የዓለም ክስተቶች ትንቢት

M. J. Fisher, M.Div

ትርጉምና ቅንብር በአዘጋጁ

 

መግቢያና ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ንፅፅር

መሐመድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነቢይ ነውን? በሙሴ ጊዜ እውነተኛ የሆነውን ነቢይ እውነተኛ ካልሆነው ነቢይ ለይቶ የማወቅ ጉዳይ የአይሁድ ሕዝብ ጥያቄ ነበር፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ መዝግቦ የያዘው መረጃ የሚያሳየው እውነተኛ ነቢይ ስለወደፊት ክስተቶች ትክክለኛ መረጃን እንደሚሰጥ ነው፡፡ የነቢዩም ንግግር የሚታወቀው በቀጥታ ከእግዚአብሔር ዘንድ የመጣ ተደርጎ ነው፣ ይህንን ማስረጃ የምናገኘው ከመጽሐፍ ቅዱስ ዘዳግም 18.21-22 ላይ ነው፡፡ ታዲያ በቁርአን ውስጥ የሚገኝ ትንቢት ይህንን ፈተና ያልፍ ይሆንን?

በዚህ ምዕራፍ ላይ የቁርአንን አንድ ጥቅስ ብቻ በመመልከት ብዙ ጊዜ መውሰዳችን ምናልባትም አስገራሚ ሊመስል ይችል ይሆናል፡፡ የዚህ አንድ ጥቅስ ጠቃሚነት ያለው ብቻውን የቆመ በመሆኑ ነው፡፡ አንድ ሰው ቁርአን እጅግ በጣም ብዙ የሆኑና የተፈፀሙ ትንቢቶችን በመያዙ ከእግዚአብሔር ለመሆኑና ለእርግጠኝነቱ ማስረጃ መሆን አለበት በማለት ሊጠብቅና ሊገምትም ይችል ይሆናል፡፡ ይሁን እንጂ መሠረታዊ በሆነ የቁርአን ጥናት የተገኘው የዓለምን የወደፊት ሁኔታ ሊናገር የሚችል ጥቅስ አንድ ብቻ ነው፡፡ ይህም አንድ ጥቅስ ቁርአን በፍርድ ቀን ስለሚሆነው ነገር ከተናገረው (ከተተነበየው ትንቢት) ውጪ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ቁርአን ስለፍርድ ቀን የሚናገረው ትንቢትም እንኳን ግልፅ ያልሆነና የተምታታ ነው፡፡

ስለዚህም ቁርአን የሚከተለውን ይናገራል

መሸነፍና ድል ማድረግ፡- ‹ሩም ተሸነፈች፡፡ በጣም ቅርብ በሆነችው ምድር፡፡ እነርሱም ከመሸነፋቸው በኋላ በእርግጥ ያሸንፋሉ፡፡ በጥቂት ዓመታትም ውስጥ (ያሸንፋሉ) ትእዛዙ በፊትም በኋላም የአላህ ነው፡፡ በዚያ ቀንም ምእምናን ይደሰታሉ፡፡› 30.2-4፡፡

