጦች› አንዳንዶች ‹አረንጓዴ ሳር› ወይንም ‹አረንጓዴ ቅርንጫፍ› ይላሉ) 37.41-44፡፡

የወጣቱ አብርሃም ውሸት፡- አብርሃም ገና ወጣት እያለ የሕዝቡን ጣዖታት አንድ ዋናው ብቻ ሲቀር በሙሉ አጠፋቸው፡፡ እሱም ከዚያ በኋላ ለሕዝቡ በውሸት እንዲህ አላቸው ሌሎቹን ጣዖታት ያጠፋቸው ዋናው ጣዖት ነው በማለት በውሸት ነገራቸው 21.58-63፡፡

አብርሃም እስማኤልና ይስሐቅ፡- አብርሃም ቅዱስና ነቢይ ነበረ፡፡ እሱም ጣዖታትን አስመልክቶ ከአባቱ ጋር ይከራከር ነበር ይህም አባቱ በድንጋይ እንደሚወግረውና ቤቱን ለቅቆ እንዲወጣ እስከሚዝትበት ድረስ ነበር፡፡ አብርሃምም ሕዝቡንና ጣዖቶቻቸውን አልቀበል ባለ ጊዜ እያንዳንዳቸው ታዋቂ ነቢያት የነበሩትን ይስሐቅንና ያዕቆብን ተሰጠው 19.41-50፡፡ አብርሃምም ልጁን እንደሚሰዋ ሕልምን አለመ (ስሙ አልተጠቀሰም)፡፡ ልጁም ስለዚህ ሕልም ተነግሮት አባቱ ሕልሙን መፈፀም እንዳለበት አበረታታው፡፡ አብርሃምም ልጁን ፊቱን ወደ ምድር ደፋው፡፡ ልጁም በመጨረሻው ሠዓት ዳነ ከዚያም ለእሱ መስዋዕት ምትክ ተላከለት፡፡ ያም አብርሃም የተባረከበት ፈተና ነበረ፡፡ ይስሐቅም ለአብርሃም ተሰጠ ይስሐቅም ቅዱስ ነቢይ ተደረገ 37.83-113፡፡

እስማኤል፡- እስማኤልም ደግሞ መልእክተኛ ነበረ፣ ነቢይም ታማኝም ሰው ነበረ፡፡ እሱም ሰዎች ምፅዋትን እንዲሰጡና መፀለይም እንዳለባቸው ሰበከ፡፡ አላህም በእሱ በጣም ተደስቶ ነበር 19.54-55፡፡

እስማኤልና አብርሃም ካባን አዘጋጁ፡- አላህ ካባን ሰራና በመካም ለሙስሊሞች የማምለኪያ ቦታ እንዲሆን እስማኤልንና አብርሃምን እንዲቀድሱት አዘዛቸው፡፡ እሱም (ካባ) በዙሪያው ለሚዞሩት ሰዎች፣ ተንበርክከውና በፊታቸው ተደፍተው ለሚፀልዩት ሰዎች ቅዱስ ሆኖ መጠበቅ ነበረበት፡፡ እነሱም ለሕዝቡ መገለጥን የሚያመጣና ለሕዝቡ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያስተምር የአረብን ነቢይ አላህ እንዲልክ ፀለዩ 2.125-131፡፡

ትንሳኤን አብርሃም ፈተነ፡- ስለሙታን ትንሳዔ ማስረጃ እንዲሰጠው አብርሃም አላህን ጠየቀው፡፡ አላህም አብርሃም አራት ወፎችን እንዲቆራርጥና በተራራዎች አናት ላይ እንዲበታትናቸው ነገረው፡፡ እሱም ከዚያ በኋላ ይጠራቸውና እነሱም ወደ እሱ እንደገና በርረው ይመጣሉ 2.260፡፡

አብርሃም መካን ስርዓት መስርቷል፡- አላህ ለአብርሃም እንደ አምልኮ ቦታ መካን በመዞር እንዲመሰርታትና ፀሎትም ሃጂም እንዲደረግባት አዘዘው 22.26-29፡፡

የመጀመሪያው ቤተመቅደስ፡- ለሰው ልጅ ሁሉ የመጀመሪያው ቤተመቅደስ ሆኖ የተመደውና የተገነባው በመካ ነው፡፡ ለሚችሉ ሁሉ ይህንን ቦታ መጎብኘት በአላህ የታዘዘ ነገር ነው 3.96፣97፡፡

እስራኤል ለመጽሐፍ ቅዱስ ያላት ክብር፡- የአዳም የኖህ የአብርሃም እና የእስራኤል  (ማለትም) የተመረጠው የዘር ሐረግ ሕዝብ አላህ ቃሉንና ምልክትን በሚገልጥላቸው ጊዜ በፊታቸው ወድቀው እና በእንባ ሆነው የሚያመልኩት ናቸው 19.58፡፡

ዮሴፍ፡-  የዮሴፍ ወንድሞች ወደ ባርነት በሸጡት ጊዜ ለያዕቆብ የነገሩት ዮሴፍ ሞተ ብለው ነበር፡፡ ያዕቆብ ግን አላመናቸውም ነበር፡፡ ዮሴፍም ወደ ግብፅ ሄዶ የአዚዝ ባሪያ ሆነ፡፡ የአዚዝም ሚስት ዮሴፍን ልታባልገው ሞከረች፡፡ በሩን ቆለፈችና እሱን ለማባበል ሞከረች እሱም በተዓምራት ለእሷ ፈተና ከመስጠት ተጠበቀ፡፡ እሱም ወደ በሩ እየሮጠ እያለ ከበስተኋላው ሸሚዙን ቀደደችውና ለባለቤቷና ለማህበረሰቡ ማስረጃ አድርጋ በማቅረብ እንዲከሰስ አደረገች፡፡ ለአካባቢው ሴቶች ሐሜትም ምላሽ የጌታው ሚስት ለከተማው ሴቶች ግብዣን አዘጋጀችና ለእያንዳንዱ ቢለዋን ሰጠቻቸው፡፡ እነሱም ዮሴፍን ባዩት ጊዜ እሱ በጣም ቆንጆ ስለነበረ እጆቻቸውን ቆረጡና  እሱ ሟች አይደለም መልአክ ነው በማለት አወጁ፡፡ የጌታውም ሚስት እሱ ከእሷ ጋር የግብረ ስጋ ግንኙነትን ካላደረገ በስተቀር እጅግ ክፉ የሆኑ ወንጀለኞች በታሰሩበት እስር ቤት ውስጥ እንዲታሰር እንደምታደርግ ገለጠች፡፡ ዮሴፍም ይህንን በሰማበት ጊዜ ከእነሱ አሳሳች ፈተና እና ከራሱም የወጣትነት የዝሙት ምኞት እንዲጠበቅ ፀለየ፡፡ እሱንም ከሴቶቹና ከራሱም የምኞት ስሜት ለመጠበቅ ግብፃውያን ዮሴፍን በእስር ቤት ውስጥ አስቀመጡት፡፡ በእስር ቤትም ውስጥ እያለ ዮሴፍ ከእስር ቤት ጓደኞቹ አንዱ እንደሚገደል ትንቢትን ተናገረ፡፡ ፈርዖንም እሱን በስቅላት ገደለው፡፡ የሴፍም ከቤተሰቦቹ ጋር በተቀላቀለበት ጊዜ እንደመቀላቀያው አንድ ክፍል የያቆብን እውርነት ፈወሰው፡፡ ይህም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ካለው የዮሴፍ ታሪክ ጋር ይስማማል እንዲሁም ያረጋግጠዋል 12.1-111፡፡

ሙሴ፡- ሙሴ ከወንድሙ ከአሮን ጋር የተመረጠ መልእክተኛና ነቢይ ነበር፡፡ አላህም እሱን ከተራራው ቀኝ በኩል ጠራውና ከራሱ ጋር ቀጥታ ንግግርን እንዲያደርግ ወደራሱ አስጠጋው 19.51-53፡፡ ከጡዋ ሸለቆ ተጠርቶ ወደ ፈርዖን ዘንድ ተላከ፡፡ እሱም ታላቅን ተዓምራት አሳየ ነገር ግን የፈርዖንን ዓመፀኝነት ተግባር እልለወጠውም ይህም ፈርዖን እንዲቀጣ አደረገው 79.15-25፡፡ የግብፃውያንም ልብ እስኪቀጡ ድረስ በጣም እንዲጠነክር ሙሴ ፀለየ አላህም ፀሎቱን ተቀበለው፡፡ እስራኤላውያንም በባህሩ ውስጥ እንዲሻገሩ ተመሩ የግብፃውያንም ሰራዊት ሰጠሙ ይህም ነገር ፈርኦንን ወደ እስልምና እንዲቀየር አደረገው፡፡ እስራኤላውያንም በተሰጣቸው ውብ አገር ውስጥ አረፉ፡፡ እነሱም መገለጥ ተሰጥቷቸው ነበር ነገር ግን ወደ ልዩ-ልዩ ቡድን ተከፋፈሉ 10.75-93፡፡

የሚቃጠለው ቁጥቋጦ የተለያዩ ዘገባዎች፡- (ሙሴን በተመለከተ የተቃረኑ ታሪካዊ ዘገባዎች ይገኛሉ እነዚህም ያሉት በ28.1-43፣ 27.7-14፣ 26.9-56፣ 20.9-97፣ 7. 103-156 ሲሆኑ እዚህ የተቀመጡት መሐመድ ባስታወሳቸው በግምታዊ ቅደም ተከተላቸው ነው፡፡ አንዱም የዚህ ምሳሌ ያለው ሙሴ በሚቃጠለው ቁጥቋጦ ዘንድ ካደረገው ነገር ጋር የተያያዘ ነው)፡፡

1. አላህ ከቁጥቋጦው ውስጥ በሸለቆው በስተቀኝ በኩል ሙሴን ጠራው እና እንደዚህ አለው፡- ‹ኦ ሙሳ በእርግጥ እኔ አላህ ነኝ፣ የዓለማት ጌታ፡፡ የያዝከውን በትር ጣለው‹ 28.30-31፡፡