በቁርአን ውስጥ ትንቢት ሆኖ የተገኘው አንድ ጥቅስ ይህ ብቻ ቢሆንም፣ በጥንቃቄ ሲመረመርም እጅግ በጣም የሚያምታታ ነው፡፡ ትንቢቱም ድል የተደረገ አንድ ጦር ሰራዊት በቅርብ የወደፊት ጊዜያት ውስጥ አንድ ዓይነት ድልን እንደሚያገኝ ይናገራል፡፡ ይህንን ትንቢት በተመለከተ ያሉት አንዳንድ የሙስሊም ትርጉሞች ድል የተደረገው የጦር ሰራዊቱ የሮማውያን ነው ሲሉ፣ ሌሎች ደግሞ የግሪኮች ሰራዊት ነው ይላሉ፡፡ ነገር ግን ሮማውያንን ወይንም ግሮኮችን ጠላት ሆኖ የሚዋጋው ኃይል ማን እንደሆነ ምንም የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ ስለዚህም ሮማውያን ወይንም ግሪኮች በአንድ ባልታወቀ ሁኔታ (በግልፅ ባልታወቀውና ድል ባደረጋቸው የጠላት ጦር ላይ) ቆይተው አሸናፊዎች ሆነው ይገኛሉ፡፡ ይህም ድል አድራጊነት የሚሆነው በጥቂት ዓመታት ውስጥ ነው፡፡ (የእንግሊዝኛው ቁርአን ከሦስት እስከ ዘጠኝ ዓመታት ውስጥ በማለት በምዕራፍ 30.4 መጨረሻ ላይ በቅንፍ አስቀምጦታል፣ ከዚህም በተጨማሪ የእንግሊዝኛው ቁርአን በቁጥር 3 ላይ በቅንፍ ያስቀመጣቸው አገሮች ሶርያ፣ ኢራቅ፣ ጆርዳን፣ እና ፓለስታይን ናቸው እነዚህም የተቀመጡት ሮምን ያሸነፉ አገሮች ሆነው ነው፣ የዚህ ቅንፍ ማብራሪያ በአዘጋጁ የተጨመረ ነው)፡፡ ይሁን እንጂ ትንቢቱ ለረጅም ጊዜ ወይንም ዘመን የሚሆን አልነበረም፡፡ ግልፅ የሆነው ነገር ይህ ክስተት ይሆን የነበረው በራሱ በመሐመድ ጊዜ ውስጥ እንደሚሆን ነበር፡፡

በሌላ ጎኑ ግን መጽሐፍ ቅዱስ ለነቢያትና ለሐዋርያት የተገለጠው በ1‚500 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ነው እሱም ዝርዝርና የተናጠል የሆኑ እጅግ በጣም በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ትንቢቶችን ይዟል፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችም እያንዳንዳቸው ከብዙ መቶ ዓመታትም በኋላ እንኳን ያለምንም ስህተት ተፈፅመው በመገኘታቸው እውነትነታቸው ተረጋግጧል፡፡ የመጀመሪያዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሐፍት የሙሴ ሕግ ወይንም ቶራ የምንላቸው ለሙሴ ተሰጥተው የነበሩት በ1445-1405 ዓመተ ዓለም ውስጥ ነው፡፡ የመጨረሻው መገለጥ ደግሞ ተሰጥቶ የነበረው ለሐዋርያው ዮሐንስ ሲሆን ይህም በ90-96 ዓመተ ምህረት ነበር፡፡ (በቅርብ እንዲፈፀሙ የተነገሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች በታሰቡበት ጊዜ ያለምንም መምታታት የተፈፀሙ ሲሆን ወደ ፊት እንደሚፈፀሙም የተነገሩት እንዲሁ ያለምንም መምታታት እንደሚፈፀሙ ግልጥ ነው፣ ይህንንም የምንለው የከዚህ በፊቶቹ በዝርዝርና በተናጠል ተፈፅመው በመረጋገጣቸው ነው)፡፡

በጥንት ከተነገሩትና ከተፈፀሙት ትንቢቶች መካከል አንዱ ምሳሌም የጥንት የጢሮስ መንግስት መውደም ነበር፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የክስተቱን ዝርዝር ሁኔታ እንኳን ማለትም  የከተማዋ ድንጋዮች እንኳን ሳይቀሩ በታላቁ አሌክሳንደር ወደ ባህር እንደሚወረወሩ ሕዝቅኤል 26.3፣ 7-14 አስቀምጦታል፣ ልክ እንደተተነበየውም ምንም ነገር ሳይዛነፍ እያንዳንዱ ነገር በዝርዝር ተፈፅሟል፡፡ የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደኢየሩሳሌም በድል መግባት ከመፈፀሙ 400 ዓመታት በፊት በዳንኤል ትንቢት ተነግሮ ነበር፡፡ ዳንኤልም የተነበየውና በ70 ዓመተ ምህረት የሆነውን የአይሁዶችን ቤተመቅደስ ሙሉ ለሙሉ መፍረስና የአይሁድን ሕዝብ በመላው ዓለም ውስጥ መበተንን ነበር፡፡ እንደተተነበየው ሁሉም ነገር በትክክልና ያለምንም መዛነፍ ተፈፅሟል፡፡ በተመሳሳዩ ምዕራፍ ውስጥ የሐሰተኛውን ክርስቶስ ማንነትና ገፀ ባህርይን ዳንኤል በትክክል ገልፆታል ዳንኤል 9.20-27፡፡ እንዲሁም ደግሞ ነቢዩ ዳንኤል የክርስቶስን ዳግም ምፅዓትና ሕዝቦችም ሁሉ እንደሚያመልኩት በራዕዩ ውስጥ አይቶት በትንቢቱ ላይ አስቀምጦታል ዳንኤል 7.13-14፡፡