2. ሙሴ የሚቃጠለው ቁጥቋጦ ጋ በቀረበበት ጊዜ የሚከተለውን ድምፅን ሰማ ‹በእሳቲቱ ያለው ሰውና በዙሪያዋ ያሉም ሁሉ ተባረኩ የዓለማትም ጌታ አላህ ጥራት ይገባው፣ ሙሳ ሆይ እነሆ እኔ አሸናፊው ጥበበኛው አላህ ነኝ፣ በትርህንም ጣል (ተባለ ጣለም)›፡፡ 27.7-10፡፡

3. ድምፁም እንዲህ አለ፡ ‹በመጣትም ጊዜ ሙሳ ሆይ በማለት ተጠራ እኔ ጌታህ እኔ ነኝ መጫሚያዎችህንም አውልቅ አንተ በተቀደሰው ሸለቆ በጡዋ ነህና፣ እኔም መረጥኩህ የሚወረድልህንም ነገር አዳምጥ፤ እኔ አላህ እኔ ነኝ ያለ እኔ አምላክ የለምና ተገዛኝ ሶላትንም (በርሷ) እኔን ለማውሳት ስገድ፡፡ ሰዓቲቱ በእርግጥ መጪ ናት ልደብቃት እቃረባለሁ ነፍስ ሁሉ በምትሠራው ነገር ትመነዳ ዘንድ (መጭ ናት) በርሷ የማያምነውና ዝንባሌውን የተከተለውም ሰው ከርሷ አያግድህ ትጠፋለህና፡፡ ሙሳ ሆይ! ይህችም በቀኝ እጅህ ያለችው ምንድን ናት? (ተባለ)፡ እርሷ በትሬ ናት በርሷ ላይ እደገፍባታላሁ በርሷም ለፍየሎቼ ቅጠልን አረግፍባታለሁ ለኔም በርሷ ሌሎች ጉዳዮች አሉኝ አለ፡፡ (አላህም) ሙሳ ሆይ! ጣላት አለው›፡፡ 20.11-17፡፡

የሙሴ አስተማሪ፡- ሙሴ ሁለቱ ባህሮች ወደሚጋጠሙበት ቦታ ለመሄድ ወሰነ፡፡ እሱና ጠባቂው ብዙ ከተጓዙ በኋላ ለመመገብ አረፉ፤ ጠባቂውም በጣም አዝኖ ነበር በከፊል የበሉት አሳ በተዓምራት ወደ ባህር አምልጦ ነበርና፡፡ ከጉዟቸውም ሲመለሱ ከድር ከሚባል አንድ አስተማሪ ጋር ተገናኙ፡፡ ሙሴም ከእርሱ ለመማር ከድርን ለመከተል ጥያቄን አቀረበ ከድርም ሙሴ ምንም ጥያቄን የማይጠይቅ ከሆነ ሊከተለው እንደሚችል ነገረው፡፡ ሙሴም በነገሩ ተስማማ፡፡ በመርከብ ሲጓዙም አስተማሪው መርከቢቱን ሰርስሮ ቀደዳት ሙሴ የተባለውን እረስቶ አጉረመረመ፡፡ ቆይቶም አስተማሪው ወጣቱን ሰው ገደለው፡፡ ሙሴም ንፁህ ሰውን ስለመግደሉ ጥያቄን አቀረበ፡፡ አስተማሪውም እነሱን አናስተናግድም ባሉ ከተማዎች ላይ ግድግዳን አደረገባቸው፣ አስተማሪውም ለሰራው ስራ ክፍያን ባልጠየቀም ጊዜ ሙሴ እንደገና እረስቶ ጥያቄን ጠየቀው፡፡ በመጨረሻም አስተማሪው ታንኳይቱን ያሰጠመው መርከበኞችን ሁሉ የሚገድለውና ከኋላቸው የሚከተላቸው ንጉስ እንዳይገድላቸውና እንዳይቀማቸው ለማስነወር ነው አለ፡፡ ወጣቱን ልጅ የገደለውም ወላጆቹ የእምነት ሰዎች ስለነበሩ ልጁ ወላጆቹን በዓመፅና ባለመታዘዝ ያሳዝናል ብሎ ስለፈራና በምትኩ ሌላ የሚታዘዝ እንዲያገኙ ተመኝቶ እንደሆነ ገለጠ፡፡ ግድግዳውም የድሃ አደጎች ልጆች ንብረት ነው በስሩም አባታቸው የቀበረው ንብረት አለው ለአካለ መጠን ሲደርሱ የሚያወጡት ነው አለ፤ 18.60-82፡፡

የፈርዖን አስማተኞች መለወጥ፡- (የታሪኩ አንደኛው አቀራረብ) ሙሴ (ከአስማተኞቹ ጋር) ውድድሩን ጀመረ፡፡ እሱም አስማተኞቹን መጎናፀፊያቸውንና በትሮቻቸውን እንዲጥሉ ጠየቃቸው፡፡ አስማተኞቹም ነገሮቻቸውን በጣሉ ጊዜ እንደሚያሸንፉ እርግጠኞች ነበሩ፣ ነገር ግን ሙሴ የእሱን ነገር በጣለ ጊዜ የእነሱን የማታለል ነገር ሁሉ ዋጣቸው፡፡ በምላሹም አስማተኞቹ በምድር ወድቀውና በፊታቸው ተደፍተው አመለኩና እንዲህ አሉ፡- ‹በዓለማት ጌታ አመንን በሙሳና በሃሩን ጌታ› 26.43-49፡፡ (የታሪኩ ሁለተኛው አቀራረብ) አስማተኞቹ ውድድሩን ሙሴ በመጀመሪያ እሱ እንዲጀምር በመጠየቅ ጀመሩ፡፡ ሙሴም የመለሰው ‹አይደለም ጣሉ› አላቸው፣ ስለዚህም እነሱ አስማታቸውን አደረጉ አስማታቸውም ሙሴን አስፈራው፡፡ አላህም ማበረታቻን መልክት ተናገረው፡፡ (ይህም ማለት ሙሴ አሸናፊ መሆኑን ነው)፡፡ ከውድድሩም በኋላ አስማተኞቹ እንዲህ አሉ፡- ‹በሃሩንና በሙሳ ጌታ አመንን አሉ› 20.65-71 በዚህም ጊዜ ፈርዖን እጅና እግሮቻቸውን ግራና ቀኝ በማፈራረቅ ቆርጦ (ግራ እግር ቀኝ እጅ በማድረግ) በዘምባባ ግንድ ላይ ሰቀላቸው፡፡

የሰማርያ ሰዎች የወርቁን ጥጃ ገነቡት፡- ሙሴ ጌታውን በተራራው ላይ በተገናኘ ጊዜ፤ በችኮላ ላይ ነበር ምክንያቱም አይሁዶች እሱን ለመከተል እየሞከሩ ነበር፡፡ ሙሴም በአላህ የተነገረው ነገር ከእነሱ ተወስዶ ባለበት ጊዜ አላህ አይሁዶችን መፈተን ነበረበት፣ ስለዚህም እነሱ እምቧዋ የሚል ድምፅን የሚያሰማ የወርቅን ጥጃ ሰርተው እንደሆነ ለማየት በጣም ተቻኩሎ ነበር፡፡ ሙሴም እነሱን በወቀሳቸው ጊዜ እነሱ ንፁሃን መሆናቸውን ተናገሩ፡፡ እነሱም ያደረጉት ነገር ሰማርያኖች ያዘዟቸውን ነገር ብቻ ነበር፡፡ ጣዖቱንም የገነቡት ሰማርያኖች ነበሩ፡፡ ሙሴም እነሱን በጣም ቀጥቷቸዋል 20.83-97፡፡

ዳዊት፡- ዳዊት የምኞት ኃጢአቱን ተናዘዘ ይህም ሁለት ሰዎች ስለ ክርክራቸው በጠየቁት ጊዜ ነበር እነሱም አንደኛው ዘጠና ዘጠኝ በጎች ያሉት ሁለተኛው አንድ በግ ያለው ነበሩ፡፡ የመጀመሪያውም የባለ አንድ በጉን ሰው በግ ወሰደበት፡፡ ዳዊትም ይህ ለእሱ ፈተና እንደሆነ ተገነዘበ እና ኃጢአቱንና ምኞቱን ተናዘዘ (ዝርዝሮቹ ግን አልተሰጡም) እሱም ይቅር ተባለ 38.17-26፡፡

መላእክት የተሸከሙት ታቦት፡- ሳዖል ንጉስ ሆኖ ይገዛ በነበረበት ጊዜ አንድ ነቢይ የታቦቱን (የአማርኛው ቁርአን ሳጥኑን ይላል) መምጣት አወጀ፡፡ በውስጡም ከሙሴና ከአሮን ቤት ውስጥ የነበረ ቅርፅ ነበረበት፡፡ መላእክት ተሸክመውት ነበር፡፡ ከዚያም በኋላ ዳዊት ጎልያድን ገደለው 2.247-253፡፡