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስም እራሱ ስለ ኢየሩሳሌም መፍረስ ዝርዝር ክንውኖችን ተናግሯል፡፡ እሱም የተናገረው በኢየሩሳሌም ዙሪያ ምሽግ እንደሚገነባ በጠላት ወታደሮች እንደምትከበብ እንዲሁም ከተለያየ አቅጣጫ እየተጠቃች በመደቆስ እራሷን እንደምታገኘው ነው፡፡ በግንቧም ውስጥ በዓመፅ የሚደረጉ ግድያዎች እንዳሉ (ሁኔታውም እጅግ በጣም አሰቃቂ እንደሆነ) ተናግሯል፡፡ ቀጥሎም የታላቁ ቤተመቅደስ ድንጋዮችም እንኳን እንደሚወገዱና እንደሚወረወሩ ጌታ ኢየሱስ ተናግሯል የተናገረውም ሁሉ በትክክል ተፈፅሟል፡፡ ለዚህም ጥፋት ምክንያት የሆነውን ነገር ጌታ ኢየሱስ ገልጦታል፡፡ የአይሁድ መሪዎች በእሱ ስጋ መልበስ ውስጥ እግዚአብሔር ሰው ሆኖ መምጣቱን አለመቀበላቸውንም ጭምር ገልጧል፣ ሉቃስ 19.41-44፡፡

ታሪክ ጸሐፊው ፍላቪየስ ጆሴፈስ በኢየሩሳሌም መፍረስ ላይ የተነገረውን የዚህን የጌታ ኢየሱስን ትንቢት ፍፃሜ ገልፆታል፣ 1‚900 ዓመት በፊት The Complete Works of Josephus (published today by Trans. William Whiston. Grand Rapids, MI: Kregel Publications, 1981, pages 566-568, 589)፡፡ ጆሴፈስ የጻፈው በ70 ዓመተ ምህረት ታይተስ ኢየሰሩሳሌምን እንዳጠቃ ነው፡፡ የሮም ጦር አዛዡ ታይተስ በኢየሩሳሌም ቅጥር ዙሪያ ቅጥርን እንደገነባና ከከተማዋ ማንም እንዳይወጣ፣ ሕዝቡንም በከተማዋ ውስጥ እንደዘጋባቸው ይናገራል፡፡ ቄሳር እራሱ ቤተመቅደሱ እንዳይፈርስ ትዕዛዝን ሰጥቶ ነበር፡፡ ወታደሮቹ ግን እጅግ በጣም በታላቅ ቁጣ ስለነበሩ በቅጥሩ ውስጥ ማንም እንዳይተርፍ ሁሉንም ገድለው ኢየሩሳሌምን፣ የታላቁን ቤተመቅደስንም ግንቦች እስከ መሰረቱ ድረስ አፈራረሱት ድንጋዮችንም አስወገዱ፡፡