ሰሎሞን፡- ሰለሞን ከእንስሳት ጋር መነጋገር ይችል ነበር፡፡ እሱም የጅኒዎችን፣ የሰዎችን የአዕዋፍን ሰራዊት ሰብስቦ ለጦርነት አስታጠቃቸው፡፡ ወደ ጉንዳኖችም ሸለቆ መጡ አንዲትም ጉንዳን እህቷ ከጥፋት እንድትድን ወደ ጉድጓድ ውስጥ እንድትሄድ ተናገረች፡፡ ሰለሞንም ሰማትና ፈገግ አለ እሱንም ስለባረከው አላህንም አመሰገነ፡፡ እሱም የአእዋፍ ሰራዊቱን ሲመረምር አንድ ወገን (ሁድሁድ) ጎድሎ አገኘ፤ እናም ከባድ የሆነውን ቁጣውን ገለጠ፡፡ እነሱንም በሞት እንደሚቀጣቸው ሲናገር እነርሱ ግን ዜና ይዘው መጡ፡፡ ወፎቹም ከሳባ ስለሆነች ፀሐይን ስለምታመልክ አንዲት አስደናቂ ሴት ለሰለሞን ነገሩት፡፡ ሰሎሞንም በወፎቹ ወደ እሷ ወደ ሳባ ንግስት መልክትን ላከ (ያም የጀመረው በሙስሊሞች የአምልኮ ገለጣ ነው) የሚለውም ‹በአላህ ስም እጅግ በጣም ርኅሩህ በጣም አዛኝ በኾነው›፡፡ በመልክቱም ውስጥ ሰለሞን ንግስቲቱ እንድትጎበኘው ጥያቄን ያቀርባል፡፡ እሷም የወርቅን ስጦታ ላከችለት ሰለሞንም ለአምባሳደሮቿ ወደ ሳባ እንዲመለሱና የእሱ ጦር እነሱን እንደሚያጠቃ ስደተኞች እንደሚያደርጋቸውና ወደ ሙሉ ውርደት ውስጥ እንደሚጥላቸው መልእክትን ላከባቸው፡፡ በምላሹም ንግስቲቱ ሰለሞንን ለመጎብኘት ጉዞዋን ጀመረች፡፡ እሷም በጉዞዋን ላይ እንዳለች በቅዱስ መጽሐፍ በጣም ብዙ እውቀት ያለው አንድ ሰው በተዓምር መንገድ የእሷን ዘውድ ወደ ሰለሞን አደባባይ አመጣው (የአማርኛው ዙፋኗን ነው የሚለው)፡፡ እሱንም እንዲያሳስታት አድርገው የእሷ እንደሆነ እንዲጠይቋት ካወቀችው ጠቢብ የመሆኗ እና ካላወቀችው ከማያውቁት እንደሆነች መለያ እንዲሆን አደረጉ፡፡ እሷም ወደ አደባባዩ በረገጠች ጊዜ ቀሚሷን ከፍ አደረገች ይህንም ያደረገችው የሚያንፀባርቀው ወለል ውሃ መስሏት ነው፡፡  እሷም ቁርጭምጭሚቷን በመግለጧ አሰቃቂ ኃጢአትን ፈፅሜያለሁ በማለት በጣም አዘነች ይህም እሷ አላህን እንድታመልክ አደረጋት 27.15-44፡፡ 

ሰለሞን ፈረሱን ገደለ፡- አንድ ምሽት ላይ ሰለሞን በጣም ለሰለጠነው ፈረሱ ያለው ፍቅር በፀሎቱ ውስጥ ጣልቃ እየገባ እንደሆነ አስተዋለ፡፡ እሱም ንስሐ ገባና እጅግ በጣም በተመረጡት ፈረሶች መካከል ገብቶ እግራቸውንና አንገታቸው ቆረጠው 38.30-33፡፡

(የአዘጋጁ ልዩ ማሳሰቢያ፡- ቁራን 38.33 በተመለከተ ያሉት ትርጉሞች የተለያዩ ናቸው፡፡ የአማርኛው ቁርአን ‹በኔ ላይ መልሷት (አለ) አጋዶችዋንና አንገቶችዋን ማበስ ያዘ› ይላል፡፡ ይህ ትርጉም በቀጥታ የሚመሳሰለው ከ Ahmed Raza Khan: Mohammed Aqib Qadri: እና ከ  Yusuf Ali: ትርጉሞች ጋር ነው፡፡ በሁለቱም ትርጉሞች ቁርአን ሰለሞንን ያስቀመጠው የፈረሶቹን እግርና አንገትን እንደአባበሰ ሲሆን በ Pickthal: ትርጉም መሠረት ግን ሰለሞን የፈረሶቹ ፍቅር በፀሎት ጊዜው ጣልቃ እየገባ ስላስቸገረው ንስሐ ግብቶ እግራቸውንና አንገታቸውን እንደቆረጠው ነው፡፡ ከአጠቃላይ የክፍሉ ዓውድ ጋር ሲታይ ትክክል የሚሆነውና ስሜት የሚሰጠው የፒክታል ትርጉም ሲሆን ሌሎቹ ሁለት ትርጉሞች የአማርኛውን ጨምሮ ለመቀበል አስቸጋሪዎች ናቸው፡፡ እንደዚህ ዓይነት የትርጉም ልዩነቶች በተለያዩ የእንግሊዝኛ ቁርአን ትርጉሞች ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ሰዎች ሁሉ እውነቱን ያውቁ ዘንድ እነዚህን የትርጉም ልዩነቶች በዚህ ድረ ገፅ ላይ በሚቀርቡ ጽሑፎችና እንዲሁም እራሳቸውን በቻሉ ዝግጅቶች የዚህ ገፅ አዘጋጆች በተከታታይ ያቀርባሉ፡፡)

ሰለሞን የሞተውን አካል መለሰ፡- አላህ በሰለሞን ዙፋን ላይ የሞተን አካል አስቀመጠ እሱም ንስሐን እስኪገባ ድረስ በዙፋኑ ላይ ቆየ 38.34-35፡፡

ሰለሞን ነፋሳትንና ጅኒዎችን አዘዘ፡- ሰለሞን ነፋሳትን ወደፈለገው አቅጣጫ እንዲነፍሱና ወደ ፈለገው ቦታ እንዲሄዱ እንዲያዝ ተፈቅዶለት ነበር፡፡ እንዲሁም ደግሞ ግንብ የሚገነቡትንና ወደ ጥልቅ የሚሰጥሙትንም ጅኒዎች ጭምር ያዛቸው ነበር፡፡ አንዳንዶቹም በሰንሰለት ውስጥ ነበሩ 38.36-40፣ 21.82፡፡

ሰለሞንና ጂኒዎች፡- አላህ ለሰለሞን የቀለጠ የነሐስ ምንጭና ለሰለሞንም የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ በፊቱ እንዲያደርጉ የጅኒዎችን ባሪያዎች ሰጠው፡፡ እነሱም ምኩራቦችን ምስሎችን ትላልቅ ገንዳዎችን ሰሩለት፡፡ ከእነሱም ወደ እረፍት ቢመለሱ አላህ በነዲድ እሳት ቅጣትን ይቀጣቸዋል፡፡ ሰለሞንም ከሞተ በኋላ እንኳን ጅኒዎች እሱን ማገልገላቸውን ቀጥለው ነበር፡፡ የእነሱም አገልግሎት ማብቃት እውነታ ከእነሱ ተሰውሮባቸው ነበር ምክንያቱም እሬሳው አልወደቀም ነበርና፡፡ ይህንን እውነታ የተረዱት የሰለሞንን በትር ምስጥ ስትበላና እሬሳው ሲወድቅ ነበር 34.12-14፡፡

ማርያምና ዘካርያስ፡- የማርያም እናት የኢምራን ሚስት ልጇ ገና በእናቷ ማህፀን ውስጥ እያለች ለአላህ ሰጥታት ነበር፡፡ ማርያምም ከተወለደች በኋላ በዘካርያስ ቁጥጥር (ጥበቃ) ስር ሆና በቤተመቅደስ ውስጥ ኖረች፡፡ ዘካርያስም በቤተመቅደስ ውስጥ በጎበኛት ጊዜ ሁሉ ያየው ነገር እርሷ የምትበላው ነገር የነበራት መሆኑን ነው፡፡ እሱም ከየት እንደመጣ ለማወቅ ፈለገ፡፡ ማርያምም ከአላህ እንደመጣላት ነገረችው 3.36፣37፡፡

ዘካርያስ የመጥምቁ ዮሐንስ አባት፡- ዘካርያስም በእርጅናው ወንድ ልጅን እንዲሰጠው ለመነ፡፡ ስለፀሎቱም መልስ መጣለት ወንድ ልጅ እንደሚኖረውና ከዚህ በፊት ማንም ሰው ሰጥቶት የማያውቀውን ስም እንደሚሰጠው እሱም ‹ዮሐንስ› እንደሚባል ነው፡፡ ዘካርያስም ጥያቄን ስለጠየቀ ለሦስት ቀናትና ለሦስት ሌሊት ድዳ ሆኖ ቆየ 19.1-15፣ 3.38-41፡፡

መጥምቁ ዮሐንስ፡- ዮሐንስ ቅዱስ መጻሕፍትን (ብሉይ ኪዳንን) እንዲወድና እንዲጠብቅ ታዝዞ ነበር፡፡ እሱም ጥበብ፣ ርህራሄ እና ንፅሕና ከሕፃንነቱ ጀምሮ ተሰጥቶት ነበር፡፡ እሱም ፃድቅና ትሁት ሰው ሆኖ እናቱንና አባቱንም የሚያከብር እና የሚታዘዝ ሆኖ አደገ 19.12-15፡፡

የማርያም የመጀመሪያ ታሪክ፡- (ማርያም እንዴት እራሷን እንዳገለለች የሚናገሩ ትውፊቶች እርስ በእርስ ይለያያሉ)፡፡ ማርያምም መጋረጃን አድርጋለች ወይንም ብቻዋን ወደ ምስራቅ ተጉዛለች፡፡ በዚህም የብቸኝነት ቦታ ላይ ወደ እርሷ በሁሉም ነገር እንደሰው ሆኖ መንፈስ ቀረባት፡፡ ማርያምም ፈርታ ነበር እሱም እሷ ቅዱስ ልጅ እንደምትወልድ ሊነግራት መልእክተኛ እንደሆነ ተናገረ፡፡ እሷም ድንግል ስለነበረች ይህ እንዴት ሊሆን እንደሚችል ተደነቀች፡፡ እሱም ልጁ ለሰዎች ሁሉ የሆነ መገለጥና ከአላህ ዘንድ ምህረት መሆኑን ተናገረ፡፡ ልጁንም ለመፅነስ እሷ ወደ ሩቅ ስፍራ ሄደች፡፡ ምጥም በጀመራት ጊዜ እሷ ከዘንባባ ዛፍ ስር ተኝታ ነበር፡፡ ሕመሙ በጣም አሰቃቂ ነበርና ማርያም ይህ ከመሆኑ በፊት በሞትኩ ኖሮ የተረሳም ነገር በሆንኩ ኖሮ በማለት ተናገረች፡፡ ድምፅም እርሷን በመልካም ዜና አፅናናት እንድትጠጣው ወንዝ በአጠገቧ እንደሚያልፍ እንዲሁም ደግሞ የዘንባባውን ዛፍ ብትወዘውዘው ተምር እንደሚረግፍላት ተናገራት፡፡ እሷም ለሌሎች በምንም ንግግር እንዳትናገር ‹እኔ እየፆምኩ ነው መናገርም አልችልም› እንድትል ታዘዘች፡፡ ልጁንም ወደ ከተማዋ ስትወስደው ሕዝቦቹ እንዲህ አሉ፡- ‹የአሮን እህት አባትሽ ከጋለሞታዎች ጋር አላመነዘረም እናትሽም ጋለሞታ አልነበረችም› እነሱም የጠረጠሩት እርሷ ዲቃላን ወልዳለች ብለው ነበር፡፡ ስትመልስም ወደ ልጁ አመለከተች እሱም ከአንቀልባው ላይ ከጀርባዋ ሆኖ ተናገረና እሱ የአላህ ነቢይም እንደሆነ ገለጠ፡፡ ይህ የማርያም ልጅ የኢየሱስ አወላለድ ታሪክ ነው፡፡ እሱ የአላህ ልጅ አልነበረም አላህ ልጅ ስለማይወልድ፡፡ አላህ ማርያም ወንድ ልጅ እንዲኖራት ብቻ ፈቀደ እሷም ፀነሰች 19.16-35፡፡  