ቀደም ብሎ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ እንደተገለጠው፣ ሙስሊሞች የሚያምኑት ኢየሱስ እውነተኛዋን ቤተክርስትያን ለመመስረት ስላልቻለ አላህ መሐመድን መላክ ነበረበት በማለት ነው፣ ይህም ኢየሱስ ትቶት የሄደውን መምታታት ለማስተካከል መሐመድ እንዲችል በማለት ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስ እንደተነበየው ደግሞ የገሃነም ደጆችም እንኳን የእሱን ቤተክርስትያን ሊቋቋሟት አይችሉም ማቴዎስ 16.18፡፡ እሱም የተናገረው ወንጌል ለዓለም ሁሉ እና ለሕዝቦች ሁሉ፣ ለቋንቋ ሁሉ፣ ከተሰበከ በኋላ እሱ እንደገና እንደሚመጣ ነው ማቴዎስ 24.14፡፡ በጣም ጥቂት ተከታዮች ለነበሩትና በከፍተኛ ተቃውሞ ውስጥ ለነበረው ክርስትና ይህ ግልፅ የሆነ ትንቢት ነው የተነገረ ሲሆን፣ አሁንም በትክክል በጌታ እንደተተነበየው በትክክል እየተፈፀመ ነው፡፡ አስደናቂ የሆነውም የወንጌል ስብከት ለዓለም ሁሉ የመሰበኩ እውነታ በቅርብ ጊዜ ውስጥ በትክክል ተፈፅሞ ነገሮች ሁሉ ይጠቃለላሉ፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ በትንቢቶቹ እውነተኝነቱን እንዳረጋገጠው ሁሉ፣ ዳግም ምፅዓትንና የመጨረሻውን ፍርድም በተመለከተ የተናገረው ነገር ሁሉ እንደሚፈፀም ክርስትያኖች ይጠባበቃሉ፡፡ በብሉይ ኪዳንም ሆነ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ብዙ ትንቢቶች አሉ፡፡ የአዲስ ኪዳን የመጨረሻውን መጽሐፍ ጨምሮ (የራዕይን መጽሐፍ ጭምር) ትንቢቶቹ ሁሉ ሙሉ ለሙሉ ትኩረት ያደረጉትና የሚናገሩት ስለ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስ የተናገረው ከምድራዊው አገልግሎቱ በኋላ ሳይመለስ ለረጅም ጊዜ እንደሚቆይና ያም የመጨረሻውም ቀን (የሚመጣበት ቀን) ሳይጠበቅ በድንገት እንደሚመጣ ነው፡፡ ያ ጊዜ ታላላቅ የተፈጥሮ አደጋ ክስተቶች ይከተሉታል፣ ሙታን ይነሳሉ፣ ሰይጣንም ይሸነፋል፡፡

እግዚአብሔርን ለማይከተሉት የዚያን ጊዜው ሁኔታ እጅግ በጣም አስፈሪ እንደሚሆን ነው፡፡ በጌታ በኢየሱስ ፀጋ ለዳኑት ለእግዚአብሔር ልጆች ግን አስደናቂ የሽልማት ጊዜ ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስ መምጣቱ በእግዚአብሔር የመለከት አዋጅ ይታወጃል፣ ከዚያም በሰማያዊ ዙፋኑ ላይ ተቀምጦ በክብር በዓለም ሁሉ ላይ ለመፍረድ ይመጣል፡፡ በእግዚአብሔር ፀጋ የዳኑት በጣም ይደነቃሉ፣ እግዚአብሔር የምህረት እና የደግነቱን እጅ በመዘርጋቱ በክርስቶስ በኩል ይቅር ተብለው እና በፀጋው ብቻ በመዳናቸው በጣም ይደነቃሉ ማቴዎስ 10.40-42፣ እና ማቴዎስ 25.31-46፡፡ እነዚያም ወደ እግዚአብሔር ዘላለማዊ ሽልማት ውስጥ የሚገቡት በክርስቶስ መስቀል ትንሳኤና የኃጢአታቸው ዕዳ ሙሉ ለሙሉ ተከፍሎላቸዋልና፡፡

የአዘጋጁ ማሳሰቢያ፡-

ነቢያትን እውነተኞች ወይንም ሐሰተኞች በማለት ለመፈረጅ የሚቻልበት ግልፅ የሆነ መመሪያ በጌታ ቃል ላይ ተሰጥቷል፡፡ ነቢዩ የተናገረው ቃል ተፈፃሚነት ያለውና የሌለው መሆኑ ለእውነተኛነቱ ዋናው መፈተኛ ነበረ፡፡ ነቢዩ የተናገረው ነገር ተፈጻሚ ካልሆነ፣ የሐሰት ነቢይ ለመሆኑ ዋና ማስረጃ ሲሆን ሰዎች እሱን መቀበልና እንደ ነቢይም መስማት እንደሌለባቸው የእግዚአብሔር ቃል መመሪያ አጥብቆ ያሳስባል፡፡ ለዚህም ዋናው ምክንያት፣ ነቢዩ የሚናገረው ከእምነት እና እግዚአብሔርን ከማምለክ ደግሞም ከዘላለም ሕይወት ጋር የተያየዘ ጉዳይ በመሆኑ ነው፡፡  