የማርያም የሁለተኛው ታሪክ፡- መልአክም ወደ ማርያም ቀረበ፡፡ እሱም በምድር ላይ ካሉት ሴቶች ሁሉ እሷ እንደ ልዩ ሆና እንደተመረጠች ተናገረ፡፡ እሱም እሷ ማምለክ እንዳለባት ተናገረ፡፡ መልአኩም ስለ ልጁ ብዙ ነገሮችን ተናገረ፡፡ እሱም ገና ልጅ እያለ ለአይሁዶች ልክ እንደአዋቂ ይናራል፡፡ የእሷ ልጅ ፃድቅ ይሆናል፡፡ እሱም ከአላህ የመጣ ቃል ይሆናል ስሙም ክርስቶስ (መሲህ) ኢየሱስ የማርያም ልጅ ይሆናል፡፡ እሱም በዕድሜውና ለዘላለምም የተከበረ ይሆናል፡፡ ኢየሱስም በገነት ውስጥ አላህን ከሚቀርቡት መካከል አንዱ ይሆናል፡፡ እሱም መጽሐፍ ቅዱስን ቶራህን እና ወንጌልን ይማራል፡፡ እሱም ለአይሁዶች ሐዋርያ ይሆናል በአላህም ፈቃድ በሆነ ተዓምራት፣ ይህም ከሸክላ ሕይወት ያላትን ወፍን መፍጠርን፣ እውሮች ሆነው የተወለዱትን እና ለምፃሞችን መፈወስን፣ እንዲሁም ሙታንን ማስነሳትን ጭምር ነው፡፡ እሱም ቶራህን ያውጃል አይሁዶችንም ከዚህ በፊት ሕገ ወጥ የነበሩትን ነገሮች እንዲያደርጉ ይፈቅዳል 3.42-50፡፡

ኢየሱስ እንደ አዳም ነው፡- ኢየሱስ ከአፈር እንደተፈጠረው እንደ አዳም ነው፡፡ አላህም እንደዚያ እንዲሆን አዘዘው እሱም ኖረ 3.59፡፡

ማርያምን ለመንከባከብ (ለመጠበቅ) ሰዎች ተወዳደሩ፡- አንተ መሐመድ ሰዎች ማርያምን ለመጠበቅ ሃላፊነቱን ማን እንደሚወስድ ለመወሰን ብዕሮቻቸውን በመጠቀም ዕጣ ሲጣጣሉ አልነበርክም፡፡ እነሱም ስለ ውድድራቸውም ውጤት ሲከራከሩ አንተ እዚያ አልነበርክም 3.44፡፡

ኢየሱስ ከአንቀልባ ላይ ሆኖ ሰበከ፡- በፍርድ ቀን ከሌሎች ሐዋርያት ጋር የሚሆነውን ኢየሱስን አላህ ይጠይቀዋል፡፡ አላህም ኢየሱስን እንዴት በመንፈስ ቅዱስ ጥንካሬ እንደተሰጠው እና ለሰዎችም ገና እንደታዘለ እንደ አዋቂ ሰው እንደተናገረ ያስታውስ እንደሆነ ይጠይቀዋል 5.110፡፡

ኢየሱስ ሕይወት ያለውን ወፍ ከሸክላ ፈጠረ፡- በፍርድ ቀን ከሌሎች ሐዋርያት ጋር የሚሆነውን ኢየሱስን አላህ ይጠይቀዋል፡፡ በአላህ እንደታዘዘ በመጽሐፍ ቅዱስ እና በጥበብ እናም በአላህ ፈቃድም ወፍን ከሸክላ እንደሰራና እስትንፋስን እንዳደረገባት ያስታውስ እንደሆነ ይጠየቃል 5.110፡፡

ኢየሱስ ከሰማይ ገበታን ይሰጣል፡- በፍርድ ቀን አላህ ኢየሱስን ይጠይቀዋል፡፡ እሱም ከሌሎቹ ሐዋርያት መካከል ይሆናል፡፡ እሱም በአላህ ፈቃድ እውር ሆኖ የተወለደውን እንዴት እንደፈወሰው፣ ለምፃሙንም እንዴት እንዳነፃው እና ሙታንንም እንዴት እንዳነሳቸው ያስታውስ እንደሆነ ይጠየቃል፡፡ ኢየሱስም ከሰማይ ለተከታዮቹ ምግብ ያለበትን ገበታ እንዲጠራ እንዴት እንደተፈቀደለት የሚናገረውም ታሪክ እንደዚሁ ይነገራል 5.110-115፡፡

ኢየሱስ ትክክል ያልሆነውን ሥላሴ ይክዳል፡- በፍርድ ቀን ከሌሎቹ ሐዋርያት ጋር ያለውን ኢየሱስን አላህ ይጠይቀዋል፡፡ ኢየሱስም የሰው ልጆችን እሱን እና እናቱን ከአላህ ጎን እንዳሉ እንደ ሁለት አማልክት እንዲመለኩ ጠይቆ እንደሆነ ይጠየቃል፡፡ ኢየሱስም ይህንን በጣም አድርጎ ይክደዋል 5.115-117፡፡

 

የአዘጋጁ ማሳሰቢያ፡-

በመግቢያው ላይ እንደተጠቀሰው ይህ ጽሑፍ እጅግ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ሰዎችን ይጠቅሳል፡፡ የተጠቀሱትም በቁርአን ውስጥ በተቀመጡበት ሁኔታ ነው፡፡ በእርግጥ ቁርአን ያስቀመጣቸው ታሪኮች በብዛት መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሱት በጣም የተለዩ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ የሁሉም ታሪክ የቀረበው ከአላህ እንደመጣ ተደርጎ ነው፡፡

የእነዚህን ታሪኮች ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ልዩ የሆኑበት ምክንያት ምንድነው? እውነተኛውንና እርግጠኛውንስ እንዴት ማወቅ ይቻላል? እርግጠኛውን ለማረጋገጥና ለማወቅ የሚፈልግስ ሰው ምንድነው ማድረግ ያለበት? የሚሉት ጥያቄዎች ሊነሱ እና መልስም ሊፈለግላቸው ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም የምናምነው እምነት መሠረት ከሞት በኋላ የሚኖረንን የዘላለም ቦታ የሚወስን ነው፣ ስለዚህም በቀላሉ እና በግዴለሽነት ልንመለከተው አይገባንም፡፡

በዚህ ጽሑፍ ውስጥ የተጠቀሱት አራት መቶ አስራ ሁለት ጥቅሶች የሚናገሩት ታሪክ እውነት መሆንና አለመሆን ሊያሳስበን ይገባል፡፡ የሚያሳስብንም የተነገሩት እውነት አይደሉም፣ እውነት ላለመሆናቸውም ማስረጃ አለኝ በማለት በቅንነትና ለእኛው መንፈሳዊ ጥቅም ሲሉ የሚናገሩ ሰዎች ሲነሱ እና ስህተቱን በማስረጃ ሲጠቁሙን ነው፡፡

እነዚህን አራት መቶ አስራ ሁለት ጥቅሶች በተመለከተ ቁርአንና መጽሐፍ ቅዱስ ማለትም ሁለቱም መጽሐፎች በአንድ ጊዜ ትክክል ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ስለዚህም የግድ አንደኛው ስህተት ሌላኛው ደግሞ እውነት መሆን አለበት፡፡ የትኛው ነው ስህተት? 

ታሪካዊ ነገሮች ከታሪክ ምንጮች፣ ከከርሰ ምድር የምርምር ውጤቶች እና ከሌሎችም ተመሳሳይ ዘገባዎች ሊገናዘቡ ያስፈልጋል፡፡ ቁርአን የተናገራቸው ታሪኮች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ምን ይላሉ? የትኛው ነው የእውነተኛነት ስሜት ያለው? አድካሚ ሊሆን ቢችልም እውነትን ለመረዳትና ለማወቅ መጣር አስፈላጊ ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 8 ላይ 32 ላይ ‹እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል› በማለት ተናግሯል፣ አዎ እውነት ብቻ ነው ነፃነት ወደምናገኝበት እውነተኛ ሕይወት ሊያመጣን የሚችለው፡፡

ስለዚህም የዚህ ድረ-ገፅ አዘጋጆች ለተከበሩ አንባቢዎች የሚያሳስቡት እውነትን ለማወቅ እንድትችሉ መጽሐፍ ቅዱስን በማግኘት እንድታነቡ ነው፡፡ ታሪካዊዎቹን ነገሮች በምታገናዝቡበትም ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስን ጽሑፋዊ ይዘት እንድታስተውሉትም እናሳስባለን፣ ከቁርአን አቀራረብ ጋር ስታስተያዩት ምን ታስተውላላችሁ?

ለዘላለማዊው መንፈሳዊ ሕይወታችሁ ጠቃሚ የሆነውን ይህንን እርምጃ በምትወስዱበትና የጌታን ቃል በምታጠኑበት ጊዜ ታላቁ እግዚአብሔር እውነቱን በማሳየት እንዲረዳችሁ እና ወደ እውነቱ ሁሉ እንዲመራችሁ የሁልጊዜ ፀሎታችን ነው፡፡

 

የትርጉም ምንጭ: Bible Characters in the Qur'an,  Chapter 14 of "A Topical Study of the Qur'an From a Christian Perspective" by M.J Fisher, M.Div

ሙሉ መጽሐፉ በአማርኛ: ርእሳዊ የቁርአን ጥናት በክርስትና አይን ሲመረመር

ለእስልምና መልስ አማርኛ  ዋናው ገጽ