በአንድ ሰው ሕይወት ዋናና ወሳኝ  ከሚባሉት ጉዳዮችም ውስጥ አንዱ የእምነት ጉዳይ ነው፡፡ የምንከተለው እምነት እውነተኛ ነው ወይንስ አይደለም የሚለውን መርምረን እንድናውቅ አዕምሮ፣ ችሎታና ማስተዋልን እግዚአብሔር ሰጥቶናል፡፡ ከዚህም ባሻገር እውነቶቹን ልናውቅ የምችልበትንም አጋጣሚዎች በመፍጠርና በማመቻቸት እንድንነቃ ያደርገናል፡፡ እንደዚህ ከሚጠቀምባቸው መጠቀሚያዎቹም ውስጥ አንዱ የዚህ ድረ ገፅ መኖር ነው፡፡

ከላይ ባየነው ርዕስ ውስጥ በቁራን ላይ ያለው ትንቢት በመሐመድ ጊዜም ሆነ ከመሐመድ በኋላ ስለመሆኑ ታሪካዊ ማስረጃ የለም፡፡ ስለዚህም ትንቢቱ የሚፈረጀው የሐሰት ትንቢት ተብሎ ነው፡፡ ሌሎቹም ብዙ በርካታ አስቸጋሪ ስህተቶች በቁራን ውስጥ ሞልተዋል፡፡ የምንከተለው እምነት በስህተት የተሞላ ከሆነ ቆም ብለን ማሰብና መከተል የሚገባንን መመርመር ይገባናል፡፡

አንባቢዎች ሆይ! የምትከተሉት እምነት እውነተኛ የመሆኑና ያለመሆኑ ጉዳይ፣ የዘላለምን ሕይወት የት እንደምታሳልፉ የሚወስን በመሆኑ በቀላሉ የምትመለከቱት መሆን የለበትም፡፡ ስለዚህም የዚህ ገፅ አዘጋጆች የምንመክራችሁ ምክር ምንም ስህተት የሌለበትን የእምነት መጽሐፍ፣ ማለትም መጽሐፍ ቅዱስን በመፈለግ በማስተዋል እንድታነቡና በውስጡም ስለ እግዚአብሔር ደግሞም ስለሰው ልጅ ያለውን ትምህርት በእርጋታ እንድትቀስሙ ነው፡፡ አንድ ኃጢአተኛ ከእግዚአብሔር ጋር ሊታረቅ የሚችለው እንዴት ነው? ከእግዚአብሔር ዘንድ ይቅርታና የኃጢአት ሥርየት የሚገኘው እንዴት ነው? የሕይወት ትርጉም እና ዓላማስ ምንድነው? አንድ ሰው በዚህ ምድር እውነተኛውን አምላክ ማምለክና መከተል ያለበት ለምድነው? ወ.ዘ.ተ ለሚሉት ጥያቄዎች ሁሉ ትክክለኛውን መልስ ልታገኙ የምትችሉት ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብቻ ነው፡፡ ለእነዚህ ጥያቄዎች ትክክለኛውን መልስ እስክታገኙ ድረስ የሕሊና እረፍት ሊኖራችሁ አይገባም፣ እኛን ያሳረፈን እግዚአብሔር እናንተንም እንዲረዳችሁ ፀሎታችን ነው፣ እግዚአብሔር ይርዳችሁ አሜን፡፡

 

የትርጉም ምንጭ: Predicted World Events, Chapter 24 of "A Topical Study of the Qur'an From a Christian Perspective" by M.J Fisher, M.Div

ሙሉ መጽሐፉ በአማርኛ: ርእሳዊ የቁርአን ጥናት በክርስትና አይን ሲመረመር

ለእስልምና መልስ አማርኛ  ዋናው ገጽ